Site icon ETHIO12.COM

ለአሸባሪው ትህነግ ተጨማሪ እድል መስጠት …

ለአሸባሪው ትህነግ ተጨማሪ እድል መስጠት የቡድኑን ህልውና በማስቀጠል በትግራይ ሕዝብ ላይ ተጨማሪ የመከራ ዓመታትን መጨመር በመሆኑ የቡድኑ ህልውና እንዲያበቃ ማድረግ ይገባል ሲሉ አቶ ምዑዝ ገብረህይወት ተናገሩ።

የሠላም አምባሳደር፣ የሰብዓዊ መብትና የመልካም አስተዳደር ተሟጋች የሆኑት አቶ ምዑዝ ገብረህይወት ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለጹት፤ አንዳንድ ምዕራባውያን ለራሳቸው ጥቅም ሲሉ ለትግራይ ሕዝብ ተቆርቋሪ መስለው ይታያሉ። ነገር ግን ትግራይ ነፃ የሚሆነው ከአሸባሪው ሕወሓት ነጻ ሲወጣ በመሆኑ ለዚህ ትልቁን ሃላፊነት መውሰድ ያለበት ራሱ የትግራይ ሕዝብ እና የፌዴራል መንግሥቱ ነው ብለዋል።

በኢትዮጵያ አሻንጉሊት የሆነ መንግሥት እንዲፈጠር ፍላጎት ያላቸው አንዳንድ የውጭ አካላት የአገርን ሉዓላዊነት ከሚንድ ተግባር መቆጠብ እንዳለባቸውም አቶ ምዑዝ ገልጸዋል።

አቶ ምዑዝ እንደገለጹት፤ እንደ አንድ ሉዓላዊት አገር የትግራይ ሕዝብ ነጻነት የሚረጋገጠው በኢትዮጵያ መንግሥት እንጂ በሌላ በማንም አይደለም።

ኢትዮጵያን ማተራመስ የሚፈልጉ የውጭ አካላት አሁንም የሽብር ቡድኑን በመደገፍ ጩኸት እያሰሙ እንዳለ የገለጹት አቶ ምዑዝ፤ ይህ የአገርን ሉዓላዊነት የሚያፈርስና ተቀባይነት የሌለው አካሄድ እንደሆነ ተናግረዋል። ኢትዮጵያ ራሷን የቻለች ሉላዊት አገር እንጂ በባዕዳን ፍላጎት ላይ ተመስርታ የምትመራ አይደለችም ነው ያሉት።

አቶ ምዑዝ አገሪቷ ሕጋዊ በሆነ መንገድ በተመረጠ መንግሥት እየተመራች እንዳለች ጠቅሰው፤ የአገሪቷ አንድ አካል የሆነችው ትግራይም ነጻነቷ የሚረጋገጠው በመንግሥት ብቻ እንደሆነ ጠቁመዋል። ይህንን የሚገዳደር የውጭ ሃይል ፍላጎት የአንድን አገር ሉዓላዊ ክብር የሚጻረር እንደሆነ አመላክተዋል።

የሽብር ቡድኑ ኃይሎች ባደረጉት ወረራ ሰው ሲያርዱ፣ አዛውንት ሲደፍሩ፣ የንጹሃንን ንብረት አውድመው ሲያፈናቅሉ፣ ለሕዝቡ የሚላከውን ሰብዓዊ እርዳታ ለተዋጊ ሃይላቸው ሲያውሉት፣ የትግራይን ሕዝብ አስገድደው እንዲወጋ ሲያደርጉ፣ የጭካኔ በትራቸውን ነጻ እናወጣሃለን ባሉት የትግራይ ህዝብ ላይ ሲያሳርፉ ዝምታን በመምረጥ፤ የሽብር ቡድኑ ሽንፈት እንደሚደርስበት ሲያውቁ ማዕቀብ ለመጣል የሚሯሯጡ አካላት ቀጠናውን በማተራመስ ፍላጎታቸውን ለማሳካት እንደሆነ አቶ ምዑዝ ተናግረዋል።

ምንም እንኳን ለሠላም ሰላማዊ ውይይት ወሳኝ ቢሆንም አሸባሪው ሕወሓት ግን በታሪኩ ሰላም ወዳድ ቡድን ባለመሆኑ የመንግሥት ራሱን የመከላከል እርምጃ ተጠናክሮ መቀጠል አለበት ብለዋል። “ትግራይ የኢትዮጵያ አካል እንደመሆኗ ለችግሮቿ ደራሽ ኢትዮጵያውያን ናቸው። በትግራይ ጉዳይ የሚያገባውም የኢትዮጵያ መንግሥት ነው” ሲሉ ገልጸዋል።

የሽብር ቡድኑ በሰማይም ሆነ በየብስ ሲላክ የነበረውን እርዳታ ከድሃው ጉሮሮ እየነጠቀ ለተዋጊዎቹ ቀለብ ሲያውል እንደነበር በመግለጽ፤ ይህንን ግፍ ሕዝቡ መቼውንም የማይረሳው እንደሆነ ጠቅሰዋል። በአሁኑ ወቅት የኢትዮጵያ መንግሥት ለሕዝቡ የተሳለጠ እርዳታ እንዲደርስ ምቹ ሁኔታ መፍጠሩ የሚደነቅ መሆኑንም ጠቁመዋል። ለቡድኑ ተጨማሪ እድል መስጠት ሌላ 50 የመከራ ዓመታትን መጨመር በመሆኑ፤ ሕዝቡ ሠራዊቱን በመደገፍ የሽብር ቡድኑ እስከመጨረሻ ተፋልሞ ከመንግሥት ጋር በመሆን ነጻነቱን ማረጋገጥ ይኖርበታል ሲሉም አቶ ምዑዝ አስገንዝበዋል።

መከላከያ ሠራዊቱ የሚወነጀል ሳይሆን ከራሱ ኮቾሮ ላይ እየቀነሰ በመስጠት ለዜጎቹ አለኝታ እንደሆነ በደረሰባቸው አካባቢዎች እያሳየ ያለው የበጎነት ሥራው ህያው ምስክር መሆኑም ተናግረዋል።

አዲሱ ገረመው

አዲስ ዘመን ጥቅምት 12 ቀን 2015 ዓ.ም

Exit mobile version