Site icon ETHIO12.COM

«…ሁሉንም ያካተተ ጠንካራ አስተዳደር መፈጠር አለበት»የቀድሞ የዋጅራት ወረዳ አስተዳዳሪ

አዲስ አበባ፡- የተፈጠረው የሰላም ዕድል ውጤታማ እንዲሆንና ህብረተሰቡ ከሰላም ተጠቃሚ እንዲሆን በክልሉ ሁሉንም አካላት ያካተተ ሕግና ስርአት የሚያስከብር ጠንካራ አስተዳደር ሊመሰረት እንደሚገባ ቀደም ሲል በነበረው የትግራይ ጊዜአዊ አስተዳደር የዋጅራት ወረዳ አስተዳዳሪ የነበሩት አቶ መኮንን አብርሃ ተናገሩ።

አቶ መኮንን ከኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ጋር ባደረጉት ቆይታ እንደተናገሩት፤ ቀደም ሲል በትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ወቅት የተፈጠረው ችግር እንዳይደገምና ህዝቡ ተረጋግቶ ወደ ቀድሞ ኑሮው እንዲመለስ አካታች፣ ጠንካራ እና ስርአት የሚያስከብር አስተዳደር መገንባት ያስፈልጋል።

አሁን የተፈጠረው የሰላም አየር ለትግራይ ህዝብና ለአጎራባች ክልሎች እጅግ እረፍት የሚሰጥ እና በተለይ በሰላም እጦት ምክንያት የተቋረጠው የትምህርትና ማህበራዊ አገልግሎት ወደ ነበረበት እንዲመለስ ከፍተኛ ሚና የሚጫወት ነው ብለዋል።

አቶ መኮንን እንደተናገሩት፤የተፈጠረው የሰላም ሁኔታ ዘለቄታ እንዲኖረውና እንዲፀና በተለይ የሚዲያ ተቋማት ትልቅ ድርሻ አላቸው። የትምህርት ስርዓቱና ሌሎች ተቋማትም አዲሱ ትውልድ በጎ ሃሳብ እንዲያመነጭ እና እርስ በርስ ከመጠላላት አጀንዳ ወጥቶ በመልካም ስነ ምግባርና በግብረ ገብ እንዲታነፅ ድርሻቸውን እንዲወጡ አቶ መኮንን ጠይቀዋል።

ያለፉት ሁለት ዓመታት ለሀገራችን በተለይ ለሰሜኑ ክፍል እጅግ ከባድ ጊዜ እና ኪሳራ ያስከተለ እንደነበር በማስታወስ ከምንም በላይ በህዝባችን ላይ የደረሰው የስነ ልቦና ቀውስ እንዳይደገም ሁላችንም የበኩላችንን ጥረት ልናደርግ ይገባል ብለዋል።

ከዚህ ጋር ተያይዞ የአእምሮ ጤና ባለሙያዎች ፣የሃይማኖት አባቶችና የሚዲያ አንቂ ግለሰቦች በህብረተሰቡ ስነልቦናዊ ውቅር ላይ ትኩረት አድርገው ቢሰሩና ከምንም በላይ በስነ ምግባር የታነፀ፣ ምክንያታዊ ትውልድ እንዲፈጠርና የተበላሸው እንዲስተካከል ቅድሚያ ሰጥተው ቢሰሩ ወደ ተሻለ ሁኔታ እንደሚደረስ ተናግረዋል።

መንግስት ከባለ ድርሻ አካላት ጋር በመሆን ሁኔታዎችን የማስተካከል ድርሻ ከተወጣ ጠንካራ ማህበረሰብ ለመፍጠር አያዳግትም ያሉት አቶ መኮንን፤ በጦርነቱ የወደሙ መሰረተ ልማቶችና የተጎሳቆለው ማህበረሰብ መልሶ እንዲያገግምና ወደ እድገት እንዲያመራ የሰብአዊ እርዳታ ላይ እየተደረገ ያለው ርብርብ ጠቃሚ መሆኑን አቶ መኮንን ተናግረዋል።

ይህንን የሰላም ዕድል በተለይ የትግራይ ህዝብ በጉጉት ሲጠብቀው የቆየ በመሆኑ ይህንን ሊያስፈፅምለት የሚችል ጠንካራ አመራርና እና የህግ ተጠያቂነት ያለው ሁሉን አካታች አስተዳደር ዘርግቶ በትኩረት መስራት እንደሚገባ አሳስበዋል።

የትግራይ ህዝብም የተፈጠረለትን የሰላም ዕድል በመጠቀም አጋጥሞት ከነበረው ችግርና መከራ ጨርሶ ለመውጣት ከመንግስትና ሲቪክ ማህበራት ጋር በመሆን መወያየትና ጠንክሮ መስራት ይጠበቅበታል ሲሉ መልእክታቸውን አስተላልፈዋል።

 ሄርሞን ፍቃዱ

አዲስ  ዘመን ታህሳስ 15/20215

Exit mobile version