ETHIO12.COM

የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ጥምረት በኢትዮጵያ ጉዳይ ልዩነት እንደሌለ አስታወቀ፤ በአንድነት እንቁም አለ

“አዲስ አበባ ተቀምጠው በውልክልና ኢትዮጵያን የሚያስለበልቡ የሁለት ምኞት ባሮች አክትሞላቸዋል” ሲሉ አሳባቸውን የሚሰነዝሩ ወገኖች የኢትዮጵያ የመጨረሻ ምጥ የመገላገያዋ እንዲሆን አንድ መሆን ግድ መሆኑንን ያሰምሩበታል። በዚህ እሳቤ የኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጥምረት ይህንኑ በማጉላት “ለኢትዮጵያ እቆማለሁ፣ ድምጼን አሰማለሁ” ሲል ለነገ በተጠራው ስብሰባ ሁሉም ኢትዮጵያዊ ነቅሎ እንዲወጣ ጥሪ አሰማ።

ፓርቲው ብቻ ሳይሆን ዜጎች በማህበራዊ ገጾቻቸው በመላው ኢትዮጵያ “አትንኩን፣ ተውን፣ ፍትሃዊ ሁኑ፣ ድምጻችንን ስሙ፣ በደላችንን ተረዱ፣ የትግራይ ህዝብም ሆነ ሌላው ህዝብ ልዩነት የለውም” በሚል ጥሪ እያስተላለፉ ያሉ ወገኖች የተለያዩ ፖስተሮችንም አዘጋጅተው እያሰራጩ ነው። ኢትዮጵያ በጦርነት ናፍቂው ትህነግ ላይ አሳረፈችውን የማያዳግም ምት በፖለቲካውም መድገምና ድሏን ማጽናት እንደሚገባት በብስለት መረጃዎች እየተንሸራሸሩ ነው።

ከአገር ውጭና በአገር ውስጥ በከፍተኛ መናበብ እየተከናውነ ባለው የተቃውሞ ሰልፍ ዝግጅትና ትግበራ ጎን ለጎን የፖኦለቲካ ፓርቲዎች ህብረት በጋራ፣ እንዲሁም የህብረቱ አካላት በድርጅታቸው አባሎቻቸው ድምሳቸውን እንዲያሰሙ ጥሪ ማድረጋቸው ተሰምቷል።

በሉዓላዊት ሀገር የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ መግባት ኢ-ፍትሓዊ አካሄድ ስለሆነ ተቀባይነት የለውም ሲሉ የኢትዮጵያ ፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ም/ቤት ባወጡት መግለጫ ላይ ተንተርሶ ኢዜአ የሚክለተለውን ዘግቧል።

በሉዓላዊት ሀገር የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ መግባት ኢ-ፍትሓዊ አካሄድ ስለሆነ ተቀባይነት የለውም ሲል የኢትዮጵያ ፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ም/ቤት አስገነዘበ።

የጋራ ምክር ቤቱ በኢትዮጵያ ላይ እየተደረገ ያለውን ጫና በመቃወምና ነገና ከነገ በስቲያ “ለኢትዮጵያ እቆማለሁ፣ ድምጼን አሰማለሁ” በሚል መርህ የሚካሄደውን ሰልፍ አስመልክቶ መግለጫ አውጥቷል። ንበመግለጫውም አንዳንድ የዉጪ ኃይሎች በኢትዮጵያ ላይ ጫና ለማሳደር የያዙትን አቋም በጽኑ አውግዟል።

በተለይም የተባበሩት መንግሥታት እና የአውሮፓ ህብረት ከዚህ አቋማቸዉ እንዲታረሙ እና ለሰላም ከኢትዮጵያ ሕዝብ ጎን እንዲቆሙ አሳስቧል።

በሰሜኑ ኢትዮጵያ የተፈጠረዉን የሰላም ችግር በየትኛውም ቦታ፣ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ እና በማንኛውም አጀንዳ ላይ በሰላማዊ መንገድ እና በአፍሪካ ህብረት አደራዳሪነት ለመነጋገር መንግስት አቋም መያዙን አስታውሶ፤ “የዉጪ ኃይሎች በተለይም የተባበሩት መንግሰታትና የአውሮፓ ህብረት በኢትዮጵያ ላይ ማዕቀብ ለመጣል የያዙት አቋም የሀገሪቱን ንጹሐን ዜጎች የሚጎዳ ከመሆኑም በላይ በአንዲት ሉዓላዊት ሀገር የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ መግባቱ ኢ-ፍትሓዊ አካሄድ ስለሆነ ተቀባይነት የለውም” ብሏል፡፡

