“በትግራይ ሰላም ሳይኖር፤ በኢትዮጵያ ሰላም ሊኖር አይችልም” ትህነግ
ቢቢሲ ለቅስቀሳ ያወጣው አጭር ቪዲዮ ሲያዩት ይፈታተናል። ትግራይ ድሮም እንዲሉ ምስኪኖች ተጎድተዋል። ይህ ሁሉ የህዝብ ስቃይ ለምንንና ለማን እንዲሆም ለምስኪኑ ሕዝብ ምን ለማስገኘት ነው? የሚል ጥያቄ ቢቀርብ ምላሽ የለም። በትግራይ ሰላማዊና ምስኪን ዜጎች አፋጣኝ ደራሽ ያስፈልጋቸዋል። ካድሬ ትግራይን በፕሮፓጋንዳ ቀርቅሮ እየገደላት ነው። ህዝቡ በዚህ መልክ እያለ ነው አንዱ አልበቃ ብሎ አራተኛ ጦርነት የተመረጠው።
ለዚህ ይመላል መንግስት ትግራይን እንደሚቆጣጠር ይፋ አድርጓል። በህገ መንግስቱ መሰረት የፌደራል ተቋሞችን እንደሚያስተዳድር ድርድር በሌለው መልኩ አስቀምጧል። መቀለ በተከበበችበት በዚ ወቅት ትህነግ የተኩስ አቁሙን እንደሚቀበል አመልክቷል። ውሳኔው የዘገየ በጎ ውሳኔ ቢሆንም መንግስት ” ያለ ቅድመ ሁኔታ” የሚለውን አሳብ እንደማይቀይር ገልጿል። በሌላ አገላልጽ ካሁን በሁዋላ ትህነግ ነጻ ክልል አይኖረውም እንደማለት ነው። ለዚህ ደግሞ ምክንያቱ አለመታመኑ እንደሆነ መከላከያ ከታረደበት ጊዘ አንስቶ በተከታታይ የተደረጉትን ወረራዎች ማስረጃ አድርጎ ጠቅሷል።
“አሁንም” ይላል ዛሬ ይፋ የሆነው የመንግስት ኮሙኒከሽን መግለጫ “አሁንም ትህነግ የሚያወጣቸው መግለጫዎች ሌላ ጦርነት ናፋቂ መሆኑንን ያሳያሉ” የአገሪቱን ሉዓላዊነት ለማስጠበቅና በትግራይ ክልል የሚገኙ ዜጎችን ሰላም ለማስጠበቅ መንግስት በህገመንግስቱ በተሰጠው ሃላፊነት መሰረት ተግባሩን እንደሚወጣ ቃል በመግባት ትግራይን እንደሚቆጣጠርና የፌደራል ተቋማትን በሌሎች ክልሎች እንደሚደረገው ሁሉ እንደሚቆጣጠር ይፋ አድርጓል።
በ24 ጦርነቱን ትህነግ እንደጀመረ አሜሪካ በይፋ ጠቃሳ በብሊንከን ጽህፈት ቤት በኩል “ትንኮሳ አቁሙ” በሚል መግለጫ ካወጣች በሁዋላ፣ መንግስት ጦርነቱን አስመልክቶ አቋሙን ይፋ ባደረገበት መግለጫው “ትህነግ ከሚደግፉት ጋር ሆኖ የአገሪቱን ሉዓላዊ የአየር ክልል አስጥሷል” ሲል ከሶ ሳይወድ እርምጃ ለመውሰድ መገደዱንም ይፋ አድርጓል። በተዛዋዋሪ በርካታ የትግራይ አካባቢዎች በመንግስት እጅ መውደቃቸውንም አስታውቋል።
ሕዝቡና የእርዳታ ሠራተኞች ራሳቸውን ከሕወሓት ወታደራዊ ተቋማት እንዲያርቁ የሚያሳስበው የመንግስት መግለጫ አሌክስ ድዋል በሚደርስበት ጥቃት የትህነግ ሰራዊት መፍረሱንና ወደ ዜሮ ደረጃ መውረዱን ካስታወቀ በሁዋላ መንግስት በይፋ ትግራይን በመቆጣጠር ልክ እንደ ማንኛውም ክልል እንድትተዳደር መወሰኑ የግንባር ድሉን ያሳየ ሆኗል። ትህነግ ግን ትናንት ባወጣው መግለጫ ላይ ” “በትግራይ ሰላም ሳይኖር፤ በኢትዮጵያ ሰላም ሊኖር አይችልም”
