Site icon ETHIO12.COM

የአማራና የኦሮሞ ሸኔዎች የግብር አንድነት – የተላላኪዎች አጀንዳ

“ስጋት አለኝ” አሉ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ። “ኮርቻለሁ” ሲሉም ደጋግመው አስታወቁ። በሌብነት ላይ የተጀመረው ዘመቻ እንደማይቆም አስረገጡ። ተስፋ፣ እድል፣ መልካም ውጤት እያየች ያለችው ኢትዮጵያ ካሁን በሁዋላ አንዱ ሌላውን ጭፍልቆ የሚያሳካው አንዳችም አይነት አጀንዳ እንደሌለ ገለጹ። ” አደራ” ሲሉም ለነብስና ልብ፣ ለሚሰሙና ለሚያስተውሉ ጥሪ አሰሙ።

የቀዳማዊ እመቤት ጽህፈት ቤት በሶዶ አስገንብቶ ያስመርረቀው ዳቦና ዱቄት ፋብሪካው በቀን 3መቶ ሺህ ዳቦና 42 ቶን ዱቄት በቀን ያመርታል። ይህ ፋብሪካ ሲመረቅ አብይ አህመድ ባደረጉት ንግግር ላይ ነው “እሰጋለሁ” ያሉት። በረባ ባልረባ የሚጀመሩ ግጭቶች አንድ ቀን መልካቸውን ቀይረው ወዳልተፈለገ እልቂትና መጨራረስ እንዳይመሩ ደግሞ ማሰብ፣ ማስተተዋል፣ ማጤንና በሰከነ ልቦና ነገሮችን መመርመር አሁን ላይ እጅግ ውድ ጉዳይ መሆኑንን አመልክተዋል።

በተደጋጋሚ ኢትዮጵያዊያንን ለርስ በእርስ መጨራረስ የሚያነሳሱና የሚመሩ አጀንዳዎች እየተነሱ መክነዋል። ለብዙ ሺህ አመታት አብሮ የኖረው ሕዝብ ጀርባ በመስጠቱ ጥቂቶች ሊያተራምሱ አስበውና ወጥነው ሲደክሙ የኖሩ አፈር ሆነዋል። የውሻ ሞት ሞተዋል። ታሪክ መሳቂያና መሳለቂያ አድርጓቸው አልፈዋል። የነሱ ርዝራዦች የዘረፉትን በመድፋት፣ ከታሪካዊ የኢትዮጵያ ጠላቶች ጋር በማበር ኢትዮጵያን ሊበትኑ፣ ሲኦል ሊያደርጉ፣ ስትበተን ማየት እንደሚያስደስታቸው አደባባይ እየተናገሩ ሲዛበቱ ታሪክ ተገልብጧል። አብይ አህመድ ይህን በዝርዝር ባይሉም ጉዳዩ ” ሌብነት ላይ የተጀመረውን ዘመቻ አቁሙ” የሚል አመጽ እንደሆነ ገልጸዋል። አክለውም “ሳይቸግረን ሌብነት ላይ ዘመቻ መጀመራችን…” በሚል ምጸት ጀምረው፣ ” የሌብነት ዘመቻው ለአፍታም አይቆምም፤ ካቆምነው መልካቸውን እየቀያየሩ ይመጣሉ፤ ህዝብ የጀመረውን ዘመቻውን የማገዝ ተሳትፎ ያበርታ” ብለዋል።

የኦሮሞ ሸኔ እንዳለ በስፋት ቢነገርም የአማራ አክራሪ ቡድን እንጂ የአማራ ሸኔ ስለመኖሩ ቃል በቃል አልተነገረም። ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ የአማራና የኦሮሞ ሸኔዎች በግብር አንድ፣ የኢትዮጵያን ካርታ ለማጉደል የሚሰሩ ግን የማይሳካላቸው መሆኑን ይፋ ተናግረዋል።

