Site icon ETHIO12.COM

ወድቆ የተገኘን ንብረት/ገንዘብ የራስ ማድረግ እና አግኝቶ መደበቅ ወንጀል

መግቢያ

ይህ አጭር ጽሁፍ በተንቀሳቃሽ ንብረት ላይ ከሚፈጸሙ ወንጀሎች የሚመደቡት ወድቆ የተገኘን ንብረት/ገንዘብ የራስ ማድረግ እና አግኝቶ መደበቅ ወንጀል ላይ አጭር ዳሰሳ ለማድረግ የተዘጋጀ ነው፡፡ በጽሁፉ ስለንብረት መብት ምንነት እና በንብረት ላይ የሚፈጸሙ ወንጀሎች ባጭሩ ለመቃኘት የምንሞክር ሲሆን በዋናነት ከላይ በርእሱ የተገለጹት ወንጀሎች ላይ ትኩረት የምናደርግ ይሆናል፡፡

ስለ ንብረት መብት በጠቅላላው

ከሰው ልጆች መሰረታዊ ሰብአዊ መብቶች መካከል የንብረት መብት አንዱ ነው፡፡ የንብረት መብት መሰረታዊ ሀሳብም አንድ ሰው በጥረቱ ወይም ለፍቶ ባገኘው ንብረት ወይም ገንዘብ ላይ ያለ ማንም ጣልቃ ገብነት ብቸኛ ባለቤት (exclusive owner) መሆኑን የሚገልጽ የህግ ጽንሰ ሀሳብ ነው፡፡ ይህ የንብረት መብት ባለቤቱን በዋነኛነት ሶስት መብቶችን የሚጎናጽፍ ሲሆን እነሱም ንብረቱን ለራሱ የመጠቀም፣ በአላባ የመስጠት እና ለሶስተኛ ወገን በመሸጥ መለወጥ የማስተላለፍ መብትን ለባለንብረቱ ያጎናጽፋል፡፡ ሌሎች ሰዎች ያለ ህጋዊ የንብረቱ ባለቤት ፍቃድ በሌላ ሰው ንብረት እነዚህን መብቶች መጠቀም አይችሉም፡፡ ይህ የንብረት መብት በኢ.ፌ.ዲ.ሪ ህገመንግሰት አንቀጽ 40 እና በ1952ቱ የፍትሐብሄር ህግ በመጽሀፍ ሶስትና ሰባት በተደነገው አግባብ የንብረት ይዞታ እና ባለቤትነት መብት ሰፊ ጥበቃ ተደርጎለት ይገኛል፡፡

በንብረት ላይ የሚፈጸም ወንጀል በጠቅላላው

ከፍትሀብሄራዊ የንብረት መብት ጥበቃ ባለፈ አንድ ሰው የንብረት መብት ላይ የሚፈጸም የወንጀል ተግባር ተጠያቂነትን እንደሚያስከትል በ1996 ዓ.ም.በወጣው የወንጀል ህግ በመጽሀፍ ስድስት ከአንቀጽ 662 ጀምሮ በንብረት ላይ የሚፈጸሙ ወንጀሎች በሚል ርእስ በዝርዝር ተደንግጎ ይገኛል፡፡ እነዚህ ወንጀሎች በሚንቀሳቀስ እና በማይንቀሳቀስ ንብረት ላይ ሊፈጸሙ ይችላሉ፡፡ በዚህ የህጉ ክፍል እንደተደነገገው በተንቀሳቃሽ ንብረት ላይ ከሚፈጸሙ ወንጀሎች መካከል ስርቆት፣ ሀይል መስረቅ፣ ውንብድና፣ ዘረፋ፣ እምነት ማጉደል፣ መሸሸግ፣ በሰው ይዞታ ላይ ጉዳት ማድረስ፣ ወድቆ የተገኘን ንብረት የራስ ማድረግ፣ አግኝቶ መደበቅ እና ሌሎች መሰል በንብረት መብት ላይ የሚፈጸሙ ወንጀሎች ይገኙበታል፡፡ እነዚህ ወንጀሎች የየራሳቸው ባህሪ ያሏቸው ሲሆን ተፈጽመው ሲገኙም የሚስቀጡት ቅጣት እንደ ወንጀሉ አፈጻጸም ብሎም የወንጀሉ ሰለባ የሆነው ንብረት ዋጋ ግምት የክብደት መጠንን መነሻ በማድረግ በመቀጮ፣ እስከ አምስት አመት በሚደርስ ቀላል እስራት እና እስከ 25 አመት ሊደርስ በሚችል ጽኑ እስራት የሚያስቀጡ ናቸው፡፡ ከዚህ ቀጥሎ እንደምናየው ለዚህ አጭር ጽሁፍ አላማ እላይ ከተዘረዘሩት ወንጀሎች መካከል ወድቆ የተገኘን ንብረት የራስ ማድረግ እና አግኝቶ መደበቅ ወንጀልን እናያለን፡፡ በተጨማሪም የተገኘው ንብረት የወንጀል ፍሬ ከሆነ እንዲሁ የሚያስከትለው የወንጀል ተጠያቂነትን በተመለከተ አጭር ዳሰሳ የምናደርግ ይሆናል፡፡

አግኝቶ መደበቅ

ከወንጀሉ ርእስ መረዳት እንደሚቻለው አንድ ሰው ከህጋዊ መንገድ ውጪ ንብረት አግኝቶ በዚሁ ንብረት ያለአግባብ ለመበልጸግ በማሰብ ንብረቱን ለመደበቅ የሚፈጽመው የወንጀል ተግባር ነው፡፡ በወንጀል ህጉ አንቀጽ 679 መሰረት ማንም ሰው የማይገባውን ብልጽግና ለማግኘት ወይም ለሌላ ሰው ለማስገኘት በማሰብ የሌላ ሰው ንብረት የሆነውን በስህተት ወይም ባልታሰበ ድንገተኛ አጋጣሚ ነገር፣ እንደ ውሃ ማእበል እና ነፋስ ባለ በተፈጠሮ ጠባዩ በመጣ ሀይል እና ከባለንብረቱ ፈቃድ ውጭ በሆኑ ማናቸውም ሁኔታ ከባለቤቱ እጅ ወጥቶ በእጁ የሚገኝን ንብረት ወይም እቃ ለራሱ ወይም ለሌላ ሰው ካደረገ በወንጀል ያስጠይቀዋል፡፡ በተጨማሪም ንብረትነቱ የሌላ ሰው የሆነ እንሰሳ ሸሽቶ በመጠጋቱ ምክንያት በእጁ ስለገባ የራሱ ካደረገ እንዲሁ የሚያስጠይቅ የወንጀል ተግባር ነው፡፡ ቅጣቱን ስናይ በመቀጮ ወይም በቀላል እስራት ያስቀጣል ሲል የወንጀል ህጉ ደንግጓል፡፡ በዚህ አንቀጽ አግባብ ማንኛውም ሰው በማንኛውም ሁኔታ አንድ ንብረት በስህተት ወይም ሌላ ሰው ሰራሽ ወይም ተፈጠሮአዊ አደጋ ምክንያት በእጁ ስለገባ የራሱ ወይም የሌላ ሰው ንብረት ማድረግ የሚያስቀጣ የወንጀል ተግባር ነው፡፡ ለምሳሌ አንድ ሰው በባንክ ገንዘብ ሲልክ በስህተት ወደ ሌላ ሰው የሂሳብ ቁጥር ገንዘቡ ቢላክ የዚህ የሂሳብ ቁጥር ባለቤት ገንዘቡ በስህትት መግባቱን ለባንኩ ሪፖርት በማድረግ ወደ ህጋዊ የሂሳቡ ባለቤት እንዲመልስ ማድረግ አለበት፡፡ ይህን ሳያደርግ ቀርቶ ይልቁንም ገንዘቡን የራሱ ለማድረግ ወይም የሌላ ሶስተኛ ሰው ለማድረግ ከሞከረ በቀላል አስራት ወይም በመቀጮ ያስቀጣል፡፡ እዚህ ላይ ቀላል እስራት ሲባል በወንጀል ህግ ጠቅላላ ክፍል አንቀጽ 106 አማካይነት እስከ ሶስት አመት ሊደርስ የሚችል ቀላል እስራት ሲሆን በልዩ ሁኔታ እንደ ወንጀሉ አፈጻጸም እና በደረሰው ጉዳት ልክ የእስር ቅጣቱ እስከ አምስት አመት ሊደርስ ይችላል፡፡ በሌላ ምሳሌ አንድ የሌላ ሰው ንብረት የሆነ እንሰሳ ወደ ተጠተርጣሪው በመጠጋቱ ተጠርጣሪው የራሱ ሊያደርገው የተለያዩ ነገሮችን ቢፈጽም ለምሳሌ በእንሰሳው ላይ የራሱ ንብረት ለማስመሰል ምልክት ቢያደርግበት ወይም የራሱ አስመስሎ ለሽያጭ ቢያቀርበው በዚሁ ድንጋጌ መሰረት የሚቀጣ ይሆናል፡፡

