Site icon ETHIO12.COM

‘ፓትሪዮት’ አሜሪካ ለዩክሬን የምትሰጣት ብዙ የተነገረለት አየር መቃወሚያ  

ፕሬዝዳንት ዜሌንስኪ ምዕራባዊያንን አጥብቀው ሲጠይቁ የነበረው አንድ ነገር የአየር መቃወሚያ እንዲሰጣቸው ነበር። ምክንያቱም ሩሲያ በአየር ኃይሏ ኪዬቭን ጨምሮ ዋና ዋና ከተሞችን በጨለማ እንዲዋጡ አድርጋለች። በካሚካዚ ድሮንና በተወንጫፊ ሚሳኤሎች ብዙ ጥፋት አድርሳለች።

ውሃና መብራት ለሚሊዮኖች ቅንጦት ሆኖ እንዲሰማቸው ሆኗል። ዩክሬናውያን የውርጩን ዘመን ያለማሞቅያ በብርድ እየተንዘፈዘፉ እንዲኖሩ ተደርገዋል።

በዩክሬን ብዙ ከተሞች መብራት በፈረቃ ነው የሚከፋፈለው። ከዚህም የከፋ ጉዳት እንዳይደርስ በዩክሬን ሰማይ ላይ የሚፈነጩትን ድሮኖችና ሚሳኤሎች ጭጭ ማድረግ አስፈላጊ ሆኗል። አንድ ነገር መደረግ ነበረበት። ዜሌንስኪ ምዕራባዊያን ድረሱልን አሉ። ይነስም ይብዛ ደርሰውላቸዋል።

ይሁንና እስከዛሬ የደረሳቸው የአየር መቃወሚያ ዘመናዊ ቢሆንም ከሩሲያ አቅም አንጻር ሲታይ የልብ አያደርስም። 

ፕሬዝዳንት ዜሌንስኪ ወደ አሜሪካ ማማተር ጀመሩ። ጆ ባይደን አላሳፈሯቸውም።

ባይደን ለዜሌንስኪ አንድ ያረጋገጡላቸው ነገር ቢኖር ከሰሞኑ እጅግ የላቁ ናቸው የሚባሉትን የአየር መቃወሚያዎች እንደሚልኩላቸው ነው። ፓትሪዮት ይባላል ስማቸው።

ይህ እርዳታ አሜሪካ ለዩክሬን 66 ቢሊዮን ዶላር ከለገሰች በኋላ የመጣ ትልቁ ስጦታ ሆኗል። ፓትሪዮት የአየር መቃወሚያዎች ውድ፣ በጣም ውጤታማ እና የልብ አድርስ ናቸው ይባላል። አንድ ፓትሪዮት ሚሳኤል ዋጋው ይጠራ ከተባለ ዋጋው 3 ሚሊዮን ዶላር ይደርሳል።

 ይህ ማለት በምሕጻረ ቃል ኤንኤኤምኤስ (NASAMS) የሚባሉትን ዘመናዊ የአየር መቃወሚያዎች በሦስት እጥፍ በዋጋ ይበልጣቸዋል።

ፓትሪዮት ሚሳኤሎች የተሠሩት በኢራቅ ጦርነት ጊዜ ነበር፤ የሩሲያ ሠራሽ ሚሳኤሎችን ለመቃወም። ይህም እንደ አውሮፓዊያኑ በ1980ዎቹ መጀመርያ ማለት ነው። ነገር ግን ከዚያ ወዲህ ብዙ ማሻሻያዎች ተደርገውለት አሁን ወደደረሰበት ወደ ላቀ ደረጃ ደርሷል።

ብዙ ያደጉ አገሮች አየር ክልላቸውን የሚጠብቁት በዚህ የአየር መቃወሚያ ነው።

በቀላሉ ከቦታ ቦታ ማንቀሳቀስ ይቻላል። በአንድ ጊዜ በርካታ የአየር ጥቃቶችን መመከት ይችላል።

የኤሌክትሮኒክ የግንኙነት እቀባ (ጃሚንግ) ቢሰነዘርበት ራሱ ይህን መመከት የሚያስችል መሣሪያ ተገጥሞለታል።

24 ሰዓት የራዳር ቅኝት ያደርጋል። 

ፓትሪዮት የአየር መቃወሚያዎችን ለመጠቀም የራዳር ጣቢያ፣ የዕዝ ጣቢያና ማስወንጨፊያ ማማ ያስፈልጋሉ።

ከ40-160 ኪሎ ሜትር የጠላት ዒላማን ተምዘግዝገው ማደባየት ይችላሉ። 

በዋናነት አገልግሎታቸው የዋርዲያ ነው። ጥበቃ የማድረግ። ከተማን፣ ወይም አንድ አካባቢን፣ ወይም አንድ ግዙፍ መሠረተ ልማትን ከየትኛውም ዓይነት የአየር ጥቃት መጠበቅ።

አሜሪካዊያን ወይም የኔቶ አባል አገራት ዩክሬን ገብተው እነዚህን መሣሪያዎች መጠቀም አይችሉም።

ስለዚህ ዩክሬናዊያን ለዚሁ ፓትሪዮት የአየር መቃወሚያ ሚሳኤል ሲባል ልዩ ስልጠና መውሰድ ነበረባቸው። አሜሪካ በጀርመን ባላት የጦር ሰፈር ይህንኑ ሥልጠና ለተመረጡ ዩክሬናዊያን ሰጥታቸዋለች ተብሏል።

ዛሬ ሐሙስ ሞስኮ ባወጣችው መግለጫ ፓትሪዮት የአየር መቃወሚያን ለዩክሬን ማስታጠቅ “የምዕራባዊያን ጠብ አጫሪነት” መቀጠሉን ማሳያ ነው ስትል ድርጊቱን አውግዛለች።

ከዛሬ ጀምሮ እነዚህ መሣሪያዎች ዋንኛ ዒላማዋ እንደሚሆኑም ዝታለች።

የጦር ባለሙያዎች ይህን ፓትሪዮት የአየር መቃወሚያ ለዩክሬን ከተሰጡ ስጦታዎች ትልቁ ብለው ያወድሱታል።

ምክንያት ሲጠቅሱም በተለይ ኼርሶን ከተማን የዩክሬን ወታደሮች ከሩሲያ ወታደሮች ከነጠቁ በኋላ የዩክሬን ሰማይ ክፍት ሆኖ መቆየቱን ያወሳሉ።

በዚህ የተነሳ ቁልፍ መሠረተ ልማቶች ክፉኛ ውድመት ሲደርስባቸው ቆይቷል። የዕለት ተዕለት ኑሮ በዩክሬን ፈተና የሆነውም ለዚሁ ነው።

ይህም ሊሆን የቻለው የሩሲያ ሚሳኤሎችንና ድሮኖችን ማቆም የሚችል ቴክኖሎጂ በመጥፋቱ ነበር።

አሁን ፓትሪዮት እንደ ስሙ አርበኝነቱን ያሳይ ይሆናል።

Addis zena news

Exit mobile version