Site icon ETHIO12.COM

ሱዳንና ኢትዮጵያ በደህንነት ዙሪያ አብሮ ለመስራት ውል አሰሩ

የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎትና የሱዳን ጠቅላላ የደህንነት አገልግሎት በጋራ ለመስራት የሚስችላቸውን ስምምነት ተፈራረሙ

በብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ዳይሬክተር ጀነራል ተመስገን ጥሩነህ የተመራ ልዑክ ከሱዳን ጠቅላላ የደህንነት አገልግሎት ዳይሬክተር ጀነራል አህመድ ኢብራሂም አሊ ሙፍዲል እና ሌሎች ከፍተኛ የተቋሙ አመራሮች ጋር በመረጃና ደህንነት ጉዳዮች ዙሪያ በካርቱም መክረዋል።

ኹለቱ የመረጃና ደህንነት ተቋማት ግንኙነታቸውን አጠናክረው በጋራ መስራት ለኹለቱ ጎረቤት አገራት እና ህዝቦች ሰላምና ደህንነት መረጋገጥ ስለሚኖረው ጉልህ አስተዋጾ በጥልቀት መምከራቸው ተገልጿል።

ከውይይቱ በኋላም ኹለቱ ተቋማት የጋራ በሆኑ ጉዳዮች ላይ መረጃ ለመለዋወጥና በጋራ ለመስራት የሚያስችላቸውን  የመግባቢያ ስምምነት መፈራረማቸው ተነግሯል።

የስምምነቱ ትኩረት ተቋማቱ በጋራ በሆኑ ጉዳዮች ላይ የተሞክሮ እና መረጃ ለመለዋወጥ፣ የቀጠናው የጋራ ስጋት የሆነውን ሽብርተኝነት በጋራ መዋጋት፣ ድንበር ተሻጋሪ ወንጀሎችን በጋራ መከላከል፣ የኹለቱ አገራት ዜጎች በሰላም የመኖርና የመንቀሳቀስ ደህንነትን ማረጋገጥ እና የኹለቱን አገራት ህዝቦች ሰላም የሚጎዱ አካላትን በጋራ መከላከል ላይ በትብብር ለመስራት ከስምምነት ላይ መድረሳቸው ነው የተገለጸው።

በተጨማሪም በተመስገን ጥሩነህ የሚመራው የልዑካን ቡድኑ በካርቱም ለኹለት ቀናት በነበረው ይፋዊ የሥራ ጉብኝት ከሱዳን ሉአላዊ ምክር ቤት ሊቀመንበር አብዱል ፈታ አልቡራሃንና ከሉአላዊ ምክር ቤቱ ምክትል ሊቀመንበር ሞሐመድ  አምዳን ዳጋሎ ጋር ተገናኝተው፤ በኹለቱ አገራት ሰላምና ደህንነት ዙሪያ መወያዩቱን አገልግሎት መስሪያ ቤቱ ለመገናኛ ብዙሃን በላከው መረጃ አመላክቷል ሲል አዲስ ማለዳ አስነብቧል።

Exit mobile version