“በትግራይ ሰላም ሳይኖር፤ በኢትዮጵያ ሰላም ሊኖር አይችልም”
ህወሓት ትናንት ባወጣው መግለጫ መስከረም 1/2015 ላይ ግጭት ለማቆም ያወጣነውን መግለጫ የአፍሪካ ኅብረት፣ የተባበሩት መንግሥታት፣ የአውሮፓ ኅብረት ጨምሮ ሌሎች አካላት በበጎ ቢቀበሉትም ግጭቱን ለማቆም ግን አንዳችም ተግባራዊ እርምጃ አልተወሰደም ብሏል።
ዓለም አቀፉ ማሕብረሰብ ግጭቱ በአስቸኳይ እንዲቆም ማረጋገጥ አልያም የትግራይ ሕዝብ እራሱን እንዲከላከል የመርዳት አማራጮች አሉት ያለው የህወሓት መግለጫ፤ ሁለቱም አማራጮች የማይወሰዱ ከሆነ፤ “የትግራይ ሕዝብ ሕልውናውን ለማረጋገጥ ትግሉን ይቀጥላል . . . በትግራይ ሰላም ሳይኖር፤ በኢትዮጵያ ሰላም ሊኖር አይችልም” ሲል ገልጿል።
በመግለጫው ማጠቃለያ ላይ ዓለም አቀፉ ማሕብረሰብ የኤርትራ ጦር ከትግራይ እንዲወጣ ጫና እንዲያሳድር፣ ግጭት እንዲቆም ተግባራዊ እርምጃዎችን እንዲወስድ እና የኢትዮጵያ መንግሥት ወደ ድርድር ጠረጴዛ እንዲመጣ ጫና እንዲያሳድር ጠይቀዋል ቢቢሲ ካስፈረው ።
ሁሉም የመከላከያ አውዶችና ምዕራፎች በከፍተኛ ዲሲፒሊን የታዘዙትን ብቻ እንዲያደርጉ እየተሰራ መሆኑንን ያስታወቀው ይህ መግለጫ ትህነግ የአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን ኮሚሽነር ሙሳ ፋኪ መሐመት በድጋሚ የተኩስ አቁም እንዲደረግ ያወጡትን መግለጫ በበጎ ጎኑ እናየዋለን በሚል መግለጫ ካወጣ በሁዋላ ነው። በተዘዋዋሪ መንግስት ትህነግ የተሰጠውን በርካታ እድሎች ያበላሸና አሁንም ቢመቸው ሌላ ጦርነት ትንፋሽ ወስዶ እንደሚጀምር አመልክቷል። አንደማይታመንም ገልጿል። ይሁን እንጂ የኢትዮጵያን ሉዓዊነት እያስከበረ ለሰላም ንግግር በሩን እንደማይዘጋ አመልክቷል።
አቶ ሬድዋን ትህነግ ሲያጠቃና ወደፊት ሲገሰግስ ዝም ይሉና ትህነግ ሲመታና የሚሸነፍ ሲመስላቸው ሁሉም ጫጫታ እንደሚጀምሩ ማስታወቃቸው ይታወሳል። በዚሁ መንፈስ ይመስላል የአሜሪካ፣ አውሮፓና የተባበቱት መንግስታት ባለስልጣኖች “አሳስቦናል” ሲሉ ጫና ለመፍጠር ሰፊ ዘመቻ ጀምረዋል። ዘመቻው ሰፊ ቢሆንም መንግስት ጉዳዩ የሉዓላዊነት ማስከበር ነው ሲል ህገመንግስት አጣቅሶ ለጫጫታው ምላሽ ሰጥቷል።