ስለሆነም እነዚህ የውጭ ሃይሎች ከዚህ አቋማቸዉ እንዲታረሙ እና ለሰላም ከኢትዮጵያ ሕዝብ ጎን እንዲቆሙ ጥሪ አስተላልፏል። በአፍሪካ ህብረት የተጀመረዉን የሰላም ዉይይትና ድርድር ጥረት ከግቡ ለማድረስ እንዲቻል ምዕራባዊያን የሀገሪቱን የሉአላዊነት ክብር ሳይጥሱ፣ በሎጂስቲክስ እና አግባብነት ባለው ሙያዊ ድጋፍ ሰላምና መረጋጋትን ለማስፈን የሚደረገውን ጥረት ለማሳካት የበኩላቸውን እንዲወጡ የጋራ ም/ቤቱ በአጽንዖት ጠይቋል።

ጥቅምት 12 እና 13 ቀን 2015 ዓ.ም በአዲስ አበባ መስቀል አደባባይ እና በመላ አገሪቱ “ለኢትዮጵያ እቆማለሁ፣ ድምጼን አሰማለሁ” በሚል መሪ ሀሳብ በሚካሄደው የሰልፍ መርሀ-ግብር ኢትዮጵያዊያን እንዲሳተፉ ጥሪ አቅርቧል።

ኢትዮጵያውያን በጋራ በመቆም የሀገራችንን ሉዓላዊነት ያላከበረና ሕዝባችንን ህልውና ያላገናዘበ የዉጪ ጫና እንዲቆም ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ድምጽ እንድናሰማና በጋራ እንድናወግዝ ሲል የጋራ ም/ቤቱ ጥሪዉን አስተላልፏል።

የኢትዮጵያ ፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ም/ቤት የሰጠው መግለጫ ሙሉ ቃል እንደሚከተለው ቀርቧል:-

የኢትዮጵያ ፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ም/ቤት በአገራችን የተጀመረውን የዲሞክራሲ ግንባታ ሪፎርም ለማጠናከር እና የፖለቲካ ፓርቲዎች ያለባቸውን ሕጋዊ እና ማህበራዊ ኃላፊነት እንዲወጡ ለማስቻል በኃላፊነት እና ተጠያቂነት መንፈስ እየሠራ ያለ ተቋም ነው፡፡ በሀገራችን የዲሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ሂደት ውጤታማ ይሆን ዘንድ የፖለቲካ ፓርቲዎችን እንቅስቃሴ በማስተባበር የፖለቲካ መረጋጋት እና ሰላም እውን እንዲሆን የድርሻውን በመወጣት የሕዝባችንን ደህንነት ለማረጋገጥ ይሠራል፡፡

ሀገራችን አሁን የምትገኝበትን የፖለቲካ ምዕራፍ ለማለፍና በተለያዩ ማዕዘናት እየተፈጠሩ ላሉት አሳዛኝ የዜጎች ሞት፣ ግጭትና መፈናቀል ዋነኛ ምንጭ የሆኑትን መዋቅራዊ ችግሮችን መረዳትና ለእነዚህ መዋቅራዊ ችግሮች መነሻ የሆኑትን የአስተሳሰብ ምንጮችን ማወቅ፣ በእውቀት ላይ የተመሠረተና ችግር ፈቺ መፍትሄ ለመስጠት ያስችላል ብሎ ያምናል፡፡

ስለሆነም፡-

1. በሰሜኑ ኢትዮጵያ የተፈጠረዉን የሰላም ችግር በየትኛውም ቦታ፣ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ እና በማንኛውም አጀንዳ ላይ በሰላማዊ መንገድ እና በአፍሪካ ህብረት አደራዳሪነት ለመነጋገር መንግስት አቋም መያዙ እየታወቀ የዉጪ ኃይሎች በተለይም የተባበሩት መንግሰታትና የአውሮፓ ህብረት በኢትዮጵያ ላይ ማዕቀብ ለመጣል የያዙት አቋም የሀገሪቱን ንጹሐን ዜጎች የሚጎዳ ከመሆኑም በላይ በአንዲት ሉዓላዊት ሀገር የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ መግባቱ ኢ-ፍትሓዊ አካሄድ ስለሆነ ተቀባይነት የለውም፡፡ ስለሆነም የተባበሩት መንግሥታት እና የአውሮፓ ህብረት ከዚህ አቋማቸዉ እንዲታረሙ ለሰላም ከኢትዮጵያ ሕዝብ ጎን እንዲቆሙ የኢትዮጵያ ፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ም/ቤት ያሳስባል፡፡

2. በአፍሪካ ህብረት የተጀመረዉን የሰላም ዉይይትና ድርድር ጥረት ከግቡ ለማድረስ እንዲቻል ምዕራባዊያን የሀገሪቱን የሉአላዊነት ክብር ሳይጥሱ፣ በሎጂስቲክስ እና አግባብነት ባለው ሙያዊ ድጋፍ ሰላምና መረጋጋትን ለማስፈን የሚደረገውን ጥረት ለማሳካት የበኩላቸውን እንዲወጡ የጋራ ም/ቤቱ በአጽንዖት ይጠይቃል፡፡

