Site icon ETHIO12.COM

“የዘር ማጥፋት፣ የሰላም ስምምነት ማፍረስና የጦርነት ወንጀሎች”በወታደራዊ ፍ.ቤት ለመዳኘት ረቂቅ ህግ ፓርላማ ቀረበ

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሀገር መከላከያ ሠራዊት አዋጅን ለማሻሻል የቀረበውን ረቂቅ አዋጅ ጨምሮ በሌሎች ጉዳዮች ላይ በመወያየት ለዝርዝር ዕይታ ለሚመለከታቸው ቋሚ ኮሚቴዎች መርቷል። በመደበኛ ስብሰባው የምክር ቤቱን 2ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 3ኛ እና 4ኛ መደበኛ ስብሰባ ቃለ-ጉባዔዎችን በመመርመርም በሙሉ ድምጽ አፅድቋል።

ምክር ቤቱ በዛሬው ውሎው በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ የገቢዎች ሚኒስትር ሆነው ቀደም ብለው የተሾሙትን ወይዘሮ ዓይናለም ንጉሴ ሹመትም በሙሉ ድምጽ አፅድቋል። የመከላከያ ሠራዊት አዋጅን ለማሻሻል የቀረበውን በውሳኔ ረቂቅ አዋጅ ቁጥር 09/2015 ዓ.ም በመመርመር ለዝርዝር ዕይታ ለውጭ ግንኙነትና ሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ መርቶታል።

የሕዝብ እንባ ጠባቂ ተቋምን እንደገና ለማቋቋም የወጣውን አዋጅ ለማሻሻል የቀረበውን ረቂቅ አዋጅ ቁጥር 8/2015 ዓ.ም መርምሮ ለዝርዝር ዕይታ ለሕግ፣ ፍትሕ እና ዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ መርቷል።

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ-ጉባዔ ታገሰ ጫፎ፤ የኢትዮጵያ ሕዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም አዋጅን ለማሻሻል የቀረበውን ረቂቅ አዋጅ አስመልክቶ ማብራሪያ ሰጥተዋል።

በማብራሪያቸውም የዜጎች መብት መከበሩን፣ የሕግ የበላይነትን መሠረት ያደረገ መልካም የመንግሥት አስተዳደርን ለማስፈን የተቋሙን የአሰራርና የሕግ ክፍተት መፈተሽ አስፈላጊ እንደሆነ ተናግረዋል።

ሥራ ላይ የሚገኘውን አዋጅ ቁጥር 1142/2011 በማሻሻል የተቋሙን ኃላፊዎችና አደረጃጀት በማጠናከር ስኬታማ ሥራ እንዲያከናውን ለማድረግ አዋጁን ማሻሻል እንዳስፈለገ አብራርተዋል።

በምክር ቤቱ የመንግሥት ቋሚ ተጠሪ ሚኒስትር ተስፋዬ በልጅጌ፤ የመከላከያ ሠራዊትን አዋጅ ለማሻሻል የቀረበውን ረቂቅ በተመለከተ ለምክር ቤት አባላት አቅርበዋል።

አገራዊ ለውጡን ተከትሎ የማሻሻያ እርምጃ ከተወሰደባቸው ተቋማት መካከል የመከላከያ ሠራዊት አንዱ መሆኑን ጠቅሰው፤ ሠራዊቱ አገራዊ ኃላፊነቱን በአስተማማኝ መልኩ እንዲወጣ የሕግ ማዕቀፎችን ማሻሻል አስፈላጊ መሆኑን አብራርተዋል።

ከዚህ በፊት አዋጁ ማሻሻያ እንደተደረገበት አስታውሰው፤ አሁንም ምላሽ የሚሹ ጉዳዮች በመኖራቸው ረቂቅ አዋጅ መዘጋጀቱን ጠቁመዋል።

የምክር ቤቱ አባላትም የቀረቡላቸውን የሹመት የውሳኔ ሃሳብ፣ የማሻሻያ ረቂቅ አዋጆች እና የፌደራል ዳኛ ስንብትን አስመልክቶ የተለያዩ ሃሳብና አስተያየቶችን በመስጠት በሙሉ ድምጽ ለየቋሚ ኮሚቴው መርተዋል።

