ETHIO12.COM

ትህነግ መንግስትንና “ወራሪ ሃይል” ያለውን አማራን ከሰሰ፤ መንግስት ማስጠንቀቂያ ሰጥቷል

በሰላም ስምምነቱ መሰረት መጠሪያ ስሙን እንደሚያስተካክል ትህነግ ቢፈርምም አሁንም “የትግራይ መንግስት” በሚል የድርጅቱ ልሳን ባተመው ዜና መንግስት የሰላም ስምምነቱን እንዳላከበረ አስታውቋል። የአማራን ህዝብ እንደቀድሞው “ወራሪ ሃይል” ሲል ጠርቶ ክልሉን ለቀው እንዲወጡ አለመደረጉን አመልክቷል። መንግስት በበኩሉ ትህነግን ሳይጠራ አስፈላጊ የተባለውን እርምጃ ለመውሰድ እንደሚችል አስጠንቅቋል።

የሰላም ስምምነቱን በማክበር ሰራዊቱን ከአራት ግንባር ማንሳቱን ያስታወቀው የትህነግ የፊስቡክ ገጽ ዜና፣ ከመንግስት በኩል መደረግ የሚገባው ግን እንዳልተደረገ ገልጿል። “… በሰላም ስምምነት ውል መሰረት የኤርትራ ሰራዊት እና የአማራ ታጣቂዎች በወረራ ከያዙት የትግራይ መሬት ለቀው ሊወጡ ሲገባ አሁንም በትግራይ መሬት ሆነው የትግራይ ህዝብ እየጨፈጨፉት ይገኛሉ ” ማለታቸውን አመልክተዋል። ከዚህ ውጭ ሌሎች የተጓደሉ ጉዳዮች ስለመኖራቸው በዜናው አልተገለጸም።

ቀደም ሲል ” በአጠቃላይ በሁሉም ደረጃ የሰላም ሂደቱ በጥሩ መልኩ እየተካሄደ ነው። ትጥቅ ያስያዘው የፓለቲካ ምክንያት ከትጥቅ እና ደም መፋሰስ ውጭ ለማሰፈፀም የሚያስችል በቂ መግባባት ላይ ደርሰናል ብለዋል ። የትግራይ ህዝብ የውጭ ደህነት እና ስጋት በአገር መከላከያ ሰራዊት የሚጠበቅ ሲሆን የውስጥ ፀጥታ ደግሞ በትግራይ የፀጥታ ሃይሎች ይጠበቃል” ሲሉ የቀድሞው ሌተናል ጀነራል ታደሰ ወረደ መናገራቸውን የድርጅቱ ገጽ አስነብቦ ነበር።

ዶክተር ደብረጽዮ “ወራሪ” ያሉት የአማራ ሃይል የትኛውን የትግራይ ክልል እንደወረረ አልዘረዘሩም። የኤርትራ ሃይል የተባለውም የትኛውን አካባቢ እንደያዘ በስም በዜናው አልተገለጸም። በፕሪቶሪያው ስምምነት መሰረት ህገወጥ ምርጫ ማድረጉን ያመነውና አዲስ ምርጫ እንዲካሄድ የተስማማው ትህነግ፣ ይህንን ውሉን አስመልክቶ “ህገወጥ ነው” ላለው ምክር ቤት “ይህ ቢሆንም ትልቁ ግባችን ሰላም ነው” ሲሉ ዶክተር ደብረጽዮን አመልክተዋል።

“የውስጥ ጸጥታ በትግራይ የጸጥታ ሃይሎች ይጠበቃል” ቢባልም የመከላከያ ሃይል ባልደረሰባቸው አካባቢዎች በፓትሮል የተደገፈ የቡድን ዝርፊያ ከቁጥጥር ውጭ መሆኑንን ከትግራይ የሚወጡ ዜናዎች ያመልክታሉ። አምራች ሃይል በሙሉ ዕድሜ ሳይለይ አንጋች በሆነባት ትግራይ የተደራጀ ሌብነት ህዝቡን እንዳማረረ በስፋት የተማጽኖ ጥያቄ እንደሚቀርብለት ያስታወቀው መንግስት ለትግራይ ህዝብ ደህንነት ሲል አስፈላጊ ነው ያለውን እርምጃ እንደሚወስድ፣ በቡድን ተደራጅተው ዘረፋ በሚፈጽሙት ላይ ህጋዊ እርምጃ እንደሚወሰድም አመልክቶ ከአንድ ቀን በፊት መግለጫ ማውጣቱ ይታወሳል። የትህነግ ልሳን ስለዚህ ጉዳይ ያለው ነገር የለም።

በደፈናው “ወራሪ ሃይል” የተባለው አማራና የኤርትራ ሰራዊት የትግራይን መሬት ለቀው እንዲወጡ አለመደረጉን ገልጾ መንግስትን የከሰሱት የድርጅቱ ሊቀመንበር ዶክተር ደብረጽዮን ናቸው። እሳቸው ለትግራይ ምክር ቤት 6ኛ ዘመን 3ኛ አመት አስቸኳይ ስብሰባ ባቀረቡት ሪፖርት ይህን ቢሉም ተሰብሳቢዎች ስለሰጡት ግብረ መልስ የተባለ ነገር ግን የለም።

መንግስትም ሆነ የተባበሩት መንግስታት በትግራይ በአራቱም አቅጣጫ የእርዳታ ስንዴ፣ ዱቄት፣ ዘይትና አልሚ ምግብ፣ እንዲሁም መድሃኒት ወደ ትግራይ ያለ አንዳች ገደብ እየገባ እንደሆነ ይፋ አድርገዋል። መልሶ ግንባታን በተመለከተ ባንኮችን ለማስጀመር የኔትዎርክ ስራ እየተጠናቀቀ መሆኑ፣ መብራት መቀለ፣ አድዋ፣ አክሱም፣ ሽሬና መስል ከተሞችን ጨምሮ ዘጠና ከመቶ መድረሱን፣ የስልክ አገልግሎት እየተስተካከለ መሆኑን መንግስት አስታውቋል። አገልግሎቱን ያገኙም ከተሞችም መኖራቸው ተመልክቷል። ይህንን ዳታና መረጃ ትህነግ አላስተባበለም።

መንግስት በሰላም ስምምነቱ ወቅት የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ሃይሉን በአገሪቱ ያሻው ስፍራ ላይ ማስፈር እንደሚችል ጠቅሶ ባቀረበው ህጋዊ አግባብ መሰረት ይሄው ተግባራዊ እንዲሆንና በአንድ አገር አንድ መከላከያ ሊኖር እንደሚገባ ህገመንግሱ በሚያዘው መሰረት የትህነግ ታጣቂዎች ትጥቅ እንዲፈቱ ቀነ ገደብ ቢቀመጥም እስካሁን ለምን ተግባራዊ እንዳልሆነ ደብረጽዮን አላስታወቁም። ከቀን በፊት መንግስት ባወጣው መግለጫ ግን ” የሰላም ስምምነቱ ተግባራዊ እንዲሆን ከሁሉም ወገን ቀና ትብብር ያስፈልጋል” በሚል ጥቅል መልዕክት አስተላልፎ ነበር።

“ትህነግ ሲያገገምና ዕህል፣ ነዳጅና መድሃኒት ሲያገኝ ጦርነት ያምረዋል” በሚል ይህንን ዜና የሰሙ በማህበራዊ ገጾች እየዘገቡ ነው። በርካቶች እንዳሉት አሁን የትግራይ ህዝብ ሊነቃ እንደሚገባው ነው። ከተለያዩ አካላት እንደሚሰማው በተለያዩ ነጻ የወጡ ትልልቅ ከተሞች ተቃዋሚዎች በስፋት ስራቸውን እየሰሩ መሆኑን ነው።

በቅርቡ “ውረድ፣ ከአገር ውጣ፣ ለፍርድ ትቀርባለህ፣…” ሲባሉ የነበሩት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ፣ አሜሪካ ሄደው ከአንቶኒዮ ብሊንከን ጋር ከተነጋገሩ በሁዋላ “የሰላም ስምምነቱ ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ እንደሚሆን አለጠራጠርም” ማለታቸው ይታወሳል። ጆ ባይደንም ከሚጎበኟቸው የአፍሪካ አገራት መካከል አንዷ ኢትዮጵያ መሆኗም ግልጽ ተደርጓል።

ዜናውን ሙሉ በሙሉ ከስር ያንብቡ።

የትግራይ መንግስት እና ህዝብ የሰላም ሰነድ ስምምነቱ ለመተግበር ከልብ ተቀብሎ በተግባር እየሰራበት ቢሆንም የፌዴራል መንግስቱ የስምምነቱ ቃል በተግባር እየፈፀመ አለመሆኑን ተገለፀ ፡፡

የትግራይ ፕሬዝደንት ዶክተር ድብረፅዮን ገብረሚካኤል በትግራይ ምክር ቤት 6ኛ ዘመን 3ኛ አመት አስቸኳይ ስብሰባ ባቀረቡት ሪፖርት እንደገለፁት የተደረሰው የሰላም ስምምነት ሰነድ የአንድ ወር አተገባበር ደረጃ አፈጻጸም በማስመልከት ለትግራይ ምክር ቤት ባቀረቡት ሪፓርት የሰላም ስምምነቱ ከተፈረመ ወዲህ የትግራይ ህዝብ እና መንግስት ሁሉም አይነት የሰላም ስምምነቱ ጥያቄዎችን እየፈጸሙ ቢሆንም በፌደራል መንግስት በኩል ከሰብአዊ እርዳታ አንፃር አበረታች ጉዳዮች ቢኖሩም በተቀሩት የሰላም ስምምነቱ ነጥቦች ዙርያ ግን የፌደራሉ መንግስት በቃሉ መሰረት እንዳልፈፀመ አብራርተዋል ፡፡

የትግራይ ሰራዊት ለሰላሙ እንቅፋት ላለመሆን ሲባል በተደረሰው የሰላም ስምምነት መሰረት በአራት ግንባሮች የውግያ ቀጠናዎች እንዲለቅ መደረጉን የገለፁት ዶክተር ደብረፅዮን ገ/ሚካኤል ይሁን እንጂ ከኢትዮጵያ ሰራዊት በኩል ግን ያንን ተግባር እንዳልተፈፀመ ገልፀዋል ፡፡

ሰላም ለትግራይ መንግስት እና ህዝብ ስትራቴጅካዊ ምርጫቸዉ ነው ያሉት ዶክተር ደብረጽዮን ለዚህም ሲባል ሁሉም ኣይነት የሰላም ስምምነቱ ተግባራት በመፈፀም ላይ ነው ያሉት ዶክተር ደብረጽዮን በመሆኑም በተደረሰው የሰላም ስምምነት ውል መሰረት የኤርትራ ሰራዊት እና የአማራ ታጣቂዎች በወረራ ከያዙት የትግራይ መሬት ለቀው ሊወጡ ሲገባ አሁንም በትግራይ መሬት ሆነው የትግራይ ህዝብ እየጨፈጨፉት ይገኛሉ ብለዋል ፡፡

