Site icon ETHIO12.COM

“ከሩቁ የሚፈራ የመከላከያ ሠራዊት ፈጥረናል”

የመከላከያ ሠራዊት ቀንን ምክንያት በማድረግ የተዘጋጀ “የጥንካሪያችን ምንጭ ሕዝባችን ነው” በሚል መልዕክት የፓናል ውይይት ተካሄደ።

በመርሃ ግብሩ ላይ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የመከላከያ ሚኒስቴር ሚኒስትር አብርሐም በላይ (ዶክተር)፣ አሁን በኢትዮጵያ የመከላከያ ሠራዊት ግንባታ ከፍተኛ አቅም ተፈጥሯል፤ ከሩቁ የሚፈራ መከላከያ ሠራዊት ፈጥረናል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ጠላቶች ሳንቆም ሊጥሉን ሞክረዋል፤ አሁን ቆመን ማንም ሊነቀንቀን የማይችልበት ደረጃ ደርሰናል ያሉት ሚኒስትሩ፣ በአሁኑ ጊዜ ሳይዋጋ የሚያሸንፍ ሠራዊት መገንባት መቻሉን አንስተዋል።

ኢትዮጵያ የግዛት አንድነቷ በማንም እንደማይሸረፍ በመስዋዕትነት የሚያረጋግጥ ጀግና ወታደር ያላት ሀገር እንደሆነች የገለጹት ሚኒስትሩ፣ ይህን በተግባር እያረጋገጠ የሚቀጥል መሆኑን ተናግረዋል።

የመከላከያ ቀንን በማስመልከት ከጥቅምት 14 እስከ 18 2015 ዓ.ም በመከላከያ ጠቅላይ መምሪያ የተዘጋጀ ከ1900 ጀምሮ የመከላከያ ሚኒስትሮችና ኢታማዦር ሹሞች የሚያሳይ የፎቶ አውደ ርዕይ በመከላከያ ሚኒስትሩ ተመርቆ መከፈቱ ይታወሳል።

ከዚሁ ጋር በተያያዘ የሠራዊቱ ቀን ሲከበር ለሀገር መስዋዕት የሆኑ ጀግኖችን በቋሚነት የሚያስታውስ ቋሚ ሀውልት በማቆም ሊሆን ይገባል ሲሉ የፓናሉ ተሳታፊዎች ገለፁ።

ጥቅምት 15 ቀን በብሄራዊ ደረጃ የሚከበረውን የሰራዊት ቀን በማስመልከት በተደረገው የፓናል ውይይት ላይ የተሳተፉ የቀድሞ ከፍተኛ የጦር መኮንኖች ፤ አባት አርበኞች እና ምሁራን በየዘመኑ ለሀገራቸው ህልውና ለተሰው ጀግኖች ማስታወሻ የሚሆን ቋሚ ሀውልት ሊቆምላቸው እንደሚገባ ገልፀዋል።

በተለያዩ ሀገራት የሰራዊቱን ቀን በተለያየ መልኩ እንደሚከበር የገለፁት ተሳታፊዎቹ ጀግኖችን በቋሚነት የሚያስታውስ ያልታወቀው ጀግና የሚል ሀውልት በማቆም ለትውልድ ማስተማሪያነት መጠቀም እንደሚገባም ገልፀዋል።

የመከላከያ ስነልቦና ግንባታ ዋና ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ሜ/ጀኔራል እንዳልካቸው ወልደኪዳን ፤ ያልተዘመረላቸው ጀግኖችን ማክበሩ ለቀጣይ ትውልድም አስተማሪ መሆኑን ጠቅሰው ተሳታፊዎችም በቀጣይ የበኩላቸውን እንዲወጡ ጠይቀዋል። (የኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት)

(ኢ.ፕ.ድ)

Exit mobile version