Site icon ETHIO12.COM

ሕዝብ “በአገሬ ቀልድ የለም ቤቴን አትንኩ” አለ

በሚሊዮኖች የሚቆጠር የአዲስ አበባና በሁሉም የአገሬው ህዝብ በዛሬው እለት ከጫፍ ጫፍ በመነሳት “ከኢትዮጵያ መንግስት ጎን እቆማለሁ ድምፄንም አሰማለሁ” በሚል መሪ ቃል ደማቅ ህዝባዊ ሰልፍ ማድረጉን ዓለም አይቷል። ይህ ወዶና ፈቅዶ ” ግፍ ሰለቸን፣ የውክልና ጦርነት በቃን” ያለ ሕዝብ ለዓለም ብቻ ሳይሆን ለመንግስትም፣ ለመንግስት ተቃዋሚምም፣ ለተላላኪውም፣ በውጭ አገር ሆኖ ለሚጮኸው ጸረ ኢትዮጵያዊ ሁሉ ነው። “በአገሬ ቀልድ የለም። ቤቴን አትንኩ” ብሏል።

ህዝቡ በዚህ ሰልፍ መልእክቱን እጅግ ጉልህና ግልፅ በሆነ መንገድ ለመላው አለም በማስተላለፍ፤ ሰላማዊ በሆነ መንገድ መጠናቀቁን ከየአካባቢው አስተዳደር መረጃ ተሰጥቷል። ሕዝብ ፈቅዶ “ኢትዮጵያ ወይም ሞት ብሏል” ጽንፈኞች አደብ በመግዛት ወደ ሰላማዊ መንገድ ተመልሱ። ከጽንፈኞች እናተርፋለን ብላችሁ የምትደክሙ ይህን አይታችሁ ከራሳችሁ ጋር ታረቁ። ይህ ሕዝብ ታጋሽ፣ አስተዋይ፣ አብሮነትን የሚያከብር የመሆኑንን ያህል፣ የዛሬ መልዕክቱ እጥፍ ነው። “ካሁን በሁዋላ አትውጉን፣ አታስወጉን፣ አትንኩን በቃ” ነው ያለው። ማርም ሲበዛ ይመራል አይነት።

ለገዢው ፓርቲም ” አሁን አብሬህ ቆሜያለሁ” ሲል ያንተ ፍቅር አንቀጥቅጦት ሳይሆን የእምዬ ኢትዮጵያ ጉዳይ ነውና አቋምህን አስተካከል። በየስርቻው ተቧድነው በውክልና የሚዘርፉ ሌቦችን መንጥር፣ በባለስልጣናት ስም የሚነገዱ መጋዣዎችን አጥራ። ገንዘብ የሚከሰከስላቸውን ወዳጅ መሳይ ሌቦች አባር። መልካምና የጸዳ አገልግሎት አዳርስ፣ ቀበኞችህን ሰብስበህ ለፍርድ አቅርብ። አለያ ይህ ህዝብ እንደዛሬው ወጥቶ ይዘርርሃል።

በአዲስ አበባ አስተዳደር ይህ መግለጫ ወጥቷል””

የአስተዳደሩ መግለጫ እንደሚከተለው ቀርቧል፦

ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ዛሬ የተካሄደውን ሰላማዊ ሰልፍ አስመልክቶ የተሰጠ ጋዜጣዊ መግለጫ!!

በሚሊዮኖች የሚቆጠር የአዲስ አበባ ህዝብ በዛሬው እለት ከጫፍ ጫፍ በመነሳት ‹‹ከኢትዮጵያ ጎን እቆማለሁ ፤ ድምፄንም አሰማለሁ›› በሚል መሪ ቃል ባካሄደው ሰላማዊ ሰልፍ ደማቅና በሆነ መንገድ ተካሂዶ መልእክቱን እጅግ ጉልህና ግልፅ በሆነ መንገድ ለመላው አለም በማስተላለፍ፤ ሰላማዊ በሆነ መንገድ ተጠናቋል፡፡

እኛ ኢትዮጵያውያን በእርግጥም ሰላም ወዳድ ህዝቦች ነን፡፡ ሰላም ወዳድነታችንና ለሰላም ዘብ መቆማችን በተደጋጋሚ በተግባር ያርጋገጥን ህዝቦች ነን፡፡ ነገር ግን በሉአላዊነታችንና በግዛት አንድነታችን ከመጡብን ደግሞ በአብሮነት እና በህብረት ቆመን ሃገራችንን የምንከላከል ፤ ለሃገራችን አስፈላጊውን ሁሉ መስዋእትነት የምንከፍል ፤ ኢትዮጵያን በውድ የደምና የአጥንት ዋጋ ያሸጋገርን ወደፊትም የምናሸጋገር ፅኑዕ እና ሃገር ወዳድ ህዝቦችም ጭምር ነን፡፡

ዛሬም ይህ ሀገር ወዳድነት በከተማችን መስቀል አደባባይ ተረጋግጧል፡፡ ከፍተኛ ቁጥር ያለው የከተማችን ነዋሪ የሀገሬ ጉዳይ ይመለከተኛል፤ በማለት ከየአቅጣጫው በመጉረፍ የፖለቲካ አመለካከት ብሄር፤ እምነት ልዩነት ሳይኖር በአንድነት እጅ ለእጅ በመያያዝ ድምፁን ከፍ አድርጎ በማሰማት ህዝባችን ሰላማዊና ሃገር ወዳድ መሆኑን ለጠላትም ለወዳጅም በማያወላዳ መልኩ ማሳየት ችሏል፡፡

የከተማችን ነዋሪዎች በነቂስ በተሳተፉበት በዚህ ፍፁም ሰላማዊ በሆነና ኢትዮጵያዊ ጨዋነት ጎልቶ በታየበት የሰላማዊ ሰልፍ ወጣቶች ሴቶች ጎልማሶች ፤ እናቶችና አባቶች፤ አካል ጉዳተኞች ፤መምህራን ፤ ተማሪዎች የመንግስት ሰራተኞች ፤የግል ድርጅት ሰራተኞች አርቲስቶችና ታዋቂ ሰዎች የሃይማኖት አባቶች እንዲሁም አባት አርበኞች በአጠቃላይ ከሁሉም አይነት የህብረተሰብ ክፍል የተውጣጡ የከተማችን ነዋሪዎች ገና ከሌሊት ጀምሮ በነቂስ በድቅድቅ ጨለማ ገንፍሎ በወጣ ሃገር ፍቅር ስሜት በመውጣት በየመንገዱ ድምፃቸውን እያሰሙ ፍፁም ሰላማዊ በሆነ መንገድ መልእክታቸው አስተላልፈው ወደየመጡበት በሰላም ተመልሰዋል፡፡

ለዚህም መላውን ሰላም ወዳድና የሰላም አምድ የሆነው የከተማችንን ነዋሪ ፤የፀጥታ ሃይል እንዲሁም ይህ ሰልፉ የተሳካ እንዲሆን ያስተባበራችሁና ያቀናጃችሁ የሲቪክ ማህበራትና የፖለቲካ ፓርቲዎች አመራሮችና አባላት በተጨማሪም በየደረጃው የምትገኙ አመራሮች የከተማ አስተዳደራችን ስላበረከታችሁት ታላቅ አስተዋፅኦ ምስጋናውን ያቀርባል፡፡

አሁንም ቢሆን የጀመርነውን ሃገራችንን ከጠላት የመጠበቅ እንቅስቃሴ አጠናክረን በመቀጠል፤ ለመካላከያ ሰራዊታችንን አስፈላጊውን ድጋፍ ማድረጋችንን እንድንቀጥል እያሳሰብን ፤ በየአካባቢው ሰላማችንን ለማደፍረስ የሚንቀሳቀሱ የውጪና የሃገር ውስጥ ጠላቶቻችን ቅጥረኞችን ከፀጥታ ሃይሉ ጋር በመተባበር በመከላከልና አጋልጠን በመስጠት ዘላቂ ሰላማችንን እናድናረጋግጥ አደራ ለማለት እንወዳለን፡፡

በመጨረሻም የጀመርነው የሃገራችንን ብልፅግና እውን የሚያደርጉ እንቅስቃሴዎች በማስቀጠል ዋነኛው የሉአላዊነት ምንጭ ራስን በመቻል ከጥገኝነት በመላቀቅ የሃገርን ብልፅግና ማረጋገጥ በመሆኑ እጅ ለእጅ ተያይዘን በደም ተገነባችዋን ሃገራችንን በላባችን ከፍ በማድረግ የኢትዮጵን ብሎም የከተማችንን ብልፅግና እውን እንድናደርግ ጥሪያችንን እናቀርባለን!!

ኢትዮጵያ በልጆቿ አብሮነትና ህብረት ታፍራና ተከብራ ትኖራለች!!

ጥቅምት 12 2015 ዓ.ም

አዲስ አበባ

Exit mobile version