ታህሳስ 9/2015 ዓም
ድምፂ ወያነ ትግራይ

የፕሪቶርያው እና የናይሮቢ የሰላም ስምምነት ፤ የትግራይ ህዝብ ፀጥታ እና ደህነንት በሚያረጋግጥ መልኩ ነው የሚፈፀመው ።
የትግራይ ሰራዊት ዋና አዛዥ ጀነራል ታደሰ ወረደ
በተፈረመው የሰላም ስምምነት መሰረት የትግራይ ሰራዊት ተግባራዊ እርምጃዎች እየወሰደ መሆኑ የትግራይ ሰራዊት ዋና ኣዛዥ ጀነራል ታደሰ ወረደ (ወዲ ወረደ ) ገልፀዋል።
ከ60 እስከ 65 በመቶ የትግራይ ሰራዊት ከውግያ ግምባርች ለቆ እንደወጣ ጀነራል ታደሰ ወረደ አብራርተዋል።
ከትግራይ ህዝብ ደህንነት ጋር የተያያዘ የሚነሳ ስጋት መኖሩን የተናገሩት ጀነራል ታደሰ ወረደ፣ ለዚህም የኤርትራ ሰራዊትና የአማራ ታጣቂዎች በህዝቡ ላይ እየፈፀሙት ያለው ግፍ ማሳያ መሆኑ አመላክተዋል።
አሁን የመጣው ሰላም የትግራይ ህዝብ እና ሰራዊት በከፈሉት መስዋእትነት የመጣ ነው ያሉት ጀነራል ታደሰ ወረደ(ወዲ ወረደ)፣ በተደረሰው የሰላም ስምምነት መሰረት የምንወስዳቸዉ ተግባራዊ እርምጃዎች ለዘላቂ የትግራይ ህዝብ ደህንነት ጠቃሚ መሆናቸው ገልፀዋል ።
በአጠቃላይ በሁሉም ደረጃ የሰላም ሂደቱ በጥሩ መልኩ እየተካሄደ ነው። ትጥቅ ያስያዘው የፓለቲካ ምክንያት ከትጥቅ እና ደም መፋሰስ ውጭ ለማሰፈፀም የሚያስችል በቂ መግባባት ላይ ደርሰናል ብለዋል ።
የትግራይ ህዝብ የውጭ ደህነት እና ስጋት በአገር መከላከያ ሰራዊት የሚጠበቅ ሲሆን የውስጥ ፀጥታ ደግሞ በትግራይ የፀጥታ ሃይሎች ይጠበቃል ብለዋል ጀነራል ታደሰ ወረደ ።
ጀነራል ታደሰ ወረደ፣ የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ባለበት የትግራይ ህዝብ ደህንነት የመጠበቅ ያለበት ሀላፊነት በከፍተኛ አትኩሮት ሊተገብረው ይገባል ያሉ ሲሆን፣ በተደረሰው የሰላም ስምምነት መሰረት በጥንቃቄ ስምምነቱ ሊተገበር እንደሚገባም አመላክተዋል።

አክሱምና አድዋ ከተሞች የኤሌክትሪክ አገልግሎት ዳግም አገኙ


(ኢ.ፕ.ድ)

ለረጅም ጊዜ የኤሌክትሪክ አገልግሎት ተቋርጦባቸው የቆዩት አክሱም፣ አድዋና ውቅሮ ማሪያም ከተሞች በዛሬ ዕለት ዳግም አገልግሎቱን ማግኘታቸውን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት አስታወቀ፡፡

እነዚህ ከተሞች ዳግም ተጠቃሚ የሆኑት ከሽረ-አድዋ የተዘረጋውን የ66 ኪሎ ቮልት ከፍተኛ የኤሌክትሪክ ማስተላለፊያ መስመር እንዲሁም የመካከለኛ የዝቅተኛ መስመር የጥገና ሥራ መጠናቀቁን ተከትሎ ነው፡፡

ተቋሙ በሰሜኑ የሃገራችን ክፍል በተከሰተው ጦርነት በኤሌክትሪክ ማሰራጫ መሠረተ ልማቶች ላይ የደረሰውን ጉዳት ከስር ከስር መልሶ በመጠገን የኤሌክትሪክ አገልግሎት የተቋረጠባቸውን አካባቢዎችን ዳግም ተጠቃሚ ለማድረግ ከፍተኛ ጥረት በማድረግ ላይ መሆኑ ይታወቃል፡፡

የሰላም ስምምነቱ ከተፈረመ በኋላም ከአማራና አፋር ክልል በተጨማሪ በትግራይ ክልል የቴክኒክ ባለሞያዎችን በማሰማራትና አስፈላጊ ግብዓቶችን በሟሟላት አገልግሎት የተቋረጠባቸው አካባቢዎችን ዳግም ተጠቃሚ እያደረገ ይገኛል፡፡

አሁንም በሶስቱም ክልሎች ቀሪ የኤሌክትሪክ አገልግሎት ያላገኙ አካባቢዎችን ዳግም ተጠቃሚ ለማድረግ ከፍተኛ ርብርብ እያደረገ መሆኑን አገልግሎቱ አስታውቋል።

Exit mobile version