Site icon ETHIO12.COM

መንግስት ከሲሚንቶ ንግድ ወጣ

የንግድ እና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ተሻለ በልሁ ከዚህ በፊት የነበረው የሲሚንቶ ሽያጭ መመሪያ መቀየሩንና መንግስት ከሲሚንቶ ንግድ መውጣቱን በያፋ ገልጸዋል።

መመሪያው የሲሚንቶ ዋጋ በመንግሥት ተወስኖ እንዲሸጥ መደረጉ በርካታ ቅሬታዎች ሲነሳበት እንደነበር የጠቀሱት አቶ ተሻለ በዚህም ክልሎች እና የከተማ አስተዳደሮች፥ ሲሚንቶን በቀላሉ እንዳያገኙ አድርጓቸው እንደነበር ተናግረዋል። በተሻሻለው መመሪያ መሰረትም አከፋፋዮችን እና ቸርቻሪዎችን መምረጥ የፋብሪካዎቹ እድል ነው ብለዋል።

የፋብሪካዎቹ የመሸጫ ዋጋ ለጊዜው ምርታማነት እስከሚጨምር ድረስ የፋብሪካ ዋጋ በስድስት ወር አንድ ጊዜ በሚኒስቴሩ እንደሚወሰን ነው የተናገሩት። መንግስት ከግብይቱ የወጣ ሲሆን በተሻሻለው መመሪያ መሰረትም መንግስት ሽያጩ ያለ ደረሰኝ እንዳይካሄድ ቁጥጥር እንደሚያደርግ አስረድተዋል።

በግብይቱ ውስጥም ህጋዊ ንግድ ፍቃድ እና ደረሰኝ ግዴታ መሆናቸውን ጠቁመዋል። እያንዳንዱ ፋብሪካ የተደራሽነት አድማሱን በማስፋትም አከፋፋዩን የመምረጥ ፍላጎት እንዳለው ተናግረዋል።

ከዛሬ ጀምሮም ሲሚንቶ በየትኛውም ቦታ ቁጥጥር እና ክትትል ሳይደረግበት በነጻ ገበያ ይካሄዳል ነው ያለው ሚኒስቴሩ። ከፋብሪካ ሲሚንቶ የሚወጣ ማንኛውም ተሽከርካሪ የመዳረሻ ሰነድ መያዝ እንደሚኖርበት ማሳሰባቸውን የገለጸው ፋና ነው።

Exit mobile version