ኢትዮጵያን በመስዋዕትነቱ እያጸና የሚገኘውን የሀገር መከላከያ ሠራዊት ተነሳሽነት ለማሳደግ በሚሻሻለው አዋጅ ውስጥ የሠራዊት ቀን እንዲካተትም ጠይቀዋል።

ሠራዊቱ የሚከፍለውን መስዋዕትነት በሚመጥን መልኩ በሥራ ላይም ሆኖ ከሥራ ሲሰናበት ክብሩን የሚመጥን ሃሳብ በአዋጁ መካተት እንዳለበትም አመላክተዋል።

በሌላ በኩል የፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ዳኛ የነበሩት ፋንታሁን ደለለ ሽፈራው፤ በቀረበባቸው የዲሲፕሊን ግድፈት የስንብት የውሳኔ ሃሳብ ላይ ምክር ቤቱ ተወያይቶ ለሕግ፣ ፍትሕና ዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ መርቷል። አዲስ ዘመን ብያብራራውም ኢትዮ ኢንሳይደር ከቀን በፊት ዜናውን በዚህ መልኩ አቅርቦታል። ከስር ያንብቡ

በሃሚድ አወል

በመከላከያ ሠራዊት ስር ያሉ ወታደራዊ ፍርድ ቤቶች፤ የዘር ማጥፋት፣ የጦርነት ማቆም ወይም የሰላም ስምምነት ውልን ማፍረስ እና በሰላማዊ ህዝብ ላይ የሚፈጸሙ የጦርነት ወንጀሎችን እንዲመለከቱ የዳኝነት ስልጣን የሚሰጥ የአዋጅ ረቂቅ ለፓርላማ ሊቀርብ ነው። ወታደራዊ ፍርድ ቤቶቹ፤ በጦርነት ጊዜ የሚደረግ ገፈፋ እና ዘረፋ፣ ለጠላት ሊደረግ የሚገባውን ተግባር መጣስ እንዲሁም በዕርቅ መልዕክተኛ ላይ የጠላትነት ድርጊት መፈጸምን የተመለከቱ ወንጀሎችን የመዳኘት ስልጣን በአዋጅ ረቂቁ ተሰጥቷቸዋል። 

ከዚህ ቀደም በመደበኛ ፍርድ ቤት ይታዩ የነበሩ እነዚህን የዳኝነት ስልጣኖች ወታደራዊ ፍርድ ቤቶቹም እንዲመለከቱ ስልጣን የሰጣቸው፤ በአራት ዓመታት ጊዜ ለሶስተኛ ጊዜ የተሻሻለው የመከላከያ ሠራዊት አዋጅ ነው። ከሳምንት በፊት ህዳር 3፤ 2015 ለሚኒስትሮች ምክር ቤት የቀረበው አዲሱ የመከላከያ ሠራዊት አዋጅ፤ “ሰፊ ውይይት” ከተደረገበት እና ግብዓቶች ከታከሉበት በኋላ፤ በፓርላማ ይጸድቅ ዘንድ “በሙሉ ድምጽ” መወሰኑን የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት አስታውቆ ነበር።

በ2011 ዓ.ም የወጣውን የመከላከያ ሠራዊት አዋጅ የሚሽረው፤ አዲሱ የአዋጅ ረቂቅ በስድስት ክፍሎች እና በ88 አንቀጾች የተዘጋጀ ነው። “ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” በተመለከተችው እና በነገው ዕለት ለፓርላማ ይቀርባል በተባለው በዚህ አዋጅ ከተሻሻሉ ጉዳዮች ውስጥ፤ የወታደራዊ ፍርድ ቤት የዳኝነት ስልጣን የተመለከተው ይገኝበታል። በመከላከያ ሠራዊት ስር ያሉ ወታደራዊ ፍርድ ቤቶች፤ “ቀዳሚ” እና “ይግባኝ ሰሚ” የተሰኙ ደረጃዎች አሏቸው።  

