Site icon ETHIO12.COM

“አንድ ነገር ላረጋግጥልዎት እፈልጋለሁ፤ የውስጣችን መንፈስ ጽኑእ ነው”ለታሪክ የሚቀር

አምባሳደር ታዬ አጽቀሥላሴ ሐሙስ ጥቅምት 17 ቀን 2015 ዓ.ም. በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ ለመነጋገር በተጠራው 77ኛው የተባበሩት መንግሥታት ስብሰባ ላይ ለቀረበብን የሀሰት ውንጀላ በተፈቀደላቸው 2 ደቂቃ የሚከተለውን ልብ የሚሞላ ምላሽ ሰጥተዋል።

” እየሰማን ያለነው የሰላም መልእክት አይደለም። ተከታታይ ማስጠንቀቂያዎችን ነው። ነገር ግን በርካታ የፖለቲካ ምስቅልቅሎችን ማለፍ እንደቻለች ኩሩ አፍሪካዊት ሀገር [የተባበሩት መንግሥታት] አባል ሀገራትን አንድ ነገር ማስታወስ እፈልጋለሁ። በርካታ ችግሮቻችንን ተጋፍጠን እንዳለፍናቸው ዛሬም የገጠሙንን ችግሮች በእርግጠኝነት እንሻገራቸዋለን።

በአንዳንድ ኃያላን ሀገሮች ዐይን ፊት ልክ በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት እንደሆነው [ኢትዮጵያውያን] ዐቅመቢስ መስለን እንታይ ይሆናል። ክቡር ሊቀመንበር አንድ ነገር ላረጋግጥልዎት እፈልጋለሁ። የውስጣችን መንፈስ ጽኑእ ነው። የውስጣዊ መንፈሳችን ጥንካሬ ኢትዮጵያዊ ሆኖ ለመቆም ብቻ ሳይሆን ሰላማዊ ለመሆን እና ተግዳሮቶቻችንን ለመፍታት ጭምር ነው።

የ120 ሚሊዮን ሕዝባችንን ዕድል ለ200 ኤክስፐርቶች ልንተወው አንችልም። ይህንን ብዬ፤ ሁልጊዜም ቢሆን በጎ ሀሳብ ያላቸውን ተሳታፊዎች በደስታ የምንቀበል ሲሆን ሊያወግዙን እና ለሞት አሳልፈው ሊሰጡን ቀድመው የወሰኑትን ግን “የሚያደርጉትን አያውቁምና ይቅር ይበላቸው” እላለሁ።

ስለዚህ እንደ [ኢትዮጽያ] መንግሥት ላረጋግጥላችሁ የምፈልገው ሁሉም የሰብአዊ መብት ጥሰት ላይ የተሳተፉትን ተጠያቂ እናደርጋቸዋለን። ይህንንም የምናደርገው የተወሰኑ ድርጅቶችን ወይንም ኤክስፐርቶችን ለማስደሰት ሳይሆን ለራሳችን መርኅ ስንል ነው።

ዘላቂ ሰላም መስፈን የሚችለው በሁሉም አካባቢዎች ለተሠሩ ወንጀሎች ተጠያቂነት እና ፍትህ ሲሰፍን ብቻ መሆኑን እንረዳለን። ነገር ግን ይህ በሀገሪቱ ባለቤትነት መመራት አለበት። አመሠግናለሁ ክቡር ሊቀመንበር “

Exit mobile version