ዛሬ ላይ ኢትዮጵያ ውስጥ ሌላውን ጨፍልቆ መኖር እንደማይቻልና ያ ያከተመ አስተሳሰብ መሆኑን ያመለከቱት አብይ አህመድ፣ ዋልታ ረገጥ እሳቤዎችን የሚያራምዱት የኦሮሞና አማራ ሸኔ የኢትዮጵያን ካርታ ለማጉደል፣ ህዝብን ለማጫረስ፣ በውክልና የሚሰሩ ስልጣንን በግድያና በነፍጥ ለመያዝና የተላላኪነታቸውን ቁልፍ ጉዳይ ተግባራዊ ለማድረግ የሚቃዡ ድርጅቶች እንደሆኑ በግልጽ ተናግረዋል።

ሁለቱም በግላቸው የሚፈልጡበትና የሚቆርጡበት አገር መምራት እንደሚያምራቸው ያስታወሱት አብይ አህመድ፣ ከማናቸውም ሃይላት ጋር ለመነጋገር፣ ለመወያየትና አስፈላጊ የሚባሉ የመፍትሄ ሃሳቦችን ለማመንጨት ቁርጠኛ ዝግጅት በመንግስት በኩል እንዳለ አስታውቀዋል። ይሁን እንጂ እነዚ ዋልታ ረገጥ አላማ ይዘው አገሪቱን በደም ለማጠብ የተነሱ ሸኔዎች እንዲህ ያለውን የስለጠነ አካሄድ እንደማይቀበሉ፣ የቀጠሯቸውም ይህን አካሄድ እንደማይፈቅዱላቸው ጠቁመዋል።

“እናም” አሉ አብይ አህመድ “ሕዝብ ደግሞ ደጋግም ሊያስብ፣ ሊመረምርና ሊያስብ ይገባል” ሲሉ በአደራ መልክ ከስጋት ጋር ጥሪ አቅርበዋል። በርካታ ተስፋ የሚሰጡና እንደ አገር አንገትን ቀና የሚያስደርጉ ውጤቶች መመዝገባቸውን ” የሚያምነን ህዝብ፣ የሚወደንና የሚያግዘን ህዝብ ስላለ አሳክተናል። ምስክራችንም ይህ ህዝብ ነው” ሲሉም ባዩት የልማት መስክ ላይ ሆነው ምስጋና አቅርበዋል። ሌሎችም ተሳስተው የዘረፉም ካሉ በተመሳሳይ እንዲያለሙበት ጥሪ አቅርበዋል። ይህ ሳይሆን ቀርቶ በተዘረፈ ሃብት ውስኪ እየጠጡ አገር ማተራመስና ታታቂ እያሰማሩ ንጹሃንን ማሳረድ እንደማያዛልቅ በይፋ ተናግረዋል።

“ታሪክ ሊታጠፍ ተቃርቧል” ሲሉ የኢትዮጵያን ተስፋና ልክ ያስታወቁት አብይ አህመድ፣ ኢትዮጵያ አቡካዶ መግዛት አቁማ ለዓለም ገበያ መሸጥ መጀመሯ፣ ስንዴት መግዛት አቁማ ለመሸጥ ዝግጅት ላይ መሆኗ፣ በርካታ ፍራፍሬዎች ወደ ውጭ ለመላክ ከዳር መድረሷን በመጠቆም፣ “ካሁን በሁዋላ አምስት ዓመት ብንሰራ መታጠፍ የጀመረው የልመናና የመረዳት ታሪክ ታጥፎ ረጂና ሽጭ እንሆናለን” ብለዋል።

