Site icon ETHIO12.COM

ኢትዮጵያና ኬንያ ሽብርተኝነት፣ ህገ ወጥ የሰዎች ዝውውርና የተደራጁ ወንጀሎችን በጋራ ለመከላከል ውል ገቡ

የኢትዮጵያ መንግስት ከሶማሌና ጅቡቲ ጋር በማንኛውም መልኩ ሁለገብ የሆነ የጸጥታ፣ ደህንነትና ሽብረተኛነትን አብሮ የመዋጋት፣ መረጃ የመቀያየርና ወንጀለኞችን አሳልፎ የመቀባበል ውል ካደረገ በሁዋላ ዛሬ ከኬንያ ጋር ተሰመሳሳይ ስምምነት ማድረጉ ተውቋል።

ከጊዜ ወደ ጊዜ በምስራቅ አፍሪካ እየተስፋፋ የመጣውን የሽብርተኝነት፣ ፣የሰዎች ዝውውርና የተደራጁ ወንጀሎች በሀገራትና ህዝቦች ላይ የሚያስከትለውን ስጋትና አደጋ ለመከላከል ሀገራት የተቀናጁ እርምጃዎችን ለመውሰድ የሚያስችላቸውን የትብብር ስምምነት ማድረጋቸውን ኦቢኤን ነው ያመለከተው።

የኢትዮጵያና የኬንያም እያደገ በምስራቅ አፍሪካ እያደገ የመጣውን ሽብርተኝነት፣ ህገ ወጥ የጦር መሣሪያዎች ፣ ህገ ወጥ የገንዘብ፣ የሰዎች ዝውውርና የተደራጁ ወንጀሎች በዋነኝነት በመከላከል በዛሬው ዕለት የመግባቢያ ስምምነት ፈጽመዋል ።

የመግባቢያ ስምምነቱን በኢትዮጵያ በኩል የብሄራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ዳይሬክተር ጄነራል አቶ ተመስገን ጥሩነህ በኬንያ በኩል ደግሞ የኬንያ ብሄራዊ መረጃ አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ሜጀር ጀነራል ፍሊፕ ካሙሩ ፈርመውታል ።

የብሄራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ዳይሬክተር ጀነራል አቶ ተመስገን ጥሩነህ በፊርማ ስነ ሥርዓቱ ወቅት እንደገለጹት ኢትዮጵያ በምስራቅ አፍሪካም ሆነ በአፍሪካ ቀንድ የሽብርተኝነትና ተያያዥ የፀጥታና ደህንነት ችግሮች በተቀናጀ ሁኔታ ለመከላከል ከአብዛኛው የአፍሪካ ሀገራት ጋር የትብብር ስምምነት መፈጸሟን ጠቁመው እነዚህ የሀገራት ትብብሮች በማጠናከር በክፍለ አህጉሩ ሰላምና ደህንነትን ማረጋገጥ እንደሚቻል ተናግረዋል ።

በኬንያ ብሄራዊ መረጃ አገልግሎት የልዑካን ቡድን መሪ ሰይፍ ሳሊም ሱሌይማን በበኩላቸው ሽብርተኝነት ፣ህገ ወጥ የጦር መሣሪያዎች፣ የገንዘብና የሰዎች ዝውውር እንዲሁም የተደራጁ ወንጀሎች ለምስራቅ አፍሪካ ስጋት በመሆናቸው እነዚህን የቀጠናው ችግሮች ተባበሮና ተቀናጅቶ ለመመከት ከኢትዮጵያ ጋር አብሮ መሥራት እንደሚያስፈልግ አመልክተዋል።

የብሄራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎትም ከኬንያ ብሄራዊ መረጃ አገልግሎት ጋር በመሆን አካባቢያዊ ስጋት የሆኑትን ሽብርተኝነት፣ ህገ ወጥ የጦር መሣሪያዎች ዝውውርን ፣ ህገ ወጥ የፋይናንስ ዝውውርን ፣ ህገ ወጥ ታጣቂዎችን፣ ህገ ወጥ የሰዎች ዝውውር፣ ድንበር ዘለል የተደራጁ ወንጀሎችና ስጋቶችን በጋራ ለመከላከል የሚያስችል የትብብር ስምምነት ሰነድ ውስጥ የተካተቱ ነጥቦች ናቸው ።

በሰይፍ ሳሊም ሱሌይማን የተመራው የኬንያ ብሄራዊ መረጃ አገልግሎት የልዑካን ቡድን ከትናንት ጀምሮ በኢንፎርሜሽን መረብ ደኅንነት አስተዳደር ፣ አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩትና ሳይንስ ሙዚየምንና የብሄራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ተቋማትን በዛሬው ዕለት ጉብኝቷል ።

ኢትዮጵያና ኬንያ ወዳጅነት ያላቸው ሁለት የጎረቤት ሀገራት ሲሆኑ ለረጅም ጊዜ በፖለቲካው ፣ ኢኮኖሚውና ማህበራዊ ዘርፎች መልካም የሚባል ግንኙነት አላቸው ።

Exit mobile version