Site icon ETHIO12.COM

ወልቃይት-ጠገዴ እና ጠለምት፤ ዐማራጭ የመፍትሔ ሀሳቦች!

… አንዳንድ ወገኖች ደግሞ በተለይም የሚዲያ ባለቤቶች፤ሆን ብለው ለመረበሽና አጀንዳውን የገቢ ማስገኛ አድርገው ለመጠቀም ሲውተረተሩ እየታዘብን ነው፡፡ ገራሚው ነገር እነዚህ ባለሚዲያዎች፤ የዚህ አጀንዳ ዋነኛ ጠበቃ መስለው ለመታየት ጥረት የሚያደርጉ መሆኑ ነው፡፡ ግን እኮ እነዚህ ወጎኖች የወልቃይት-የጠገዴና ራያ አጀንዳ ተፈጥሮ ብዙዎች ዋጋ ከከፈሉ በኋላ ወደ ፖለቲካው ዓለም ብቅ ያሉ ናቸው፡፡ ይሄም ሆኖ በዚህ አጀንዳ ብዙ ዋጋ የከፈሉ አማራዊያን እያሉ እነሱ በጉዳዩ ዙሪያ አንዳች አስተዋጽኦ ሳይኖራቸው፤ የአጀንዳው ሻምፒዮን ሆነው ለመታየት መሞከራቸው ያስተዛዝባል፡፡

በቹቹ አለባቸው አበበ

የማንነት ትግላችን ዘ-ፍጥረት!

ወያኔ ወልቃይትን ከ1972 ዓ.ም በወረራ ከተቆጣጠረበት ዕለት ጀምሮ የወልቃይት አማራዎች ድርጊቱን በመቃወም ያልተቋረጠ ትግል እያደረጉ መጥተዋል፡፡ በተለይም በመጀመሪያ ከፋኝ የተባለ የታጠቀ ኃይል በተደራጀ መልኩ የወያኔን ወረራ በተግባር ተፋልሟል፡፡ የከፋኝ ብረት ያነገበ ንቅናቄ በወያኔ እንዲበተን ከተደረገ በኋላና ወያኔ መላ ኢትዮጵያን መቆጣጠሩን ተከትሎ፤ ወልቃይትና ጠገዴን እንዲሁም ጠለምትን ወደ ትግራይ ማካሉን በመቃወም የጎልማ (የጎንደር ልማት ማህበር) አመራሮች ድርጊቱን በጽኑ አውግዘው ጎንደር ይሄን ድርጊት እንደማይቀበለው፤ ጉዳዩ እዲስተካከል በክልል ደረጃ እና በፌደራል ደረጃ አቋማቸውን አሳውቀዋል (የወቅቱ ሊቀመንበር ዳኘው ወልደ ስላሴ ከፃፉት ታሪካዊ ደብዳቤ በተጨማሪ አቶ ባዩህ በዛብህ እና አቶ ስንታየሁ ተፈራ ሕያው ማመሳከሪያዎች ናቸው)፡፡

ይሁን እንጅ በወቅቱ የአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር የነበሩት አቶ መለስ ዜናዊና በአቶ አዲሱ ለገሰ ይመራ የነበረው የአማራ ክልል አስተዳር ቅሬታዎችን ተቀብሎ መፍትሄ ከመስጠት ይልቅ ጉዳዩን በጉልበት አፍነው መቀጠልን መረጡ፤ ይባስ ብለው አንጀዳውን ያነሱ የነበሩ ግለሰቦችን እና የጎልማ አመራሮችን ማሸማቀቅና ከሥራ ማባረርን ሥራየ አድርገው ተያያዙት፡፡ ነገረ ግን ይህ አጀንዳ በወቅቱ ዝቅ ሲል የጎንደር በጌምድር አጀንዳ ነበርና አዳፍኖ መቀጠል አልተቻለም፡፡

ጎንደሬዎች ልዩ ልዩ የትግል ስልቶችን በመከተል የወልቃይት፤ጠገዴና ጠለምት አጀንዳ ለአንዲትም ቀን እንዳይዳፈን ማድረግ ቻሉ፡፡ በሂደትም ራሱን የቻለ የወልቃይት-ጠገዴና ጠለምት አማራ አስመላሽ ኮሚቴዎችን በማደረጃት ወደ ሥራ እንዲገባና ትግሉ በተደራጀ መልኩ እንዲቀጥል ማድረግ ተቻለ፡፡ ይህ ኮሚቴ፤ የወልቃይት-ጠገዴ አጀንዳ የጎንደር በጌ ምድር አጀንዳ ብቻ ሳይሆን የመላው አማራ እንዲሆን አደረገ፡፡ በሂደትም የወልቃይት-ጠገዴ አማራነት አጀንዳ ከአማራ ዘሎ አካባቢው ባለው ጂኦ-ፖለቲካዊ ጠቀሜታ የተነሳ የመላ ኢትዮጵያዊያን ከፍ ሲልም አለም አቀፍ አጀንዳ ለመሆን በቃ፡፡

ይሄም ሆኖ የወልቃይት-ጠገዴና ጠለምት ጉዳይ ውስብስብና የብዙ ወገኖች ፍላጎት የሚታይበት አጀንዳ በመሆኑ ዛሬም ድረስ መቋጫ አላገኘም፡፡ ይሁን እንጅ ይህ አጀንዳ ለዝንታለሙ ተንጠልጥሎ ሊኖር አይገባም፡፡ የሆነ ቀን ላይ አጀንዳው ዘላቂ ሰላምን ሊያረጋጥ በሚችል መልኩ መዘጋት አለበት፡፡ ከዚህ አንጻር የተለያዩ ወገኖች፤ የወልቃይት-ጠገዴ እንዲሁም የራያ ግንባር የአማራ ማንንት ጥያቄዎች ስለሚፈቱበት አግባብ የየራሳቸውን አቋም ሲየንጸባርቁ መስማት የተለመደ ሆኗል፡፡ በዚህ በኩል የመንግሥት አቋም ግልጽ ነው፤ ጉዳዩ ህገ-መንግስታዊ መርህን ተከትሎ ይፈታል የሚል ነው፡፡ ይሄንን አቋሙንም ከወያኔ ጋር በፕሪቶሪያ ባደረገው የሰላም ስምምነት ላይ አጠናክሮታል፡፡