በአዲሱ አዋጅ፤ በመደበኛው የወንጀል ህግ የተደነገጉ እና ቀዳሚ የወታደራዊ ፍርድ ቤት የሚመለከታቸው ወንጀሎች ብዛት ከዚህ ቀደም ከነበረው ከፍ ብሏል። አሁን በስራ ላይ ባለው አዋጅ፤ የቀዳሚ ወታደራዊ ፍርድ ቤት የዳኝነት ስልጣን በወንጀል ህጉ የተነደገጉ “ወታደራዊ ወንጀሎችን” በማየት የተገደበ ነበር። ለፓርላማ በተላከው የአዋጅ ረቂቅ፤ በመደበኛው የወንጀል ህግ ያሉ ተጨማሪ 15 አንቀጾች፤ በቀዳሚ ወታደራዊ ፍርድ ቤት የዳኝነት ስልጣን ላይ እንዲያርፉ ተደርገዋል።

ዓለም አቀፍ ህጎችን በመጣስ የሚፈጸሙ እንደ ዘር ማጥፋት፣ በሰላማዊ ህዝብ ላይ የሚፈጸም የጦርነት ወንጀል እንዲሁም የጦርነት ማቆም ውልን ወይም የሰላም ስምምነትን ማፍረስ የተመለከቱ ወንጀሎች፤ ቀዳሚ ወታደራዊ ፍርድ ቤት የመዳኘት ስልጣን እንዳለው በአዲሱ አዋጅ ሰፍሯል። በጦርነት ጊዜ የሚደረግ ገፈፋ፣ ዘረፋ እና የባህር ወንብድና፤ በቁስለኞች፣ በበሽተኞች ወይም በጤና አገልግሎት ላይ እንዲሁም በታሰሩ የጦር ምርኮኞች እና በተጋዙ ሰዎች ላይ የሚፈጸሙ የጦርነት ወንጀሎችም፤ በቀዳሚ ወታደራዊ ፍርድ ቤቱ እንደሚታዩ በአዋጅ ረቂቁ ላይ ተቀምጧል።

ከዚህ በተጨማሪም የቀዳሚ ወታደራዊ ፍርድ ቤቱ፤ ለጠላት ሊደረግ የሚገባውን ተግባር መጣስ፣ በዕርቅ መልዕክተኛ ላይ የጠላትነት ድርጊት መፈጸምን እንዲሁም በዓለም አቀፍ ሰብዓዊ ድርጅቶች ላይ የሚፈጸሙ ወንጀሎችን የመመልከት ስልጣን በአዋጅ ረቂቁ ተሰጥቶታል። የቀዳሚ ወታደራዊ ፍርድ ቤቱ በመደበኛ ወንጀል ህጉ ላይ የተካተቱ፤ በሰራዊት አባላት መካከል የሚፈጸሙ የግድያ እና የአስገድዶ መድፈር ወንጀሎችን የመዳኘት ስልጣን እንደሚኖረውም በአዋጅ ረቂቁ ተደነግጓል።

በወታደራዊ እና በመደበኛ ፍርድ ቤቶች ስልጣን ስር የሚታዩ ክሶች በአንድ ተከሳሽ ላይ በሚቀርቡበት ጊዜ፤ የመዳኘት ስልጣን ያለውን አካል በተመለከተ የአዋጅ ረቂቁ ማሻሻያ አድርጓል። እንዲህ አይነት ክስተት በሚያጋጥም ጊዜ፤ ሁሉም ክሶች “ከባድ ቅጣት የሚስከትለውን ወንጀል የማየት ስልጣን ወዳለው ፍርድ ቤት” እንደሚቀርቡ አሁን በስራ ላይ ያለው አዋጅ ይደነግጋል። አዲሱ የአዋጅ ረቂቅ ግን “አንድ ተከሳሽ ከቀረቡበት ክሶች መካከል ከፊሉ በወታደራዊ ፍርድ ቤት የዳኝነት ስልጣን ስር፤ ከፊሉ ደግሞ በመደበኛ ፍርድ ቤት የዳኝነት ስልጣን ስር የሚወድቅ ከሆነ፤ ሁሉም ክሶች በወታደራዊ ፍርድ ቤት ተጠቃለው ይታያሉ” ሲል ያትታል።

አዲሱ የመከላከያ ሠራዊት አዋጅ፤ የቀዳሚ ወታደራዊ ፍርድ ቤት ዳኞች አሿሿም ላይም ማሻሻያ አድርጓል። በአዲሱ አዋጅ መሰረት የቀዳሚ ወታደራዊ ፍርድ ቤት ዳኞች የሚሾሙት በመከላከያ ሚኒስትሩ ነው። በ2011 ዓ.ም. የወጣው የመከላከያ ሠራዊት አዋጅ፤ የወታደራዊ ፍርድ ቤቱ ዳኞች ሹመት የሚሰጠው “በመከላከያ አዛዦች ምክር ቤት ነው” ይላል። የመከላከያ አዛዦች ምክር ቤት በጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኤታማዦር ሹሙ የሚመራ ሲሆን ስድስት አባላት ያሉት ነው። 