ዛሬ ላይ እንደሚሰሙት ከሆነ መቀለ ተከባለች። ህዝብ ከትህነግ የወታደራዊ እንቅስቃሴ አካባቢዎችና ጦር ካምፖች ራሱን እንዲያርቅ መንግስት በዓይር ወረቀት በመበተን ቅስቀሳ እያደረግ መሆኑ እየተሰማ ነው። መንግስት አማጺና ህገወጥ የሚለው የትህነግ ሰራዊት ዳግም የመደራጀት ዕድል ሊኖረው እንደማይችል መረጃዎች እየወጡ ነው።
በሰሜን ኢትዮጵያ የሚካሄደውን የመከላከል ርምጃን በተመለከተ የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት መግለጫ አውጥቷል
የመግለጫው ሙሉ ቃል እንደሚከተለው ቀርቧል፡-
በሰሜን ኢትዮጵያ የሚካሄደውን የመከላከል ርምጃ በተመለከተ የተሰጠ መግለጫ
በአሁኑ ወቅት በሰሜን ኢትዮጵያ የተፈጠረው ግጭት፤ ትህነግ ነሐሴ 18 ቀን 2014 ዓ.ም በሙሉ አቅሙ የከፈተውን ጥቃት ተከትሎ የመጣ መሆኑን ማስታወስ ተገቢ ነው።
ይህም የኢትዮጵያ መንግሥት በሚያዝያ ወር ያወጀውን በሰብአዊነት ላይ የተመሠረተ የተኩስ አቁም የጣሰ ነው። የመንግሥት ጥረት ምንም ዋጋ ስላልተሰጠው፣ ትህነግ በሁለት ዓመት ውስጥ ሀገሪቱን ለሦስተኛ ጊዜ ወደ ግጭት አስገብቷታል።
ትህነግ ሦስተኛውን ግጭት የከፈተው በአፍሪካ ኅብረት በኩል በሚደረገው የሰላም ንግግር፣ ያለ ቅድመ ሁኔታ በየትኛውም ጊዜና ቦታ ላይ ለመነጋገር የኢትዮጵያ መንግሥት ዝግጅነቱን ከገለጠ ከጥቂት ጊዜያት በኋላ ነው። ከዚህም በተጨማሪ ለልዩ መልእክተኞችና መቀመጫቸውን በአዲስ አበባ ላደረጉ ዲፕሎማቶች ጥቃት ለመሠንዘር ሕወሐት ያለውን ዝግጁነት አመልክቶ ነበር።
ትህነግ ለተለያዩ ዓለም አቀፍ አካላት በበተነው ደብዳቤ ላይ ይሄንን ጥቃት የመክፈት ፍላጎቱን በግልጽ አመልክቷል። በመሆኑም አሁን ለተፈጠረው ችግር ሁሉ ብቸኛ ተጠያቂው ትህነግ መሆኑ የተረጋገጠ ነው። ጊዜና ቦታ ከተሰጠውም ሌላ ዙር ግጭት እንደሚፈጥር ከሰሞኑ መግለጫዎቹ ለመረዳት ይቻላል።
ትህነግ በሙሉ ዐቅሙ ጥቃት ከመክፈቱ በፊት የኢትዮጵያን የአየር ክልል ደጋፊዎቹ በሆኑ የኢትዮጵያ የውጭ ጠላቶች ሲያስደፍር ቆይቷል። በዚህም የተነሣ የኢትዮጵያ መንግሥት የሀገሪቱን ሉዓላዊነትና የግዛት አንድነት የመጠበቅ ግዴታውን እንዲወጣ አስገድዶታል።
የኢትዮጵያ መንግሥት የሚወስዳቸውርምጃዎች የግድ አስፈላጊ የሆኑት በትህነግ ተደጋጋሚ ጥቃት የተነሣ ብቻ ሳይሆን ከሀገሪቱ ታሪካዊ ጠላቶች ጋር ተቀናጅቶ በሚፈጽማቸው ተግባራት ምክንያትም ጭምር ነው።