ለመሆኑ የወልቃይት-ጠገዴ፤ ጠለምትና ራያ አማራ አስመላሽ ኮሚቴዎች ጥያቄ ምንድን ነው? ለመሆኑ አሁን ላይ መፍትሄው ፖለቲካዊ እንጅ ህገ-መንግስታዊ መሆን አለበት የሚለውን ሀሳብ አንቀበልም የምንል ወገኖች፤ የወልቃይት-ጠገዴ፣ ጠለምትና ራያ አማራ አስመላሽ ኮሚቴዎች የማንነት ጥያቄው እንዲፈታ ያቀረቡት ህገ-መንግስቱን መሰረት አድረገው መሆኑን አናውቅም ይሆን? ለሁሉም ሦስቱም የማንነት ኮሚቴዎች ለፌደሬሽን ምክር ቤት ጥያቄያቸውን ያቀረቡት የኢፌድሪ ህገ-መንግሥትን የተለያዩ አንቀጾችን ጠቅሰው መሆኑን ልብ ማለት ይገባል፡፡ ታድያ ከዚህ በተፃራሪ መቆም ከጳጳሱ በላይ ክርስቲያን ነኝ ብሎ ከሚታበይ ምዕመን ጋር አያመሳስልም?

1. ሁኔታዎች ወዴት ያመራሉ…?

የፕሪቶሪያውን የሰላም ስምምነት ተከትሎ፤ የወልቃይት-ጠገዴ እና ጠለምት እንዲሁም ራያ ችግር አፈታትን በተመለከተ በአንዳንድ ወገኖች የአመለካከት ልዩነት ተስተውሏል፡፡ አንዳንዶቹ ችግሩ መፈታት ያለበት በህገ መንግስታዊ ማዕቀፍ መሆን አለበት የሚለውን የሚደግፉ ሲሆን፤ አንዳንዶቹ ደግሞ አካባቢዎቹ ድሮውም በጉልበት ስለተወሰዱ፤ አሁን ግን በአማራ እጅ ስለገቡ፤ ችግሩ መፈተታ ያለበት በፖለቲካ ውሳኔ ነው፤ ህገ-መንግስታዊ መፍትሄ የሚለውን አንቀበልም በማለት ይሞግታሉ፡፡ ይህ ስጋታቸው ከፍ ብሎ በነዚህ የአማራ መሬቶች ላይ መንግሥት ብቻውን ከወያኔ ጋር መደራደር የለበትም፤ “እውነተኛ የአማራ ወኪሎች” የድርድሩ አካል መሆን አለባቸው እስከማለት ደርሰዋል፡: በእነሱ እምነት “እውነተኛ የአማራ ወኪሎች” ያሏቸውን ግለሰቦችም ለይተው አሳውቀዋል፡፡ በእኔ እምነት ብዙዎቹ ወገኖች ይሄንን ሀሳብ የሚያነሱት በቅንነት፤ በመንግሥት ላይ ያላቸው እምነት ደካማ በመሆኑና 1983ን በማስታወስ ”እባብ ያየ በልጥ በረየ” ከሚል ስሜት እንደሆነ እረዳለሁ፡፡ ለድርድር ተወካይ ተብለው በተሰየሙት ሰዎች ላይም (ሁለቱን ብቻ ነው የማውቃቸው) በአማራ አጀንዳ ዙሪያ የሚታሙ አይመስለኝም፡፡ ከኔ ጋር ያለን ልዩነት በምን ዓይነት አግባብ ነው ‹የአማራ ወኪል እኛ ነን› ብሎ መቅረብ የሚቻለው? የሚለው ላይ ነው፡፡

ከዚህ በተረፈ አንዳንድ ወገኖች ደግሞ በተለይም የሚዲያ ባለቤቶች፤ሆን ብለው ለመረበሽና አጀንዳውን የገቢ ማስገኛ አድርገው ለመጠቀም ሲውተረተሩ እየታዘብን ነው፡፡ ገራሚው ነገር እነዚህ ባለሚዲያዎች፤ የዚህ አጀንዳ ዋነኛ ጠበቃ መስለው ለመታየት ጥረት የሚያደርጉ መሆኑ ነው፡፡ ግን እኮ እነዚህ ወጎኖች የወልቃይት-የጠገዴና ራያ አጀንዳ ተፈጥሮ ብዙዎች ዋጋ ከከፈሉ በኋላ ወደ ፖለቲካው ዓለም ብቅ ያሉ ናቸው፡፡ ይሄም ሆኖ በዚህ አጀንዳ ብዙ ዋጋ የከፈሉ አማራዊያን እያሉ እነሱ በጉዳዩ ዙሪያ አንዳች አስተዋጽኦ ሳይኖራቸው፤ የአጀንዳው ሻምፒዮን ሆነው ለመታየት መሞከራቸው ያስተዛዝባል፡፡

ለሁሉም አንዳንዴ ‹ሰው ይታዘበናል› ማለት ጥሩ ነው፡፡ ስለ ወልቃይት-ጠገዴ እና ራያ ዋጋ የከፈሉት እነማን ናቸው? ዛሬ ላይ ስለ ወልቃይትና ራያ ከኛ በላይ አማራ የለም የሚሉት ብዙዎቹ ወገኖች ያ ሁሉ ዋጋ ሲከፈል የት ነበሩ? ዛሬ ላይስ የያዙት አቋም አማራን ምን ያክል ያሻግረዋል ? የሚሉት ጥያቄዎች በቅጡ መመርመር አለባቸው፡፡

ለመሆኑ የወልቃይት-ጠገዴ፤ ጠለምትና ራያ አማራ አስመላሽ ኮሚቴዎች ጥያቄ ምንድን ነው? ለመሆኑ አሁን ላይ መፍትሄው ፖለቲካዊ እንጅ ህገ-መንግስታዊ መሆን አለበት የሚለውን ሀሳብ አንቀበልም የምንል ወገኖች፤ የወልቃይት-ጠገዴ፣ ጠለምትና ራያ አማራ አስመላሽ ኮሚቴዎች የማንነት ጥያቄው እንዲፈታ ያቀረቡት ህገ-መንግስቱን መሰረት አድረገው መሆኑን አናውቅም ይሆን? ለሁሉም ሦስቱም የማንነት ኮሚቴዎች ለፌደሬሽን ምክር ቤት ጥያቄያቸውን ያቀረቡት የኢፌድሪ ህገ-መንግሥትን የተለያዩ አንቀጾችን ጠቅሰው መሆኑን ልብ ማለት ይገባል፡፡ ታድያ ከዚህ በተፃራሪ መቆም ከጳጳሱ በላይ ክርስቲያን ነኝ ብሎ ከሚታበይ ምዕመን ጋር አያመሳስልም?

ለሁሉም በእኔ በኩል ስለ ወልቃይት-ጠገዴና ጠለምት እንዲሁም ራያ አጀንዳ፤ ከእነ እንቶኔ በላይ እኔና ጓዶቼ ዋጋ ስለመክፈላችን በሙሉ ልብ እናገራለሁ፡፡ መፍትሄ ያልኳቸውንም ነጥቦችም ዛሬ ሳይሆን ቀደም ሲል አመላክቻለሁ (‹‹ዳገት ያበረታው የዐማራው ፍኖት›› [2010] የተሰኘውን መጸሐፌን ያነበበ እውነታውን ያውቀዋል)፡፡ እኔና ጓዶቼ ስለ ወልቃይት-ጠገዴና ራያ ጉዳይ የዘመኑ መንፈስ ነድቶ ያመጣን ሳንሆን፤ በዛ የጭለማ ዘመን ዋጋ የከፈልን፤ ለትግሉ የሚበጀውን መውጫ መንገዱን ያመላትከን ሰዎች ነን፡፡ አሁንም የበለጠ ለማስረገጥ ያክል ስለወልቃይት-ጠገዴ እና ራያ ግንባሮች መፍትሄ ናቸው ያልኳቸውን ነጥቦችን ዛሬም ላይ ሆኘ የማጠናክራቸው፣ በዕድሜና በትግል ልምድ የቀሰምኳቸው እውነታዎች ስለሆኑ ነው፡፡

በዚህ ጽሁፍ የወልቃይትን ብቻ አነሳለሁ፡፡ የራያ ግንባር መፍትሄም ከሞላ ጎደል በተመሳሳይ አግባብ ሊታይ የሚችል ነው (የራሱ የሆነ አፈታት ባህሪ እንዳለው ሆኖ)፡፡

2. ለወልቃይት የዐማራ ማንነት ጥያቄ ዐማራጭ የመፍትሔ ሀሳቦች!

ወልቃይት-ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ለዘመናት በጎንደር ክፍለ ሀገር ዳባት አውራጃ፤ ቀደም ሲል ደግሞ በበጌምድርና ስሜን ጠቅላይ ግዛት ይተዳደር የነበረ እንጅ አንድም ቀን በትግራይ ተከዜን ተሻግሮ እንደማያውቅ ታሪክ ምስክር ነው፡፡ ከቅድመ-አክሱም እስከ 1983 ድረስ ወልቃይት-ጠገዴ ሰቲት ሁመራ የበጌምድር እንጅ የትግራይ ሆነው አያውቁም፡፡

የጥንታዊት ኢትዮጵያ ነገዶች ታሪክ ፀሐፊ አለቃ ታዬ ወልደማርያም “የኢትዮጵያ ህዝብ ታሪክ፡ ባጭር ቃል የወጣ” በሚል ርዕስ በ 1919 ባሳተሙት መፅሐፍ ውስጥ፡- ‹‹ከለው ከሳባ ወደ ምዕራብ ወደ ደቡብ ያለ የአማራ የወልቃይት-ጠገዴ አባት ነው።›› ሲሉ ይገልጹታል፡፡ ወልቃይት-ጠገዴ የከለው ልጅ፤ የአማራ የዘር ግንድ መነሻ ነው ስንል የታሪክ ማስረጃ ይዘን ነው፡፡

“ትግሬ እንጅ ትግራይ ተከዜን ተሻግራ አታውቅም” የሚለው አባባል የታሪክ እውነታ አለው፡፡ ምክንያቱም ቅድመ-1983 በነበሩ ጊዜያት የትግራይ ተወላጆች የግንባታ ስራ፣ ለቤተ-ክርስቲያን አገልግሎት፣ እንዲሁም የግብርና ሥራ ሰርተው ለመመለስ እንጅ ለነዋሪነት ከተከዜ ምላሽ መጥተው አያውቅም ነበርና፡፡

2.1. ወልቃይት እና ፖለቲካዊ እውነታዎች!

ወያኔ ገና ከመነሻው በግዛት ተስፋፊነቱ ተከዜን ተሻግሮ ወልቃይት ላይ የፈፀመው ወረራ በሁለት መሰረታዊ ምክንያቶች ነው፡-

1ኛ. በወያኔ ለታለመችው የ “ታላቋ ትግራይ ሪፐብሊክ” የምግብ ዋስትና የሚያረጋግጥ

ለም መሬት በመፈለግ፤

2ኛ. ለወደፊቷ በ‹‹ሀገርነት›› ለታጨችው ለ ‹‹ታላቋ ትግራይ›› ከቀሪው ዓለም ጋር

የየብስ መውጫና መግቢያ ስትራቴጂያዊ በር ለማግኘት በመፈለግ የተፈጸመ ወረራ

ነበር፡፡

ይህን ፖለቲካዊ እውነታ ከወያኔ ጋር አብረው በታገሉ የቀድሞ ታጋዮች ምስክርነት አስደግፈን እንመለክተው፡-

‹‹…በታሪክ የትግራይ ወሰን እስከ ሱዳን ነው የሚል ነገር የለም፡፡ የትግራይ ክልል በማንኛውም ጊዜ ከሱዳን ጠረፍ ጋር የተያያዘ ነው የሚል ታሪክ ፈጽሞ የለም፡፡ ይሁን እንጅ ‹የትግራይን ሪፐብሊክ እንመሰርታለን› በሚል ከጎንደር ወልቃይትን በመቁረጥ እስከ ሱዳን ድረስ፣ እንዲሁም ከወሎ ሰቆጣን፣ አሸንጌን፣ አላማጣ (ራያ)ን ወስዶ እስከ አሰብ ድረስ አዲስ ካርታ ተነድፏል፡፡ ይህ ካርታ ፈጽሞ በታሪክ የሌለ ከመሆኑም ሌላ አሁንም ሆነ ወደፊት ከአጎራባች ክፍላተ ሀገር ጋር የሚፈጥረው ችግር ከፍተኛ ይሆናል ብዬ እገምታለሁ፡፡ የወሎንም ሆነ የጎንደርን መሬት የእኔ ነው ብሎ የሚነሳ ክፍል ከእነዚህ ሕዝቦች ጋር ከፍተኛ ቅራኔ መፍጠሩ የማይቀር ነው፡፡ (ገብረመድኀን አርዓያ፤ ታላቁ የወያኔ ሴራ፣ 1982)››

የቀድሞው የወያኔ ታጋይ የሰጡትን ምስክርነት በሌላ መልኩ የሚያጠናክሩልን በወቅቱ የወያኔ ወታደራዊ ኮማንደር አዛዥ የነበሩት አረጋዊ በርኼ (ዶ/ር) ናቸው፡፡ ከስድስት ዓመት በፊት ለኢትዮጵያ ሳተላይት ቴሌቭዥን (ኢሳት) በሰጡት ቃለ-መጠይቅ በትግሉ ወቅት ‹‹ወልቃይትን መቆጣጠር ያስፈለገው ወደሱዳን መውጫ ለማግኘት ነው›› ሲሉ የወልቃይትን ጂኦ-ፖለቲካዊ ጠቀሜታ ገልጸዋል፡፡

ወልቃይትና የወያኔ ‹‹ነጻ ትግራይ ሪፐብሊክ›› ቅዠት ከምስረታው ጀምሮ ትስስር አላቸው፡፡ ለዚህ አብነት ለአስር ዓመት አብሯቸው የታገለው የኢህዴኑን ያሬድ ጥበቡን ምስክርነት እንጠቅሳለን፡- ወያኔ የነጻ ትግራይ ሪፐብሊክ ማቋቋም ዓላማ በነበረው ወቅት፣ አንደኛ ከውጭው ዓለም የሚያገናኝ መስመር ፍለጋ፣ ከፖርት ሱዳን ወደብ ጋር የሚያገናኝ የሱዳን መሬት ወሰን በመፈለግ፣ ሁለተኛ፣ (ከተከዜ ወዲያ ያለችው መደበኛዋ ትግራይ) መሬቱ ያለእረፍት ሲታረስ በመኖሩ ምርቱ እየደከመ የመጣ በመሆኑና በአንጻሩ ወልቃይት/ሁመራ ሰፊ ያልታረሰ ድንግል መሬትና እንደሰሊጥ ዓይነት ለውጭ ገበያ የሚቀርብ ሰብል የሚያመርት በመሆኑ፣ ነጻ ለትምትወጣው (የትግራይ ሪፐብሊክ) ትልቅ ለም መሬት ስለሚያስገኝ ወልቃይትን ለመጠቅለል ታቀደ፡፡

የወያኔ መሪዎች ወልቃይት-ጠገዴ የቢትወደድ አዳነ አገር (አባ ደፋር) መሆኑን ያውቁ ስለነበር፣ በትጥቅ ትግሉ ማጠናቀቂያ ዓመታት ‹ክሳድ ግመል› መሬት ውስጥ የስምሪት ጣቢያ (ቤዝ አምባ) የመሠረቱ ቢሆንም፣ የትግራይ ነው ሲሉ ሰምቼም አላውቅም፡፡ በግርግር የጨመሩት መሬት ነው፡፡ የትግራይን ነጻ ሪፐብሊክ የማቋቋም ዓላማ ትተናል በሚባልበት ወቅት፣ ወልቃይትንና ጠገዴን ትግሬ የማድረግ ህልሙ ግን አልቆመም ነበር፡፡

በ1972 ዓ.ም. አጋማሽ ላይ ወያኔ ወልቃይትን ለመውረር ሲመጣ በመጀመሪያ የኢሕአፓን ጦር መደምሰስ ነበረበት፡፡ የኢሕአፓ ሠራዊት ከየሪጅኑ የተውጣጣ ኃይል ሰብስቦ ደባርቅና ደባት አካባቢ ለመንቀሳቀስ አብዛኛውን ኃይሉን ከወልቃይት ባራቀበት ወቅት ወያኔ ድንገት ከፍተኛ የሰራዊት ኃይሉን ይዞ ወልቃይትን ወረረ፡፡ ከያዘ በኋላ ለማስለቀቅ ቀላል አልሆነም፡፡ ብዙ የኢሕአፓም ሆነ የወያኔ የሠራዊት አባላት የተወሰውበት የሽሬላና የቆላ መዘጋ ጦርነቶች የተካሄዱ ቢሆንም፣ ወያኔን ከወልቃይት መንቀል ግን አልተቻለም፡፡ እንደገና ወደጠለምት ለማፈግፈግ ተገደድን፡፡ ወያኔ 1972 አጋማሽ ጀምሮ የወልቃይት ይዞታውን ለማጠናከር (መንግሥት ከሆነ በኋላ) በከፍተኛ ደረጃ የመሬት ችግር ያለባቸውን ትግሬዎች እያመጣ አሰፈረ፡፡ ባለፉት ሠላሳ ዓመታት አስከ ሰማንያ ሺሕ ሕዝብ ከትግራይ አምጥቶ እንዳሰፈረ ይነገራል፡፡ አዲስ አበባም እንደገባ ከምዕራባውያን ጋር የሠራዊት ቅነሳ ለማድረግ ሲስማማም፣ ለቅነሳው ማካሄጃ የተሰጠውን ድጎማ በመጠቀም ተቀናሾቹን የወያኔ ሠራዊት አባላት በቃፍቲያና ዳንሻ አካባቢ ሠላሳ ሺሕ የቀድሞ ወያኔ አባላትን ከነትጥቃቸው አስፍሯል፡፡ (ያሬድ ጥበቡ፣ ወጥቼ አልወጣሁም፤ ገጽ፣ 188-189)

በ1983 ዓ.ም ወደሥልጣን የመጣው የወያኔ/ኢህአዴግ አገዛዝ በወቅቱ የነበሩ ገዥ ሕጎችን በግልጽ በተቃረነ የፖለቲካ ውሳኔ አካባቢዎቹን ወደትግራይ ክልል በጉልበት ከልሏቸዋል፡፡ ይህን ፖለቲካዊ እውነታ ከሕግ አንጻር በሚከተሉት አብነቶች እንፈትሸው፡-

አንደኛ፡- የኢትዮጵያ የሽግግር ጊዜ ቻርተር አንቀጽ ቁጥር 13 ‹‹የክልሎች አስተዳደር በብሄሮች በብሄሮች አሰፋፈር ላይ ተመርኩዞ ይቋቋማል››፤

ሁለተኛ፡- የብሔራዊ ክልላዊ የሽግግር መስተዳድሮች ማቋቋሚያ አዋጅ ቁጥር 7/1984 በአንቀጽ በአንቀጽ ቁጥር 4 ደግሞ ‹‹የብሔር፣ ብሄረሰብ እና ሕዝብ ኩታ ገጠም አሰፋፈር ለብሄራዊ መስተዳድር ወሰን አከላለል መሰረት ይሆናል››

ሦስተኛ፡- የኢፌዴሪ ሕገ-መንግሥት አንቀጽ ቁጥር 46 ‹‹ክልሎች የሚዋቅሩበትን የሕዝብ አሰፋፈር፣ ቋንቋ፣ ማንነትና ፍቃድ ላይ በተመሰረተ ሁኔታ ይሆናል›› ይላል፡፡

በዚህም የወልቃይት-ጠገዴና ጠለምት ሕዝብ በብሄር፣ በኩታ ገጠም አሰፋፈር፣ በማንነትና በቋንቋ ከሚመስለው የቀድሞው ስሜን በጌምድርና ጎንደር ክፍለ-ሀገር የተካለሉበት የዐማራ ክልል ወጥቶ በኃይልና በጉልበት ወደትግራይ ክልል ተከልሎ ለሠላሳ ዓመታት ቆይቷል፡፡

ይህ የግዛት ተስፋፊነትን ማዕከሉ ያደረገ አከላለል፣ ከዚህ በላይ የተመለከቱ ሕጎች ካስቀመጡት መስፈርት ጋር በተቃርኖ የሚቆም ሲሆን፤ በአንፃሩ በ1968 ዓ.ም. ወያኔ ባዘጋጀው ማኒፌስቶ ላይ ለትግራይ ሕዝብ እና መሬት የሰጠውን ትርጓሜ ገቢር አድርጓል፡፡ ጎንደሬን በግድ ‹ትግሬ ነህ› ሲል፤ መሬቱን ‹‹የትግራይ›› በሚል በጉልበት ይዞት ቆይቷል፡፡ በመሆኑም ሕዝቡ ወደትግራይ ከተካለለበት ጊዜ ጀምሮ ለረጅም ጊዜ ስለዐማራዊ ማንነቱ እና ወደዐማራ ክልል መካለልም እንደሚፈልግ ሲጠይቅ እና ሲታገል ዋጋም ሲከፍል ቆይቷል፡፡

የማንነት ጥያቄው በተደራጀና ሕጋዊ ሥነ-ሥርዓትን በተከተለ መልኩ የወልቃይት ማንነት አስመላሽ ኮሚቴ ለትግራይ ክልላዊ መንግሥት በአዋጅ ቁጥር 251/2001 መሰረት እና ለፌዴሬሽን ምክር ቤት በኢፌዴሪ ሕገ-መንግሥት አንቀጽ ቁጥር 46 መሰረት የማንነት ጥያቄውን ቢያቀርብም ጥያቄውን በጉልበት ሊያፍን የሞከረው ወያኔ፣ ለዛሬው ውድቀቱ ምክንያት የሆነውን የሕዝብ አመጽ ቀስቅሶበታል፡፡