ይህ ምክር ቤት በአዋጁ ከተሰጡት ስልጣን እና ተግባራት መካከል፤ “በሠራዊቱ የበጀት ድልድል ላይ ሃሳብ” ማቅረብ የሚለው ይገኝበታል። አዲሱ አዋጅ ከዚህ ቀደም ለምክር ቤቱ ተሰጥቶት የነበረው “የትጥቅ ግዢዎች ፍላጎት የውሳኔ ሃሳብ የማቅረብ” ስልጣንን ሳያካትት ቀርቷል። በአዋጅ ረቂቁ “ስለ ግዢ እና ንብረት አስተዳደር” የሰፈረው አንቀጽ፤ የመከላከያ ሚኒስቴር “ከአገር ደህንነት አንጻር ወታደራዊ ሚስጥርነት ያላቸው ግዢዎችን፤ የፌደራል መንግስት የግዢ ህግጋትን ሳይከተል ሊፈጽም ይችላል” ይላል። 

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ወደ ስልጣን ከመጡ ወዲህ ለሶስተኛ ጊዜ ለውጥ የተደረገበት የመከላከያ ሠራዊት አዋጅ፤ የውትድርና ማዕረግ እና የጡረታ መውጫ ጊዜ ማራዘምን በተመለከቱ አንቀጾች ላይ ማሻሻያ አድርጓል። አዲሱ አዋጅ የቃላት ትርጓሜዎችን በዘረዘረበት ክፍሉ፤ የ“ፊልድ ማርሻል” ወታደራዊ ማዕረግ ምንነት አስቀምጧል። የ“ፊልድ ማርሻል” ማዕረግ “አገርን ከከፍተኛ የደህንነት ስጋት ለማውጣት ለሚፈጸም ከፍተኛ የውትድርና አመራር ብቃት” በሀገሪቷ ርዕሰ ብሔር “በልዩ ሁኔታ” የሚሰጥ መሆኑ በአዲሱ አዋጅ ሰፍሯል።

ኢትዮጵያ የ“ፊልድ ማርሻል” ወታደራዊ ማዕረግን ለመጀመሪያ ጊዜ የሰጠችው ከአንድ ዓመት ገደማ በፊት በታህሳስ 2014 ዓ.ም ነበር። በጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ አቅራቢነት በፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ ማዕረጉ የተሰጣቸው፤ የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኤታማዦር ሹሙ ብርሃኑ ጁላ ናቸው። ለኤታማዦር ሹሙ ማዕረጉ በተሰጠበት ወቅት፤ የማዕረግ ደረጃው “በመከላከያ ሠራዊት አዋጁ ውስጥ ያልተካተተ ነው” የሚል ክርክር ቀስቅሶ ነበር። 

ለዚህ ክርክር በማጣቀሻነት ሲቀርብ የነበረው በ2011 ዓ.ም የወጣው የመከላከያ ሠራዊት አዋጅ ነው። ይህ አዋጅ የወታደራዊ ማዕረግ ደረጃን በዘረዘረበት ክፍሉ፤ ከፍተኛው ወታደራዊ ማዕረግ “ጄነራል” መሆኑን አስፍሮ ነበር። የመከላከያ ሠራዊት በወቅቱ ባወጣው ማብራሪያ የፊልድ ማርሻሉ ሹመት ህጋዊ የሚሆነው፤ በ2013 በወጣ የአዋጅ ማሻሻያ መሰረት መሆኑን አስታውቆ ነበር። 

ይህ የማሻሻያ አዋጅ ያካተተው፤ “በዓለም አቀፍ ደረጃ በተለይም በአፍሪካ ተቀባይነት ያላቸውን የከፍተኛ መኮንን ማዕረጎችን፤ በልዩ ሁኔታ በጦር ኃይሎች ጠቅላይ አዛዥ አቅራቢነት በርዕሰ ብሔር ሊሰጥ ይችላል” የሚለው አዲስ ድንጋጌ የፊልድ ማርሻልን ሹመት የሚጨምር መሆኑ በወቅቱ ተገልጿል።