ስለሆነም የሀገሪቱን ሉዓላዊነትና የግዛት አንድነት ለማስከበር የኢትዮጵያ መንግሥት የአውሮፕላን ማረፊያዎችን፣ የፌዴራል ተቋማትንና ታላላቅ መሠረተ ልማቶችን የግድ መጠበቅ አለበት ማለት ነው። ይህም የሀገሪቱን ሉዓላዊነትና የግዛት አንድነት በተለይም የአየር ክልልን በሚገባ ከማስከበር አንጻር መጠበቅን የግድ አድርጎታል።
እነዚህ ተግባራት መፈጸሙ መንግሥት ሰብአዊ ርዳታን ለተረጂዎች በተገቢው ሁኔታ እንዲያሣልጥ የሚረዳው ይሆናል። በአንድ በኩል እነዚህን ዓላማዎች እያስፈጸመ በሌላ በኩል ደግሞ በአፍሪካ ኅብረት አማካኝነት ለሚካሄደው የሰላም ውይይት ዝግጁ መሆኑን የኢትዮጵያ መንግሥት በድጋሚ ያረጋግጣል። ዘላቂ ሰላም እንዲመጣ ሁለንተናዊና በንግግር ላይ የተመሠረተ ስምምነት አስፈላጊ መሆኑን መንግሥት ያምናል።
የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት አግባብነት ባላቸዉ አሠራሮችና በዓለም አቀፍ የሰብአዊ ሕጎች በጽኑ የሚገዛ መሆኑን መንግሥት ግልጽ ለማድረግ ይፈልጋል። ንጹሐን እንዳይጎዱ ለመከላከል እንዲቻል የኢትዮጵያ የመከላከያ ሠራዊት ጦርነቱ በከተሞች ውስጥ እንዳይደረግ ጥንቃቄ እያደረገ ይገኛል። ይሄንን በጽኑ ለመፈጸም እንዲቻልም ለሁሉም ተዋጊ አሐዶች ጥብቅ መመሪያ ተላልፏል።
ከዚህም ባሻገር በመንግሥት ቁጥጥር ሥር በሆኑ አካባቢዎች ሰብአዊ ርዳታ በተሻለ መንገድ መቅረብ እንዲችልና የርዳታ ሠራተኞች ደኅንነት የተጠበቀ እንዲሆን መንግሥት ከርዳታ ድርጅቶች ጋር አብሮ ለመሥራት ዝግጁ ነው። ትህነግ ንጹሐንን እንደ ጦር መከላከያ የመጠቀምና ሲቪል ተቋማትን ለወታደራዊ ሠፈርነት የመጠቀም የቆየ ልማድ አለው።
ስለሆነም ሕዝቡና የርዳታ ሠራተኞች ራሳቸውን ከትህነግ ወታደራዊ ተቋማት እንዲያርቁ የኢትዮጵያ መንግሥት ጥሪ ያደርጋል። የርዳታ ሠራተኞችን ጨምሮ በሲቪሎችን ላይ ለሚደርሰው ማንኛውም ጉዳት መንግሥት ኀዘኑን በዚህ አጋጣሚ ይገልጣል። እውነቱን ለማወቅና ያልተገደበ የርዳታ ተደራሽነትን ለማረጋገጥ እንዲቻል ጉዳቶች ከተከሠቱ የሚያጣራ ይሆናል።
በመጨረሻም፣ በትግራይ ክልል የሚገኙ ዜጎቹን ደኅንነት ለመጠበቅ በሕግ የተሰጠውን ሕገ መንግሥታዊ ግዴታውን ለመወጣት የኢትዮጵያ መንግሥት ያለውን ዝግጁነት በዚሁ አጋጣሚ ያረጋግጣል።
ጥቅምት 7 ቀን 2015 ዓ.ም
አዲስ አበባ
የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት