Site icon ETHIO12.COM

መንግስት በጫና አልንበረከክም አለ – ጫና ከሚፈጥሩት አገራቱ ጋር ያለውን ግኝኙነት እንደሚፈትሽ ይፋ አደረገ

ያልተረጋገጡና ፖለቲካዊ ዓላማ ያላቸውን ውንጀላዎች ከሚያቀርቡ ከአንዳንድ ሀገሮችና ተቋማት ጋር ያለውን ግንኙነት የኢትዮጵያ መንግሥት መልሶ ለማጤን እንደሚገደድ አስታወቀ። “ኃላፊነት የጎደላቸው አካላት ለአደገኛ የፖለቲካ አጀንዳ ሲባል እየፈጠሯቸው የሚገኙ መሠረተ ቢስ ውንጀላዎችን ኢትዮጵያ ታወግዛለች” ሲል የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት መግለጫ አውጥቷል።

ከኢፌዴሪ የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት የተሰጠው መግለጫ በግልጽ ለትህነግ ያደላ የማስገደድ ዘመቻ እየተካሄደ መሆኑንን አመልክቷል። ድርጊቱንም “በቀቀን” ሲል የትህነግን ወሬ በመልቀም ሳያጣሩ እንደሚደጉት በስም ሳይጠራ በደፈናው አውግዟል።

ድርድሩ በኢትዮጵያና በአሜሪካ መካከል እንጂ ከትህነግ ጋር እንዳልሆነ በደቡብ አፍሪካ የሚደረገውን ንግግር አስመልክቶ አሜሪካ በየሰዓቱ ከምትሰተው መግለጫና መረጃ ለመረዳት ተችሏል። በተመድ የአሜሪካ አምባሳደር ሊንዳ ቶማስ “ለስምምነት የማይቀበሉት ላይ እርምጃ እንወስዳለን” ሲሉም አሜሪካ ያዘጋጀችው የስምምነት ፕሮፖዛል እንዳለ አሳብቀዋል።

አሜሪካ በታዛቢነት ሳይሆን በተሳታፊነት የገባችበት የሰላም አማራጭ ንግግር የኢትዮጵያ መንግስት ምን እንዲያደርግ በቀጥታ ጫና እንደሚደረግበት ባይገልጽም ትህነግን ነብስ ዘርቶ ለማስቀጠል ያለመ ጫና እንደሆነ ከየአቅጣጫው እየተገለጸ ነው።

የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ከወትሮው በተለየ አክርሮ የተቃወመው ጣልቃ ገብነት ” ሲያምራችሁ ይቅር” ዓይነት ምላሽ የሰጠ ሆኗል። የመንግስት አቋም ከአገራቱ ወይም ከተቋማቱ ጋር ያለውን ግንኙነት ለማጤን የሚገደድበት እንደሆነም አመልክቷል።

ገንኙነትን ማጤን ማለት የዲፕሎማሲ ግንኙነትን መቀነስ፣ ማቋረጥ፣ ኤምባሲውዎች የሰው ሃይላቸውን እንዲቀነሱ ማድርገ የመሳሰሉትን እንደሚያካትት የዓለም ልምድ ያሳያል።

በኢትዮጵያ ላይ እንዲህ ያለ ዘመቻ የተከፈተው አሁን ያለው መንግስት አድርግ የተባለውን ሁሉ የማያደርግና ተላላኪ ሊሆን ባለመቻሉ እንደሆነ የመንግስት ከፍተኛ አመራሮች በተላየዩ ወቅቶች አስታውቀዋል።