ወድቆ የተገኘን ንብረት/ገንዘብ የራስ ማድረግ

ይህ ወንጀልም ከላይ በተራ ቁጥር አንድ ላይ ካነሳነው ወንጀል ጋር ተቀራራቢነት አለው፡፡ በወንጀል ህጉ አንቀጽ 680 መሰረት ማንም ሰው አንድ የጠፋ ንብረትን አግኝቶ የሄንኑ ለባለስልጣን ሳያሳውቅ ከቀረ ወይም የንብረቱን ባለቤት ለማወቅ አስፈላጊውን ጥረት ሳያደርግ ከቀረ እና ንብረቱን ለራሱ ካደረገው እስከ አምስት ሺ ብር ወይም ነገሩ ከባድ ሲሆን እስከ አንድ አመት ቀላል አስራት ሊቀጣ እንደሚችል ህጉ ደንግጓል፡፡ በተጨማሪም የተደበቀ ገንዘብ ወይም ሀብት አግኝቶ በህግ መሰረት ለመንግስት ገቢ እንዲሆን አስፈላጊውን ማስታወቂያ ሳይሰጥ መቅረት ወይም ለባለቤቱ አስፈላጊውን ክፍያ ሳይሰጥ ንብረቱን የራሱ ያደረገው እንደሆነ እንዲሁ ከላይ በተገለጸው አግባብ የሚቀጣ ይሆናል፡፡ ከዚህ ድንጋጌ መረዳት የሚቻለው ማንም ሰው ባለቤት ሊሆን የሚችለው ለፍቶና ጥሮ ባፈራው ንብረት ብቻ መሆኑን ነው፡፡ ከዚህ ውጪ የሌላ ሰው የሆነን ንብረት ወድቆም ሆነ ተደብቆም ከተገኘ ያገኘው ሰው በዚህ ሀብት ወይም ገንዘብ ላይ ምንም የባለቤትነት መብት የሌለው መሆኑን እና ይህን ንብረት ለህጋዊ ባለቤቱ ወይም እሱን ማግኘት ካልቻለ ለፍትህ አካለት ወይም በቅርብ ለሚገኝ የመንግስት አስተዳደር አካላት ማሳወቅና ንብረቱ ለባለቤቱ እንዲመለስ ጥረት ማድረግ ያለበት መሆኑን ነው፡፡ ይህን ሳያደርግ ንብረቱን የራሱ ለማድረግ መሞከር በወንጀል የሚስጠይቅ እና ከላይ በተገለጹት ቅጣት የሚያስቀጣ መሆኑን መረዳት ያስፈልጋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ልብ ሊባል የሚገባው በወንጀል ህጉ አንቀጽ 98 መሰረት በጥፋተኛው ላይ ከሚወሰነው የገንዘብ ቅጣት እና የእስር ቅጣት በተጨማሪ ከወንጀሉ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ የተገኘው ንብረት ይወረሳል፡፡

ወድቆ የተገኘው ወይም ተገኝቶ የተደበቀው ገንዘብ ወይም ንብረት የወንጀል ድርጊት ፍሬ ሲሆን የሚኖር ተጠያቂነት

ተገኝቶ የተደበቀው ወይም ወድቆ የተገኘው ንብረት ምናልባትም ምንጩ የወንጀል ድርጊት ሊሆን ይችላል፡፡ ለምሳሌ በስህተት በተጠርጣሪው የባንክ ሂሳብ ቁጥር የገባው ገንዘብ በሙስና ወንጀል የተገኘ ቢሆን በጉቦ መቀበል የተገኘ ገንዘብ ሊሆን የችላል፡፡ በዚህ ጊዜ ገንዘቡ በእጁ ወይም ሂሳብ ቁጥር የገባው ሰው የባንክ ሂሳቡን በመቆጣጠር ረገድ አስፈላጊውን ጥንቃቄ ማድረግ ያለበት ሲሆን ይሄን ጥንቃቄ ሳያደርግ ቀርቶ በወንጀል ድርጊት የተገኘ ገንዘብ በሂሳቡ ገብቶ እሱም ይንኑ ገንዘብ አለአግባብ ለመበልጸጊያነት ቢጠቀመው ወይም ሌላ ሰው እንዲጠቀመው ቢፈቅድ በወንጀል ድርጊት የተገኘ ገንዘብን ህጋዊ ማስመሰል ወንጀልን ለመከላከል እና ለመቆጣጠር በወጣው አዋጅ ቁጥር 780/05 በአንቀጽ 29 እና በወንጀል ህጉ አንቀጽ 59 መሰረት በቸልተኛነት ለፈጸመው ወንጀል የሚጠየቅ ይሆናል፡፡ በዚህ ድንጋጌ መሰረት ገንዘቡ ወይም ንብረቱ የወንጀል ፍሬ መሆኑን ማወቅ ሲገባው ይሄንኑ ሳያደርግ በመቅረት ገንዘቡን መረከብ፣ በይዞታው ማድረግ ወይም መጠቀም የንብረቱ መወረስ እንደተጠበቀ ሆኖ ከ10 እስከ 15 አመት ጽኑ እስራት እና እስከ ብር አንድ መቶ ሺ በሚደርስ የገንዘብ መቀጮ ሊያስቀጣ የሚችል ከባድ ወንጀል ነው፡፡

ባጠቃላይ ዜጎች የንብረት ባለቤት ሊሆኑ የሚችሉት ለፍተው ጥረው ባገኙት ገንዘብ ወይም ንብረት ሲሆን በስጦታም ሆነ በውርስ ለሚተላለፉላቸው ንብረቶችም እንዲሁ የባለቤትነት መብት ይኖራቸዋል፡፡ ከዚህ ውጭ በስህትት የተገኘ ንብረትን ወይም ወድቆ የተገኘን ንብረት ያገኘው ሰው ባለመብት ሊሆን የማይችል ሲሆን ለህጋዊ ባለቤቱ እንዲመለስ ማድረግ እና በዚህ ሂደት ውስጥ በቅርብ ላሉ የመንግስት አካላት ማሳወቅ ያስፈልጋል፡፡ ይህን አለማድረግ በወንጀል የሚያስጠይቅ ነው፡፡ ለምሳሌ በፋይናንስ ተkማት በሚኖር የገንዘብ ዝውውር ገንዘብ በስህተትም ሆነ በማናቸውም ምክንያት ሊላክለት ለማይገባ ሰው የባንክ ቁጠባ ሂሳብ ቁጥር የገባ ከሆነ ባለሂሳብ ቁጥሩ ስህተቱን ሳይቆይ ለባንኩ ማሳወቅ እና ባንኩ የማስተካከያ እርምጃ በመውሰድ ገንዘቡ ለህጋዊ ባለቤቱ እንዲመለስ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ ይህን አለማድረግ በወንጀል ህጉ አንቀጽ 679 መሰረት የሚያስጠይቅ ወንጀል ነው፡፡ ወድቆ የተገኘው ንብረት ወይም ተገኝቶ የተደበቀው ንብረት የወንጀል ፍሬ በሚሆንበት ጊዜ ተጠርጣሪው ከላይ የተገለጹትን የጥንቃቄ እርምጃ ካልወሰደ እና ይልቁንም ንብረቱን ለራሱ ወይም ለሶስተኛ ወገን ጥቅም ላይ እንዲውል ካደረገ በቸልተኝነት በሚፈጸም በወንጀል ፍሬ የተገኘን ገንዘብ ወይም ንብረት ህጋዊ አስመስሎ ማቅረብ ወንጀል ሊጠየቅ ይችላል፡፡

ስለዚህ በስህተት ወደ እኛ የመጣውን ገንዘብ ወይም ንብረት ባለቤቱን ለማግኘት ተገቢውን የማፈላለግ ጥረት በማድረግ ለህጋዊ ባለቤቱ መመለስ እና ለመንግስት አካላትም ማሳወቅ ያስፈልጋል፡፡ ይህን አለማድረግ አላይ በተገለጸው አግባብ በወንጀል የሚያስቀጣ ተግባር ነው፡፡

Via ministry of justice

Exit mobile version