ኢትዮጵያ ያላትን የተፈጥሮ ሃብት እንዳትጠቀም አቅሟንና ልኳን የሚያውቁ ለአፍታም እንደማይተኙ በተደጋጋሚ በማስረጃ የተረጋገጠ በመሆኑ እንደ ሕዝብ ትስስርን ማጽናቱ አስፈላጊ መሆኑንን አገራቸውን የሚወዱ በተደጋጋሚ የሚሉት ጉዳይ ነው። የትግራይ ሕዝብ ነጻ አውጪ ግንባር መንደር ነጻ አወጣለሁ ብሎ ተመስርቶ ሳያስበው መንግስት የሆነውም ኢትዮጵያ ላይ ክፉ ምኞትና ዓላማ ባላቸው ታሪካዊ ተላቶቿ ድጋፍ እንደሆነም አጥኚዎች፣ የበሰሉ ምሁራኖችና አገር ወዳዶች ሲያስተምሩ ቆይተዋል።

ላለፉት ሃያሰባት ዓመታት በግብር ከፋዩ ህዝብ በሚተዳደሩ የመንግስት መገናኛዎች ሳይቀር ጥላቻን፣ መላያየትን፣ አንዱ በሌላው ላይ ጠላት እንዲሆን ቅርሾ በማባባስ፣ የፈጠራና የግነት ታሪካ በማራባት ይህ የዘር ፖለቲካ አራማጅ ድርጅት (ትህነግ) ውጤታም ስራ ሰርቷል። ትህነግ በሃይማኖት ተቋማት፣ በትምህርት ፖሊሲ፣ በህገመንግስትና በተለያዩ አደረጃጀቶቹ በመጠቀም ኢትዮጵያን ሲፈልግ የሚበትናት፣ ሲፈልግ የሚሰበስባት ዓይነት አገር አድርጓት እንደነበር በርካቶች ይስማማሉ። በዚህ መካከል ከውስጥና ከውጭ በደረሰበት ጫና ተስፈንጥሮ ወደ መቀለ የሸሸው ዘረኛ ድርጅት ያሳደጋቸውና የገነተራቸው እዚህ ግባ በማይባሉ ምናምንቴ ጉዳዮች እየተነዱ ሌላውን ሲነዱ ማየት በርካቶችን የሚያሳዝን ሆኗል።

ለዚህም ነው አብይ አሕመድ ” በዋዛ የሚነሱ ግጭቶች መተላለቅን እንዳያስከትሉ” ሲሉ ፍርሃቻቸውን የገለጹት። ከትህነግ እሳቤ “ዘረኝነት” ያልተላቀቁ የተሰገሰጉበት ብልጽግናን የሚመሩት አብይ አህመድ ” ስጋታቸው የበዛ፣ፈተናቸው የጠነከረ ነው” ሲሉ በርካቶች በአዘኔታ የሚገልጿቸው አብይ አህመድ በጠቀሷቸው አካላት ላይ ምን እርምጃ እንደሚወሰድ ባይናገሩም ነገሩ ቀላል እንዳልሆነ ግን የሰሞኑ ንግግራቸው ያመላክታል።

“መንግስት ጽንፈኞችን እንዲቀጣ ህዝብ ሚዲያዎች ይወተውታሉ። ነውጠኛና እልቂት ሰባኪ ሚዲያዎችና ባለቤቶቹ ላይ መንግስት ተፋዟል የሚል አስተያየት አለ። እነዚህ አካላት ላይ መንግስት እርምጃ ሲወስድ ደግሞ ጩኸቱ ይበረክታል። ኢትዮጵያ ውስጥ እየሆነ ያለው ግራ ቢያጋባም፣ ያለፉት ሰላሳ ዓመታት የተዘራውን ዘር በአራት ዓመት ማምከን ከባድ በመሆኑ ጤነኞች ሳይሰልሱ መታገል እንጂ ዳር መቆም አለባቸው። ካልሆነ መናድና መፈርከስ ያመጣል” ሲሉ አያሌው ሞገስ መናገራቸው ይታወሳል።

አብይ አህመድ ለሶዶ ዳቦ ፋብሪካ ግንባታ ግንባር ቀደም ተዋናይ ለሆነው የሚድሮክና ሼኽ መሐመድ ሁሴን አላሙዲንን አምስግነዋል። አዲሱ የአላሙዲን ወኪል የሆኑትን አቶ ጀማልን ” ባለሃብቱ ጥሩ ልጅ አግኝተዋል” ሲሉ አሞካሽተው አወድሰዋል። በጎንደር፣ በደሴና በተለያዩ ከተሞች ከአስር የሚበልጡ ዳቦ ማረቻዎች እንደሚገነቡም አመልክተዋል።