አዲሱ አዋጅ የ“ፊልድ ማርሻል” ወታደራዊ ማዕረግ ትርጓሜን ቢያስተዋውቅም፤ ከዚህ ቀደም እንደነበሩት አዋጆች የማዕረግ ደረጃዎችን አጠቃላይ ዝርዝር ከማስቀመጥ ተቆጥቧል። የምድር፣ የአየር እና የባህር ኃይል ወታደራዊ የማዕረግ ደረጃዎች ዝርዝር ወደፊት በደንብ እንደሚወሰን በአዋጅ ረቂቁ ላይ ተመላክቷል። የፊልድ ማርሻልን ጨምሮ የሌሎች የጦር አዛዦችን የጡረታ መውጫ ጊዜ በተመለከተ የተደረጉ ማሻሻያዎች ግን በአዋጁ ረቂቁ ተካትተዋል። 

በ2013 በተሻሻለው የመከላከያ ሠራዊት አዋጅ፤ ከጄነራል ማዕረግ በላይ ያሉ የጡረታ አዛዦች የጡረታ መውጫ ዕድሜ 60 መሆኑ ተቀምጧል። ይህ የጡረታ መውጫ ዕድሜ፤ ፊልድ ማርሻልን እንደሚጨምር በአዲሱ አዋጅ ሰፍሯል። ሆኖም የጡረታ መውጫ ጊዜው፤ በጦር ኃይሎች ጠቅላይ አዛዥ ውሳኔ መሰረት “ላልተወሰነ ጊዜ ሊራዘም” እንደሚችል የአዋጅ ረቂቁ ደንግጓል። 

የጦር ኃይሎች ጠቅላይ አዛዥ፤ ከመከላከያ ሰራዊት ኤታማዦር ሹም በተጨማሪ የምክትል ኤታማዦር ሹም እና የኃይል አዛዦችን የጡረታ መውጫ እድሜ የማራዘም ስልጣን እንዳላቸው በአዋጁ ሰፍሯል። ከእነዚህ ውጭ የሆኑትን የሰራዊት አባላት የጡረታ መውጫ እድሜ የማራዘም ስልጣን ያላቸው የሠራዊቱ ኤታማዦር ሹም መሆናቸውን አዲሱ አዋጅ አስቀምጧል።   

አዲሱ የመከላከያ ሠራዊት አዋጅ ማሻሻያ ያደረገበት ሌላው ጉዳይ፤ ለሠራዊት አባላት የሚደረግ ማበረታቻ ነው። ሰላሳ ዓመት እና ከዚያ በላይ ያገለገሉ የሠራዊት አባላት፤ ከቀረጥ እና ግብር ነጻ የሆነ አንድ መኪና መግዛት እንደሚችሉ በአዋጅ ረቂቁ ተፈቅዶላቸዋል። በስራ ላይ ባለው አዋጅ ይህ መብት የተሰጠው፤ ከጀኔራል መኮንን በላይ ማዕረግ ኖሯቸው ከ20 ዓመት በላይ ላገለገሉ እና በቀላሉ የማይተካ ልዩ ክህሎት ላላቸውና ከሰባት ዓመት በላይ ላገለገሉ የሠራዊት አባላት ነበር።

የመከላከያ ሠራዊት የመኖሪያ ቤት መስሪያ ቦታ ለማግኘት ይጠበቅባቸው የነበረው የ15 ዓመት እና ከዚያ በላይ የውትድርና አገልግሎት፤ በአዲሱ አዋጅ ወደ 30 ዓመት እና ከዚያ በላይ ከፍ ብሏል። የተጠቀሰውን ያህል ዓመት ያገለገሉ የሠራዊት አባላት፤በተወለዱባቸው የክልል ከተሞች ውስጥ የግል የመኖሪያ ቤት መስሪያ ቦታ እንዲያገኙ መንግስት ድጋፍ እንደሚያደርግ በአዋጁ ተቀምጧል። የሠራዊት አባላቱ በማህበር ተደራጅተው የመኖሪያ ቤት መገንባት እንዲችሉ መንግስት የገንዘብ ድጎማ እንደሚያደርግም በአዋጁ ተደንግጓል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)

Exit mobile version