3. የፊታችን ቅዳሜ እና እሁድ (ጥቅምት 12-13/2015ዓ.ም) በአዲስ አበባ መስቀል አደባባይ እና በመላው ኢትዮጵያ “ለኢትዮጵያ እቆማለሁ፣ ድምጼን አሰማለሁ” መርሀ-ግብር ኢትዮጵያዊያን በጋራ በመቆም የሀገራችንን ሉዓላዊነት ያላከበረና የሕዝባችንን ህልውና ያላገናዘበ የዉጪ ጫና እንዲቆም ለዓለም አቀፍ ማህበረሰብ ድምጽ እንድናሰማና በጋራ እንድናወግዝ የኢትዮጵያ ፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ም/ቤት ጥሪዉን ያስተላልፋል፡፡

ኢትዮጵያ በነፃነቷ ታፍራና ተከብራ ለዘላላም ትኑር! ጥቅምት 11 ቀን 2015 ዓ.ም. አዲስ አበባ

በተመሳሳይ ዜና ኢዜማ መግለጫ አውጥቷል።

ኢዜማ በነገው ሰልፍ ላይ አባላቱ እንዲሳተፉ ጥሪ አቀረበ


በሀገር ሉዓላዊነት እና በሕዝብ ደኅንነት ጉዳይ ላይ ኢትዮጵያውያን ያለ ልዩነት ተባብረን በህብረት መቆም እናውቅበታለን!

ኢትዮጵያ የገጠማት ችግር ግልጽ ነው፡፡ ጥያቄው የኅልውና እና የሉዓላዊነት ጉዳይ መሆኑ ገሃድ ወጥቷል፡፡ አዜማ በፖለቲካ ፕሮግራሙ ያስቀመጠው ቁጥር አንድ መርኅ ‹‹የኢትዮጵያ እና የሕዝቧ ጥቅም፤ ሰላም እና ደኅንነት ምንጊዜም ቅድሚያ ይኖረዋል›› የሚል ነው፡፡ በሀገር ሉዓላዊነት እና የኅልውና ጥያቄ በሚነሳበት ጊዜ እኛ ኢትዮጵያውያን በታሪክ እንዳስመሠከርነው ለጊዜው ውስጣዊ የፖለቲካ ልዩነቶቻችንን ወደጎን በመተው ከሀገር እና ከሕዝብ ፍላጎት ጎን በህብረት እንሠለፋለን፡፡

የውጪ ኃይሎች እጃቸውን በማስረዘም በሀገራችን የውስጥ ጉዳይ አዛዥ እና ናዛዥ ለመሆን የሚያሳዩትን ጣልቃ ገብነት በጽኑዕ የምንቃወመው ነው፡፡ በምንም ሁኔታ ውስጥ ብሔራዊ ጥቅማችንን የሚጎዳ የቱንም አይነት ጣልቃ ገብነት እንደማንቀበል በህዳሴው ግድባችን ሂደት ላይ ያስመሰከርን ሲሆን ህወሓት የቃጣብንን ጦርነትም በተመለከተም ለሰላማዊ ድርድርና መፍትሄ በራችንን ክፍት ማድረግ ላይ መንግስት የወሰደው ግልፅ አቋም የሚታወቅ ሆኖ ሳለ በሀገር ሉዓላዊነት እና ኅልውና ጉዳይ የሚመጣን የትኛውንም አይነት ጣልቃ ገብነት መታገስ እንደማንችል ግን ሊታወቅ ይገባል፡፡ እኛ ኢትዮጵያዊያን በህብረት ቆመን በአደባባይ ለዓለም መንግስታት ይህን እውነታችንን ለመናገር ለቅንጣትም አናመነታም፡፡

የመንግሥትን ሥልጣንን የያዘው የብልጽግና ፓርቲ ይህንን ሕዝባዊ ሠልፍ የፓርቲ አቋም መግለጫ ወይንም ነጥብ ማስቆጠሪያ ሳይሆን ለዘመናት በተከተልነው ማንነትን መሠረት ባደረገ ስሁት የፖለቲካ ሥርዓት የተራራቀውን ሕዝብ ለአንድ ዓላማ ማሠለፊያ አጋጣሚ አድርጎ እንዲጠቀምበት አጥብቀን እንመክራለን፡፡

የፓርቲያችን ኢዜማ አባላት እና ደጋፊዎች በያሉበት ይህንኑ የምዕራባውያን ፖለቲካዊ ጣልቃ ገብነት ለማውገዝ በተጠሩ ሕዝባዊ ሠልፎች ላይ በንቃት እንዲሳተፉ ከወዲሁ ጥሪውን ያቀርባል፡፡

የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ)
ጥቅምት 11 2015 ዓ.ም.

Exit mobile version