ETHIO12.COM

ኳታር ለዓለም ዋንጫ የኮንቴነሩ ስታዲየም

ዛሬ ከምሽቱ 1 ሰአት በምድብ አራት ሜክሲኮ ከፖላንድ የሚያደርጉትን ጨምሮ ሰባት የዓለም ዋንጫ ጨዋታዎችን የሚያስተናግደው 974 ስቴድየምን አለማድነቅ አይቻልም።

ኳታር ለዓለም ዋንጫ ጨዋታዎች ካሰናዳቻቸው ስምንት ስታዲየሞች ሰባቱ አዲስ የተገነቡ ናቸው።

ከእነዚህ አዲስ ስታዲየሞች መካከል ደግሞ 974 የተሰኘው ስታዲየም በአይነቱ ልዩ የሆነ አዲስ የፈጠራ ውጤትና ድንቅ የግንባታ ጥበብን ለአለም በማስተዋወቁ በርካቶችን ያነጋገረ ነው።

ስያሜያውን ያገኘው ድጋሚ ጥቅም ላይ ከዋሉ 974 የመርከብ ዕቃ ማጓጓዣ ኮንቴነሮች የተሰራ በመሆኑ ነው።

ለስያሜው ምክኒያት ኳታር ለረጅም ዘመናት በባህር ላይ ያላትን አለም አቀፍ የንግድ እንቅስቃሴ ለማመልከትም ጭምር የሚውል ነው። በተጨማሪም የኳታር የስልክ መለያ ቁጥር የሚጀመረው +974 ከመሆኑ ጋር የተሳሰረ ነው።

የስታዲየሙ ንድፈ ሀሳብ የተዘጋጀው ‘ፌንዊክ ኢሪባረን አርክቴክት’ በተባለ የሕንጻ ዲዛይን ድርጅት ሲሆን፣ የተወሰኑት ኮንቴነሮች የፋይናንስ አገልግሎት መስጫዎችና መኪና ማቆሚያ አሏቸው።

በዚህ ስታዲየም ጨዋታዎችን የሚከታተሉ ተመልካቾች ከአረብ ባህር የሚነፍሰውን ቀዝቃዛ አየር እየተቀበሉ ዘና እንደሚሉም ይጠበቃል።

የስቴድየሙ ግንባታ እኤአ በ2018 ተጀምሮ በ2021 ነው የተጠናቀቀው።

ለስታዲየሙ ግንባታ ዋነኛ ግብአት የሆነው የመርከብ እቃ ማጓጓዣ ኮንቴነሮችና መቀመጫዎች ዓለም ዋንጫው ከተጠናቀቀ በኋላ ለሌሎች አገራት ለመሸጥና በእርዳታ ለመስጠት ታስቧል።

974 ስታዲየም በፊፋ ዓለም ዋንጫ ታሪክ የመጀመሪያው ጊዜያዊ ስታዲየም ነው። ስቴድየሙ ከማእከላዊ ዶሃ በስተምስራቅ አስር ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ይገኛል።

ከአለም ዋንጫው በኋላ በቀላሉ ተነቃቅሎ መልሶ መገጣጠም ይችላል። ኳታር ግን ከአለም ዋንጫው በኋላ ይህን ስታዲየም አትፈልገውም። የተገነባበትን ስፍራ አስደናቂ የሕዝብ መዝናኛና የንግድ ቦታ ልታደርገው አስባለች።

የስታዲየሙ ግንባታ ዓላማ ውስን ግብአቶችን በመጠቀም በዝቅተኛ ወጪ እንዲሁም ብክለትና ወደ ከባቢ አየር የሚለቀቁ ጋዞችን መቀነስ መሆኑን ለማሳየት ጭምር ነው።

44 ሺህ 89 ተመልካቾችን የመያዝ አቅም ያለውን ይህን ድንቅ ስታዲየም ለመገንባት ኳታር ምን ያህል መዋእለ ንዋይ እንዳፈሰሰች የሚገልጽ ትክክለኛ መረዳ የለም።

በቦጋለ አበበ (ኢ.ፕ.ድ)

Exit mobile version