3.2. የወልቃይት-ጠገዴ የዐማራ ማንነት ጥያቄ የጋራን ዕድል በጋራ መወሰን ስለመሆኑ…

ቴዎድሮስ ታደሠ በላይ የተባለ የሰብዓዊ መብቶች ተመራማሪ የማይካድራን የዘር ጭፍጨፋ በተነተነበትና ከሌሎች ጸሐፍት ጋር በጋራ ባሳተሙት ‹‹የወልቃት፣ ጠገዴና ጠለምት የታፈኑ እውነታዎች›› በተሰኘ መጽሐፍ ላይ የወልቃይት-ጠገዴና ጠለምት የዐማራ ሕዝብ ጥያቄ፡-

 የማንነትና እውቅና ጥያቄ፣

 ራስን በራስ የማስተዳደር ጥያቄ፣

 የራስን ዕድል በራስ የመወሰን ጥያቄ ብቻ እንዳልሆነ ይሞግታል፡፡

የሕዝቡ ዐማራዊ ማንነት እውቅና ተሰጥቶት፣ በጉልበት ከተያዘበት ከትግራይ ክልል ወጥቶ በማንነት፣ በባህል፣ በአሰፋፈር፣ በታሪክ፣ በቋንቋ እና በስነ-ልቦና ከሚመስለው የዐማራ ሕዝብ ወደሚተዳደርበት የዐማራ ክልል መጠቃለል ነው፡፡ በዚህም ጥያቄው የማንነት፣ የመገንጠል እና ወደዐማራ ክልል የመጠቃለል ጥያቄዎችን በአንድ ላይ አጣምሮ የያዘ ድርብድብ ጥያቄ ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ጥያቄው የወልቃይት-ጠገዴና ጠለምት ሕዝብ ጥያቄ ብቻ ሳይሆን ‹‹የሕዝቡን ዐማራዊ ማንነት ተቀብሎ መሬቱን ብቻ ሳይሆን ሕዝቡንም በዐማራ ክልል ውስጥ የማስተዳደር ጥያቄ›› የዐማራ ሕዝብና የዐማራ ክልል መንግሥት ጥያቄም በመሆኑ ሕዝቡ ሲጠይቀው ከነበረው የጥያቄ ይዘት፤ የዐማራ ሕዝብ እና መንግሥት ጥያቄ ጋር ተዳምሮ ጉዳዩ ‹ኢሪደንቲዝም› (Irredentism) በሚል አውድ ይገለጻል፡፡

እንደሕግ ባለሙያዎች ትንታኔ ‹ኢሪደንቲዝም› ሁኔታው የሕግ እና ፖለቲካዊ ጉዳዮችን አጣምሮ የያዘ ሲሆን፤ አንድ ማኀበረሰብ በራሱ ሳይሆን ከሌላ ‹የእኔ ነው› ከሚለው ማኀበረሰብ ጋር በጋራ በመሆን ፖለቲካዊ እና ማኀበራዊ ህልውናውን የሚወስንበት አካሄድ ነው፡፡ ጥያቄው በአንድ ለመዋሀድ በሚፈልጉት ሁለት ተመሳሳይ ማኀበረሰቦች (ሕዝብ) የጋራ ጥረት እና ፍላጎት እንጅ አንደኛው ማኀበረሰብ ብቻ ስለፈለገ በራሱ የሚያደርገው ባለመሆኑ ሁኔታውን የራስን (የወልቃይት፣ ጠገዴና ጠለምት) ዕድል በራስ መወሰን ሳይሆን የጋራን (የወልቃይት፣ ጠገዴና ጠለምት ዐማራን) ዕድል በጋራ መወሰን የሚለው ሀሳብ በጋራ ይገልፀዋል፡፡ በአጭሩ የወልቃይት ጉዳይ እንደዐማራ የጋራ ዕድልን በጋራ የመወሰን ጉዳይ ነው፡፡ ሁኔታው ከፍ ብሎ ሲታይም የኢትዮጵያ ሀገረ-መንግሥት ህልውና መቋጠሪያ ነው፡፡

3. ወደመፍትሔው…

በአሁኑ ወቅት የወልቃይት-ጠገዴ፣ ጠለምት ዐማራ ሕዝብ ጥያቄ በተመለከተ፣ በተለያዩ ወገኖች አማካኝነት የተለያዩ ዐማራጭ የመፍትሔ ሐሳቦች ሲቀርቡ ይደመጣሉ፡፡ አብዛኞቹ መፍትሔ አቅራቢ ወገኖች በአንድ ነገር በጋራ ይስማማሉ፡፡ ይኼውም ባለፉት ሠላሳ ዓመታት የወልቃይት-ጠገዴና ጠለምት ዐማራ ሕዝብ በወያኔ አገዛዝ የጅምላ ፍጅት፣ አፈናና እስር ከቅኝ ግዛት በከፋ አስተዳደር ስር ሲማቅቅ እንደኖረ፣ ምንም እንኳ በሕግ ያልጸና ቢሆንም ነጻነቱን ያገኘው ድኀረ-ጥቅምት 24/2013 እንደሆነ ብዙዎች ይስማማሉ፡፡ እነዚህ ወገኖች በዚህ ነጥብ ላይ ተስማምተው ሲያበቁ መፍትሔ በሚሏቸው ዐማራጮች ላይ ግን የተለያየ አቋም ሲያንጸባርቁ ይደመጣሉ፡፡

