Site icon ETHIO12.COM

አየርላንድ የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት እና የግዛት አንድነት ከሚጥሱ እንቅስቃሴዎች እንድትታቀብ ኢትዮጵያ ጠየቀች

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን አየርላንድ በኢትዮጵያ ላይ ዓለም ዓቀፍ ጫና እንዲደርስ የምትፈጽመው ድርጊት የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት የሚጋፋና የዓለም ዓቀፍ ህጎችን የጣሰ እንደሆነ በማስገንዘብ ለአየርላንድ የውጭ ጉዳይ እና የመከላከያ ሚኒስትር ሲሞን ኮንቬይ ደብዳቤ ልከዋል።

የአየርላንድ መንግስት ኢትዮጵያ በኢኮኖሚውም ሆነ በፖለቲካው መስኮች ላይ ለውጥ ለማምጣት የምታደርገውን ጥረት ከመደገፍ ይልቅ በተባበሩት መንግስታት የጸጥታው ምክር ቤት እና በአውሮፓ ህብረት ያላትን የአባልነት ወንበር በመጠቀም በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ ለመግባት የምታደርገው ያልተገባ እንቅስቃሴን ኢትዮጵያ እንደማትቀበለው አስታውቀዋል።

በመሆኑም አየርላንድ የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት እና የግዛት አንድነት ከሚጥሱ እንቅስቃሴዎች እንድትታቀብም ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ አሳስበዋል።

ኢትዮጵያ ከአየርላንድ ጋር ያላትን ታሪካዊ ግንኙነት ማስቀጠል እንደምትፈልግ የገለጹት አቶ ደመቀ፤ ኢትዮጵያ ከአውሮፓ ህብረት ጋር ያላትን ግንኙነት ለማስተካከል በምታደርገው ጥረት ልክ አየርላንድ የበኩሏን ጥረት ማድረግ ይገባታል ብለዋል።

ለዚህም አየርላንድ በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ በመግባት እንዳትረጋጋ የምታደርገውን ያልተገባ እንቅስቃሴ እንድታቆም ጠይቀዋል።

ኢትዮጵያ ከአየርላንድ ጋር ያላትን ግንኙነት በአዲስ መንፈስ ማደስ ትፈልጋለች ያሉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን፤ አየርላንድ አሸባሪውን ህወሃት በመደገፍ በጸጥታው ምክር ቤት እያንጸባረቀች ያለችው አቋም ከኢትዮጵያ ጥቅም በተቃራኒው የሚታይ በመሆኑ ግንኙነቱን ለማሻሻል የሚደረገውን ጥረት የሚረብሽ መሆኑን አስገንዝበዋል።

ሁለቱ ሀገራት ዓለም አቀፍ ህጉ በሚፈቅደው መሰረት ግንኙነታቸውን ማጠናከር እንደሚችሉ ጠቅሰው፤ የአየርላንድ መንግስት ኢትዮጵያ እንዳትረጋጋ ከሚያደርገውን ያልተገባ እንቅስቃሴ እንዲታቀብም ጠይቀዋል።

የጋራ ፈቃደኝነት እስካለ ድረስ ኢትዮጵያ ከአየርላንድ መንግስት ጋር ያላትን ግንኙነት ቀደም ሲል ወደነበረበት ለመመለስ ያሉ ዕድሎችን ለመጠቀም ዝግጁ መሆኗንም ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ ከአየርላንድ ጋር የነበራትን የሁለትዮሽ ግንኙነት በሀገራቱ ሉዓላዊነት እና የጋራ ተጠቃሚነት መርህ ላይ በመመስረት ለማስተካከል ካላት ፍላጎት በመነጨ ከመንግስትዎ ቀና ምላሽ እንደሚመጣ ትጠብቃለች ብለዋል።

ኢትዮጵያ ከአየርላንድ ጋር ያለው ግንኙነት እንዲስተካከል የተለያየ ጥረት ማድረጓን አስታውሰው፤ እስካሁን ድረስ በተደረገው ጥረት በአየርላንድ በኩል ተስፋ ሰጪ ነገር ሊታይ እንዳልቻለ ገልጸዋል።

በተቃራኒው አሸባሪው ህወሃትን በመደገፍ በኢትዮጵያ መንግስት ላይ የጸጥታው ምክር ቤት ጫና እንዲያሳድር አየርላንድ ጥረት እያደረገች እንደምትገኝ ገልጸዋል።

በመሆኑም የአየርላንድ መንግስት በኢትዮጵያ ግጭት እንዲባባስ ከሚፈጽመው ድርጊቱ እንዲቆጠብ ጠይቀዋል።

(ኢዜአ)

Exit mobile version