ETHIO12.COM

የኤፍቢአይና የሶማሊያ የደህንነት ባለስልጣናት አዲስ አበባ ናቸው

አቶ ሲሳይ ቶላ የመረጃ ደህንነት ምክትል ዳይሬክተር ከሶማሊያ የብሄራዊ ደህንነት ዳይሬክተር ጋር ከሳምንት በፊት በሞቃዲሾ ተገናኝተው አብረው ሽብረተኛነትን ለመዋጋት ስምምነት ማድረጋቸው ይታወሳል።

የኤፍ ቢ አይ (USA,FBI) የአለም ዓቀፍ የኦፕሬሽን ዲቪዥን ምክትል ዳይሬክተር ሚስተር ሬይሞንድ ዱዳንና በሶማሊያ ብሔራዊ መረጃና ደኅንነት ኤጀንሲ ዳይሬክተር ጀነራል ማሀድ ሞሐመድ አዲስ አበባ ናቸው። ሬይሞንድ የፌደራል ፖሊስን መጎብኘታቸው ሲገለጽ የሶማሊያው የደህንነት ሃላፊም ተመሳሳይ ግብኝት እንደሚያደርጉ ከመጠቀሱ ውጪ የተባለ ነገር የለም።

“የዩኤስ ኤ፣ ኤፍ.ቢ.አይ የአለም አቀፍ ኦፕሬሽን ዲቪዥን ምክትል ዳይሬክተር በኢትዮጵያ ፌደራል ፓሊስ የስራ ጉብኝት አደረጉ” በማለት የዘገበው ኢፕድ “በሶማሊያ ብሔራዊ መረጃና ደኅንነት ኤጀንሲ ዳይሬክተር ጀነራል ማሀድ ሞሐመድ የተመራ የልዑካን ቡድን ዛሬ አዲስ አበባ መግባቱን የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት አስታውቋል” ከማለቱ ውጭ የሁለቱም አካላት አዲስ አበባ መገኘት የታሰበበት ስለመሆኑ አልገለጸም። ዜናውን የሚከታተሉ ግን ግጥምጥሞሽ እንዳልሆነ አመልካተዋል።

ኢትዮጵያና ሶማሊያ በደህነት፣ በፖሊስና በጸጥታ ጉዳይ አብረው ለመስራት ስምምነት እንደነበራቸው የገለጹ እንደሚሉት የኤፍቢአይ ባለስልጣንን እግር ተከትለው አዲስ አበባ የገቡት የሶማሊያ የድህንነት ባለስልጣን አመጣጥ ለጋራ ስራ እንደሆነ አመልካች መሆኑንን ጠቁመዋል።

ኢፕድ እንዳለው የኢትዮጵያ ፌደራል ፓሊስ ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገ/ሚካኤል ከምክትል ዳይሬክተሩ ጋር ባደረጉት ውይይት በኢትዮጵያ ፌደራል ፓሊስ ባለፉት አራት አመታት የተከናወኑ የሪፎርም ስራዎችን ገልፀውላቸዋል፡፡

የዩኤስኤ፣ ኤፍ.ቢ. አይ (USA, FBI) የአለም ዓቀፍ የኦፕሬሽን ዲቪዥን ምክትል ዳይሬክተር ሚስተር ሬይሞንድ ዱዳ በበኩላቸው ኤፍ.ቢ.አይ በድንበር ተሸጋሪ ወንጀሎች ዙሪያ ማለትም ህገወጥ የሰዎች ዝውውርን፣ ሽብርተኝነትን በመከላከል ረገድ ከኢትዮጵያ ፌደራል ፓሊስ ጋር በትብብር እየሰራ እንደሚገኝ በውይይቱ ወቅት አንስተው ትብብሩን የበለጠ አጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግረዋል፡፡

በተጨማሪም ኤፍ.ቢ.አይ ለኢትዮጵያ ፌደራል ፓሊስ በአቅም ግንባታ ዙሪያ ድጋፍ ለማድረግ እና የፎረንሲክ ዲፓርትመንቱንም በማቴሪያል ለመደገፍ ቃል ገብቷል። ሁለቱ ተቋማት በቀጣይ ግንኙነታቸውን የበለጠ አጠናክረው በሰላምና ደህንነት ዙሪያ አብረው ለመስራት ተስማምተዋል፡፡

ዜናው የሁለቱን አካላት ስምምነትና በሰላም ዙሪያ አብረው እንደሚሰሩ ካስታወቀ በሁዋላ “በሶማሊያ የመረጃና ደኅንነት ኤጀንሲ ኃላፊ የተመራ የልዑካን ቡድን አዲስ አበባ ገባ” ሲል ሌላ ዜና አስከትሏል። እንዲህ ይነበባል።

በሶማሊያ ብሔራዊ መረጃና ደኅንነት ኤጀንሲ ዳይሬክተር ጀነራል ማሀድ ሞሐመድ የተመራ የልዑካን ቡድን ዛሬ አዲስ አበባ መግባቱን የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት አስታውቋል።

አገልግሎቱ ለኢፕድ በላከው መግለጫ የሶማሊያ የመረጃና ደኅንነት ተቋም ልዑካን ቡድኑ ለሁለት ቀናት የሥራ ጉብኝት አዲስ አበባ ቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ሲደርስ የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ከፍተኛ ኃላፊዎች አቀባበል አድርገውለታል። የልዑካን ቡድን በኢትዮጵያ ቆይታው የሀገሪቱን የመረጃና ደኅንነት ተቋማት ይጎበኛል ተብሎ ይጠበቃል።

ሽብርተኝነትን ለመከላከል በሚደረጉ የመረጃ ልውውጦች፤ በአቅም ግንባታ መስኮች፤ ቀጣናዊ ሰላምና ደኅንነት ለማረጋገጥ በሚደረጉ የጋራ ስምሪቶች ዙሪያ ከብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት አመራሮች ጋራ ምክክር እንደሚደረግም ተገልጿል።

በቅርቡ በኢትዮጵያ በኩል ከብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ፣ከኢፌዴሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ ከኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊትና ከኢፌዴሪ ጤና ሚኒስቴር የተወጣጣ የልዑካን ቡድን በሶማሊያ በአልሻባብ ጥቃት ጉዳት ለደረሰባቸው ሶማሊያውያን የሚውሉ የተለያዩ የሕክምና መሣሪያዎችና መድሐኒቶችን በሀገሪቱ በመገኘት ድጋፍ ማድረጉን የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት የላከልን መረጃ አስታውሷል።

Exit mobile version