Site icon ETHIO12.COM

ተመድና አንዳንድ አገራት እንደሚሉት በትግራይ ከቁጥጥር ውጭ የሆነ ነገር የለም

መንግስት የአፍሪካ ሕብረት የሰላም ውይይቱ የሚካሄድበትን ቀን እስኪያሳውቅ በመጠባበቅ ላይ እንደሚገኝ በይፋ የቲወተር ገጻቸው ያስታወቁት አቶ ሬድዋን ሁሴን፣ በትግራይ ከአቅም በላይ የሆነና ከቁጥጥር ውጪ የሆነ ነገር እንደሌለ አመልክተዋል። የተመድ ጸሃፊ አንቶንዮ ጉተሬዝን ጨምሮ አሜሪካና የአውሮፓ ህብረት በትግራይ ልዩ ስጋት እንዳላቸው ላስታወቁት ምላሽ ነው አቶ ሬድዋን ይህ ያሉት።

ጦርነቱ ከተጀመረ ጀምሮ ድምጹን አጥፍቶ የነበረው የመንግስት የመረጃ ልሳን በተከታታይ እንዳስታወቀው መንግስት ሽሬን፣ አላማጣንና ኮረምን በእጁ አድርጎ ዜጎችን እያረጋጋ መሆኑንን አስታውቋል። ከትህነግ በኩል ሽሬና አንዳን ስፍራዎች መያዛቸውን በይፋ ከማመናቸው በስተቀር ስም ጠርተው ኮረምና አላማጣን እንደተነጠቁ ማረጋገጫ አልሰጡም።

“በሰሜን ኢትዮጵያ በተፈጠረው ግጭት ከቁጥጥር ውጪ የወጣ ነገር የለም፤ ሁሉም ነገር በታቀደው መሰረት እየሄደ ነዉ” ያሉት አቶ ሬደዋን “አንዳንዶች በሰሜን ኢትዮጵያ የተፈጠረው ግጭት ከቁጥጥር ውጪ ሆኗል በሚል እየተጠቀሙበት ያለው አገላለጽ ከእውነት የራቀ ነው” ሲሉ የመንግስት ኮሙኒኬሽን ላወጣው መግለጫ ማጠንከሪያ ሰንዝረዋል።

በይፋ አይነገር እንጂ መንግስት ነጻ ባወጣቸው አካባቢዎችና ከተሞች እርዳታ ለማሰራጨት ከተለያዩ የውጭ አገር ድርጅቶችና አገራት ጋር ስምምነት ላይ ተደርሷል።

ቀደም ሲል “ግጭቱ ወደ ሌሎች ክልሎች ተስፋፍቶ ነበር፣ አሁን ግን እንደቀድሞው ዓይነት ነገር የለም፤ የመከላከል እርምጃው በታሰበው በወጣለት ዕቅድ መሰረት እየተከናወነ ነው” ያሉት የጠቅላይ ሚኒስትሩ የደህንነት አማካሪ፣ “የሰብአዊ እርዳታ አቅርቦትና አገልግሎት በቅርቡ ይጀመራል”ሲሉ ከላይ ለተገለጸው ድጋፍ የሚሆን ሃረግ በደፈናው ጽፈዋል።

የኢትዮጵያ ጥምር ጦር በከፍተኛ የውጊያ ዲሲፒሊን ሶስቱንም ከተሞች የከተማ ውጊያ ሳያደርግ መቆጣጠሩን የገለጸው የመንግስት ኮሙኒኬሽን፣ የትህነግ አመራሮች እልቂቱ የከፋ እንደሆነ በተደጋጋሚ ለሚገልጹት ምላሽ ሰጥተዋል።

ቢቢሲ የትህነግን ሃይሎች ጠቅሶ እንደጻፈው በርካቶች ለመፈናቀልና ለህልፈት ተዳርገዋል። እንደ ቢቢሲ ገለጻ አሁን ትግራይ ላይ ያለው ችግር ከቁጥጥር ውጪ ሊወጣ እንደሚችል ነው። ቢቢሲ ለዜናው ግብዓት ይሆኑት ዘንዳ ይህን ቢልም በመንግስት በኩል በተቃራኒው ስራዎች በወጉ እየሄዱ ነው ተብሏል።

በትግራይ ምግብ፣ መድሃኒትና የመሰረታዊ ፍላጎት ችግር ከፍተኛ ደረጃ ላይ መድረሱን በርካቶች እየገለጹ ነው። መንግስት ለዚህ ችግር አስቸኳይ መላ መፍለግና የትግራይን ህዝብ ሊታደግ እንደሚገባ በስፋት እየተገለጸ ነው።

ይህ በንዲህ እንዳለ ጦርነቱን አስመልክቶ ለሳንቲም መሰብሰቢያና ለሌሎች ፖእቲካዊ ዓላማዎች ሲባል መረጃ የሚያሰራጩ ጥንቃቄ ሊወስዱ እንደሚገባ ገለልተኛ ወገኖች እየተማጸኑ ነው። አሁን ላይ ችግር ማባባስና ህዝብን ማናከስ ዋጋ እንደሌለው፣ ሌላ ዋጋም እንደሚያስከፍል በመግለጽ አደራቸውን ያስተላለፉ እንዳሉት ጥንቃቄ እጅግ አስፈልጊ ነው።

በዚህ ጦርነት አሸናፊና ተሸናፊ እንደሌለ በመረዳት ለተወሰኑ ጊዜያት ቢሆን ሳንቲሙም፣ ሴራውም፣ ክፋቱንም በማስታገስ ሁሉንም ወገን ለማቀራረብና ስጋትን ለመግፈፍ በሚያስችል አውድ በጥንቃቄ የሚዲያው ስራ እንዲከናወን ነው ጥሪ የቀረበው።

Exit mobile version