የመግለጫው ሙሉ ቃል ከስር ያለው ነው።

በምዕራባውያን የተለያዩ አካላት አማካኝነት በኢትዮጵያ ላይ የሚነዙ የሐሰት ስም ማጥፋቶችን የኢትዮጵያ መንግሥት ፈጽሞ አይታገሥም። እነዚህ አካላት ኢትዮጵያ ውስጥ የከፉ ወንጀሎች ሊፈጸሙ ይችላሉ በሚል የሕወሐትን ጊዜ ያለፈበት ፕሮፓጋንዳ እንደ በቀቀን መድገማቸው አሳፋሪ ነው። እነዚህ አካላት የሚከሱት ፍንጮችን ወይም ተጨባጭ ክስተቶችን መሠረት አድርገው አይደለም፤ የመፈጸም ዕድል አለ በሚል ያልተጨበጠ ግምት እንጂ።

እጅግ የሚያሳዝነው ደግሞ የተሻለ ስም ያላቸው ተቋማት ሳይቀሩ ይሄንን በኢትዮጵያ ላይ ተቀነባብሮ የሚለቀቅ ፕሮፓጋንዳ ለመቃወም አለመቻላቸው ነው። ጥቂቶቹም ስለ ኢትዮጵያ የተነገረውን ስም ማጥፋት በማመን ሳይሞኙ እንዳልቀሩ ይገመታል።

አንዳንዶችም እነዚህን የሐሰት ክሶች ኢትዮጽያን ለማንበርከክ ሊጠቀሙባቸው ይፈልጋሉ። ይሄን መሰል አስደንጋጭ ክሶችን አቅርቦ የኢትዮጵያ መንግሥትን በማስጨነቅ በሕወሐት ላይ እየወሰደ ያለውን የመከላከል ርምጃ ለማስቀየስ የሚችሉ መስሏቸው ከሆነ ተሳስተዋል።

አንዳንዶችም የሚችሉትን ሁሉ በማድረግ ይህንን ቡድን ለማዳን እየተረባረቡ ነው። አንዳንድ ምዕራባውያን ባለ ሥልጣናት ጭምር ይሄንን የሐሰት ክስ የሚነዙት ኢትዮጵያ ትእዛዛቸውን አልቀበል ስላለቻቸው መሆኑን በይፋ መናገር ጀምረዋል።

ይህ ጊዜ አመጣሽ የሐሰት ክስ መሬት ላይ ያለውን እውነታ ጨርሶ አይቀይረውም። እነዚህ ጉምቱ ተቋማትና ወሳኝ ተዋንያን፣ በቂ ግንዛቤ ሳይኖራቸው በዚህ የሃሰት ዘመቻ እየተሳተፉ ይገኛሉ። ይሄን የመሰሉ የከፉና ሊወገዙ የሚገባቸው ውንጀላዎች ለፖለቲካ ዓላማ መዋላቸው ኃላፊነት የጎደለውና አሳፋሪ ነው።

ይሄንን ለመሰለው አደገኛ ስም ማጥፋት ምላሽ ሳይሰጡ ታግሦ ማለፍ የሚቻል ባለመሆኑ በከፋ መልኩ በኢትዮጵያ ላይ ያልተረጋገጡና ፖለቲካዊ ዓላማ ያላቸውን ውንጀላዎች ከሚያቀርቡ ከአንዳንድ ሀገሮችና ተቋማት ጋር ያለውን ግንኙነት የኢትዮጵያ መንግሥት መልሶ እንዲያጤን ተገድዷል።

የኢትዮጵያ መንግሥት ከመነሻውም በግልፅ እንዳሳወቀው በአፍሪካ ኅብረት በኩል እየተደረገ ላለው የሰላም ንግግር ቁርጠኛ ነው። ምክንያቱም ግጭቱን በሰላማዊና ቋሚ በሆነ መንገድ ለመፍታት የጸና አቋም አለውና። በሌላም በኩል በግጭቱ ምክንያት የተከሠቱ የሰብአዊ መብትና የሰብአዊነት ጥሰቶችን ተጠያቂ ለማድረግ ቁርጠኛ መሆኑን ለመግለጥ ይወዳል፡፡

ጥቅምት 18 ቀን 2015 ዓ.ም

አዲስ አበባ

የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት

Exit mobile version