በዚህ በኩል የሚንጸባረቁትን አራት ዋና ዋና ዐማራጭ የመፍትሔ ሐሳቦችን እንደሚከተለው ለማቅረብ እሞክራለሁ፡፡

ችግሩን በፖለቲካ ውሳኔ መፍታት፡- ቅድመ-1983 በነበረው የኢትዮጵያ ግዛት አስተዳደራዊ ታሪክ ውስጥ ወልቃይት-ጠገዴና ጠለምት የትግራይ ግዛት አስተዳደር ሆነው እንደማያውቁ የታሪክ ሀቅ ነው፡፡ ወያኔ በግዛት ተስፋፊነቱ በጉልበት ይዞት እንደቆየ ታምኖበት፣ በፖለቲካ ውሳኔ ወደቀደመ እናት ግዛቱ (በጌምድር፤ ዐማራ) እንዲመለስ መወሰን አንደኛው ዐማራጭ ነው፡፡ ይህ መሰሉ የፖለቲካ ውሳኔ፡- ወያኔ የኢፌዴሪ ሕገ-መንግሥት ከመጽደቁ ከሦስት ዓመት ቀደም ብሎ የሽግግር ቻርተሩን ጥሶ የወሰደው በመሆኑ፣ የወልቃይት ጉዳይ ሊፈታ የሚገባው በሕገ-መንግሥታዊ መፍትሔ ነው የሚለውን ሙግት ውሃ እንዳያነሳ ያደርገዋል፡፡

ችግሩን በሕዝበ ውሳኔ መፍታት፡- በሁለተኛ ደረጃ የሚደመጠው የመፍትሔ ሀሳብ ደግሞ፣ ሕዝበ ውሳኔ ይደራጅ የሚል ነው፡፡ እዚህም ላይ ይህን ሀሳብ የሚደግፍ በሚመስል መልኩ፣ ከአንዳንድ የቀድሞ የወያኔ ነባር አመራሮች ተመሳሳይ አስተያየት ሲሰጥ ይደመጣል፡፡ ችግሩ በሕዝበ ውሳኔ ይፈታ በሚለው ነጥብ ዙሪያ፣ በባለቤቱ የወልቃይት-ጠገዴና ጠለምት ዐማራ ሕዝብ እና በወያኔ መካከል መሠረታዊ ልዩነት አለ፡፡ ይኼውም ባለቤቱ ሕዝበ ውሳኔ ይደረግ ሲል፣ ተወላጁ የወልቃይት-ጠገዴና ጠለምት ሕዝብ ብቻ ይወስን (ከሁሉ በፊት በወያኔ የግፍ አገዛዝ ዘመን የተፈናቀለው ከ 500,000 [አምስት መቶ ሺህ] በላይ ሕዝብ ይመለስ) ማለቱ ነው፡፡

በወያኔዎች በኩል ደግሞ ሕዝበ ውሳኔ ይደረግ ሲሉ አሁን በተጨባጭ ወልቃይት-ጠገዴና ጠለምት ያለው ሕዝብ (ድኀረ-1983 ለፖለቲካል-ኢኮኖሚ ዓላማ ያሰፈሯቸውን የትግራይ ተወላጆች ባካተተ መልኩ) በሙሉ የተሳተፈበት ሕዝበ ውሳኔ ይካሄድ ማለታቸው ነው፡፡ ይሄንን የተንሸዋረረ ዐማራጭ የወልቃይት-ጠገዴና ጠለምት ሕዝብ ብቻ ሳይሆን መላው የዐማራ ሕዝብ ይቀበለዋል ተብሎ አይታሰብም፡፡ ሕዝበ ውሳኔ የሚካሄድ ከሆነ በሕዝበ ውሳኔው የሚሳተፉ ቅድመ-1983 የነበሩ የትግራይ ተወላጆች እንጅ ድኀረ-1983 ወያኔ አምጥቶ ያሰፈራቸው የትግራይ ተወላጆች የሕዝበ ውሳኔው አካል ሊሆኑ አይገባም፡፡ ስለሆነም አቶ ያሬድ ጥበቡ ከላይ በተጠቀሰ መጽሐፋቸው ላይ በትክክል እንደሞገቱት ይህ መፍትሔ ሊሠራ ከሆነ “ከማንኛውም ሕዝበ ውሳኔ በፊት ወልቃይት ወደ ነበረበት መመለስ… ይኖርበታል፡፡ ይህ ቅድመ ሁኔታ ሳይሟላ ስለሕዝበ ውሳኔ ማውራት አይቻልም” (ገጽ፣189)፡፡

ወልቃይት የዐማራ መሬት መሆኗን እውቅና መስጠት፡- ሦስተኛው የመፍትሔ ሐሳብ ደግሞ፣ከሁሉም በፊት ወልቃይት ሰውም ጎንደሬ ነው፤ መሬቱም የዐማራ› የሚለውን ሀሳብ ከልብ መቀበልን ይጠይቃል፡፡ የዚህ መፍትሔ ዋነኛ ጭብጥ አስተዳደራዊ ባለቤትነቱ (ርስትነቱ) የወልቃይት- ጠገዴና ጠለምት ዐማራ ሆኖ፣ ትግሬዎች ደግሞ እንደማንኛውም የኢትዮጵያ ብሔር ብሄረሰቦች ወልቃይት ውስጥ መብታቸው ተጠብቆላቸው እንዲኖሩ ማድረግን ታሳቢ ያደረገ ነው፡፡ ይህ ከወያኔና ከአስተሳሰቡ ተሸካሚዎች በስተቀር ሁሉንም ሊያስማማ የሚችል የመፍትሔ ሐሳብ ነው፡፡ ይሁን እንጂ ይህን አመለካከት ወያኔና ደጋዎቹ እንዲህ በቀላሉ ይቀበሉታል ብሎ ማሰብ ይከብዳል፡፡ በእኔ እይታ የጊዜ ጉዳይና የዐማራ ብልጽግና የመደራደር አቅም መዳከም ወይም መጠንከር ካልሆነ በስተቀር ሊታይ የሚችል ተመራጭ መፍትሔ ነው፡፡

