Site icon ETHIO12.COM

ዘመን ተሻጋሪ አኩሪ ታሪክ ሠሪ ፅኑ ኃይል

መቼም፣ የትም ፣በምንም ሁኔታ የማንዘነጋው በደም የታተመ የአበው አደራ ስላለብን እንጂ የጦርነትን አስከፊነት ስላማናውቅ አይደለም። ጦርነት መነሻ ምክንያቱ ብዙ ቢሆንም ውጤት ኪሣራና ውድቀት መሆኑን ጠንቅቀን እናውቃለን።

በአብዛኛው ታሪካችን ከጦርነት ጋር የተሳሰረ መሆኑ ከመቅደም ይልቅ ወደኋላ እንድንቀር አስገድዶናል። እንሳሳትን ቀድመን ያላመድን ፣ አርሶ መብላትን ለዓለም ህዝቦች ያስተማርን ቀደምት የስልጠኔ ፊት አውራሪዎች እኛ እስከ ቅርብ ጊዜ እርዳታ ጠባቂ ሆነን ቆይተናል። የምንዋጋው ሠላማችንን አጥብቀን ስለምንፈልግ፣ የመለወጥ ፍላጎታችንን ለማሳካት ካለን ፅኑ ፍላጎት ነው።ሁሌም ነፍጥ የምናነሳው ያሳጡንን ሠላም ለመመለስ ለማረጋገጥ ስንል ነው።

ኢትዮጵያውያን ጦርነትን የሚመርጡት የሀገራዊ ክብርና ሉዓላዊነት ጉዳይ ሲሆንባቸው ብቻ ነው። ኢትዮጵያዊያን ደማቸውን አፍስሰው፣ ሥጋቸውን ቆርሰው፣ አጥንታቸውን ከስክሰው፣ ህይወት ገብረው ሀገር ያፀኑት ለነፃነታቸው ነው።

በነፃነት ውስጥ የአእምሮ ሠላም፣ የምድር ልምላሜ ፣የራስን ጉዳይ በራስ የመወሰን ድፍረትና ስነልቦና አለ።ሳይነኩን ነክተን አናውቅም። ሲነኩን አብረን፣ ተባብረን፣ መሠናክሉን ሁሉ በአንድነት ተሻግረን ያሳጡንን ሠላም እንመልሳለን ።

የሰውን የማንፈልግ የራሳችንም የማንሰጥ ስለመሆናችን የአድዋና ካራማራ ትዝታዎች ምስክሮቻችን ናቸው። ከምንም በላይ ኢትዮጵያ አትፈርስም ያለው የአባት እናቶችን አደራ የመቀበል ዕድል ያደለው ይሄ ትውልድ ታሪክ ሰሚ ብቻ ሳይሆን ገድል ፈፃሚ መሆኑን አረጋግጧል።

ጥንትም ሆነ አሁን ዛሬም ሆነ ነገ የምንዋጋው ለሀገራችን ክብር ፣ ለሠማይና ምድራችን ቸር ውሎ ማዳር ለህዝባችን ያለምንም ስጋት ወጥቶ መግባት፣ አርሶ መብላት ተምሮ መለወጥ ተመራምሮ መላቅ በአጠቃላይ ለሠላማችን ነው።

ድል ያጠናክራል። ድል ያኮራል። ድል ያሻግራል። ድል የመደራደር አቅም ይፈጥራል። ድል የሀገርን ክብር ያረጋግጣል። ለቅርብም ሆነ ለሩቅ ጠላት ትምህርት ይሰጣል ።የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊትም የዚሁ ድል ባለቤት ነው።

ስለሠላም ሲነገር፣ ስለመተባበር እና አንድነት ሲተረክ፣ ለዘላቂ ሀገራዊ ህልውና ሲሠራ ፣ፍሬ ሲያፈራ ፣ሠራዊታችን ክብሩ ከፍ ይላል። ህዝባዊ ፍቅሩ ያይላል።
ህዝብ ነው ሃያል ክንዳችን
ሠላም ልማት ነው ቋንቋችን
የመፈቃቀድ አንድነት
እኩልነት ነው ዜማችን
ብሎ የዘመረ ፣ቃሉን የተገበረ፣ ሀገረ ያሸገረ ነው መከላከያ ሠራዊታችን። የግዮን እናት ጋሻና መከታ፣ የሠው ልጅ መገኛ የነፃነት ተምሳሌት፣ የጥቁሮች እንቁ፣ የወራሪዎች እራስ ምተት የሆነች ታላቅ ሀገር የሚያስመካ ወታደር ነው ሠራዊታችን።

የመከላከያ ሠራዊታችን ሠላም ከሠፈነ፣ ልማት ከተረጋገጠ ፣የመፈቃቀድ አንድነታችን ሥር ከሠደደ፣ ራዕዩ እውን ሆነ ፣ተልዕኮው ተሳካ ግቡ ላይ ደረሰ የልቡ ሞላ ዘላለማዊ ሐውልት ተከለ ማለት ነው።

ውክልናችን የኢትዮጵያ ህዝቦች ፣ሥራችን የውዲቷ ሀገራችን ዘቦች ፣ህልማችን ያደገች ምድር ፣የተዋበ ህብር የሚያስቀና ፍቅር ነው ያለው የታላቋ ሀገር ትልቅ ተቋም ትላንት ተዓምር ሠርቷል። ወገኑን አኩርቷል። ነገም ዘመን ተሻጋሪ ሆኖ ዘመን ተሻጋሪ ገድሎችን እየፈፀመ ይቀጥላል።

ፈይሳ ናኔቻ

Exit mobile version