የተፈጥሮ ወሰን ይከበር፡- በዚህ በኩል የሚነሳው መፍትሔ የታሪክ ሀቆችን መነሻ በማድረግ ተከዜ ወንዝ የዐማራና የትግራይ ተፈጥሯዊ ወሰን መሆኑን በመቀበል ችግሩን ለዘለቄታው መፍታት ይቻላል የሚል አመለካከት ነው፡፡ ይህንን የመፍትሔ ሀሳብ ዐማራም ቢሆን በወሳኝነት የሚቀበለውና ሲታገልለት የኖረው ሕዝባዊ ዓላማው ነው፡፡

ዘለቄታዊ መፍትሔውም ይሄው የተፈጥሮ ወሰንን ማስከበር ነው፡፡ የትግራይ ተወላጆችም ከወያኔ አስተሳሰብ እስከተላቀቁ ድረስ እንደማንኛውም የኢትዮጵያ ብሔር ብሄረሰብ በወልቃት-ጠገዴና ጠለምት ከቦታ ቦታ ተንቀሳቅሰው መስራት፣ ሀብት ንብረት ማፍራት ይችላሉ፡፡ ከዚህ ውጭ ያለው ዐማራጭ ወልቃይትን አኬልዳማ ከማድረግ በዘለለ ፋይዳ አይኖረውም፡፡

ከላይ የቀረቡት አራት ዐማራጮች በአንድም ሆነ በሌላ አግባብ የወልቃይት-ጠገዴና ጠለምት ዐማራ ማንነት ለማስመለስ የሚደረገውን ትግል የሚያሳኩ ናቸው። ይሁን እንጂ፣ ወያኔና የአስተሳሰቡ ተሸካሚ የሆኑ የትግራይ ወንድሞቻችን እነዚህን ዐማራጮች (በተለይም ዐማራጭ 1, 3, እና 4ን) በቀላሉ ይቀበሏቸዋል ተብሎ አይጠበቅም።

ወያኔም ሆነ ማህበራዊ መሰረቱ እየመረራቸውም ቢሆን ሊቀበሉት የሚችሉት ሁለተኛውን ዐማራጭ እንደሚሆን መገመት አይከብድም። የእኔ ምክር ደግሞ የአማራ ሕዝብና የአማራ ክልል መንግሥት ከሁሉ በፊት በተራ ቁጥር 1፣ 3 እና 4 ላይ የተቀመጡትን አማራጮች ዋነኛዎቹ አድርጎ መውሰድ አለበት የሚል ነው፡፡ በዚህ ረገድ የአማራ ወዳጆችና የኢትዮጵያ ሀገረ-መንግሥት ህልውናን መቀጠል የሚፈልጉ መላ ኢትዮጵያዊን ከግፉዓን የወልቃይት-ጠገዴና ጠለምት ዐማራዎች ጎን እንደሚሰለፉ አልጠራጠርም፡፡

ከእነዚህ አማራጮች ውጭ የሚታሰብ ከሆነ ግን፤ በወያኔ 30/40 አመታት የአገዛዝ ዘመን የተፈናቀሉ ከ500, 000 በላይ ተፈናቃይ የአማራ ተዎላጆች ወደ ቀያቸው መመለስ አለባቸው የሚለው የመከራከርያ ነጥብ ቀይ መስመር መሆን አለበት እላለሁ።

4. ማጠቃለያ

የወልቃይት-ጠገዴና ራያ ጉዳይ የሚፈታው በህገ-መንግስታዊ ማእቀፍ እንደሚሆን አትጠራጠሩ፡፡ ቁም ነገሩ በሕገ-መንግሥታዊ ማዕቀፍ ሲባል ምን ማለት ነው የሚለውን አብጠርጥሮ መያዝ፣ መተንተንና ማንቃት ይጠይቃል፡፡ ይህ መሆን ሲገባው ወደ ተግባር የማይቀየር ነገር በማውራት አማራን አሸናፊ ማድረግ አይቻልም፡፡ ከዚህ ጋር በተያያዘ ሕገ-መንግሥቱን በማይፃረር መልኩ የወጡ አዋጆችን መዘርዘር ይቅርና የኢፊድሪ ህገ የመንግሥት በአ/ቁ 48 የአከላለል ለውጦችን በሚመለከት የፌደሬሽን ምክር ቤት “የሕዝብ አሰፋፈር እና ፍላጎትን መሰረት” በማድረግ እንዲወስን ስልጣን እንደሚሰጠው ለማስተዋል የሁለተኛ ደረጃ ተማሪ መሆን በቂ ነው፡፡

በዚህ በኩል ብዥታ ያለባችሁ ወገኖች ብዥታችሁን አጥሩ፡፡ ምድር ላይ መስራት የሚገባንን ስራ እስከሰራን ድረስ አማራ (በወሰንና ማንነት ጉዳዮች) በዚህ ህገ-መንግስታዊ ማዕቀፍ ስር ሆኖ ማሸነፍ ይችላል፡፡ የቤት ስራችንን ስለመስራታችን ግን እርግጠኛ መሆንን ይጠይቃል፤ በተለይም የክልሉ መንግስትና የአካባቢዎቹ አስተዳሮች፡፡ ሳይሰሩ ድልን መጠበቅ ደግሞ ጅልነት ነው፡፡ ከዚህ ውጭ ማህበራዊ ሚዲያው ተመቸኝ ብሎ ተግባራዊ ማይሆን ነገር ሲያወሩ ከመዋል፤ ወደ ምድር ወርዶ ስራ መስራ ይሻላል፡፡ እውነትም አጀንዳው የሚያሳስባችሁ ወገኖች ካላችሁ ኑ ወደ ወልቃይት-ጠገዴ፤ ጠለምት፤ ራያ፤ ኦፍላ፤ አበርገሌ ውረዱ፤ ምድር ላይ የሚሰራ ብዙ ስራ አለ፡፡ ይሄው ነው፡፡

ሰላማችን የፀና ይሁን!

Exit mobile version