“ፈጣሪ ረድቶን፣ ከሌብነት የጸዳ እጅ ይዘን፣ የጀመርነውን በመጨረስ ያማረች ኢትዮጵያን ለመጪው ትውልድ እናስረክባለን” ሲሉ ተስፋቸውን የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ፣ ኢትዮጵያን ለሚወዱ ሁሉ “ግማሽ ጎንን ቆርጦ መጣል አያዋጣም። አንዳችን ለሌላችን ግማሽ ጎን ነን” ሲሉ ኢትዮጵያዊያን የተገመዱበትን ረቂቅ የደም ትስስር መመርመር የሚያስችል ሃሳብ አኑረዋል። እሳቸው ባይሉትም ይህ በየጊዜው የሚቀረጸው አጀንዳ አብሮ የማይኖር፣ አንዱ የሌላውን ሳይሆን የራሱን ግማሽ ጎን ቆርጦ እንዲጥል የሚያደርግ፣ ረጋ ተብሎ ሲመረመር የሚያስደነግጥ አክሳሪ መንገድ ነው።

ሙክታሮቪች በቴሌግራም ገጹ አንድ የሶማሊ ላንድ ዜጋ ወዳጁን ጂጂጋ ከተማ አግኝቶት ስለወቅታዊ የኢትዮጵያ ሁኔታ ሲነጋገሩ በሰማው ተደንቆ ይህንን አስፍሯል።”እኛ የሶማሊላንድ ዜጎች የሀገር መፍረስ የሚያመጣውን ውስብስብ ችግር አይተነው እናውቃለን። ይህ የሀገር መፍረስ ጣጣን እናንተ ኢትዮጵያውያን ከኛ መማር አለባችሁ። በኢትዮጵያ ከባድ የፖለቲካ ፍጥጫ አለ። እኛ ሶማሊላንዶች ለኢትዮጵያ በጣም ነው የምንጨነቀው” ሲል እንግዳው ይናገራል።

“እናንተ ስለኛ ምን አስጨነቃችሁ?” ሲሉ ሙክታሮቪች ይጠይቃል። “እንዴ? አብደሃል እንዴ? እንዴት አንጨነቅ? ኢትዮጵያ ከ120 ሚልየን በላይ ናት። እኛ 3 ሚሊየን አንሞላም። ኢትዮጵያ ችግር ከገጠማት ሱናሚው እኛን የሚተወን ይመስለሃል? ለኢትዮጵያ የምንጨነቀው ለራሳችን ህልውና ብለን ነው” ሲል ስሌቱን አጫወተው።

የብልጽግና ስብስብ ውስጥ ያሉ ያልተቀየሩ፣ የዋልታ አመለካከት አራማጆች፣ ሌቦች፣ መንታ መንገድ አጣቃሾች ወዘተ. አጀንዳ ይሰፍራሉ። ወይም የተሰፈረውን አጀንዳ ያሰራጫሉ። ወይም ባሉበት ወንበር ሆነው አጀንዳው ላይ ነዳጅ ይረጫሉ። ብዙ የክፋት አጀንዳዎች ተሞክረው መክሸፋቸው እየታወቀ፣ በቂ ተሞክሮና ልምድ መውሰዱ እየተረሳ መልካቸውን በሚቀያይሩት የትርምስ አሳቦች ጥቂቶች እየውኙበት ብዙ ጥፋት ሲደርስ እየታየ ነው። ይህ ዘርና ሃይማኖት ላይ እንደመዥገር ተጣብቆ እየተከናወነ ያለው የጥፋት ወረሺኝ ” ለራሴ ስል” በሚል ማምከኛ ካተገታ አገር አልባ እንደሚያደርገን ጥርጥር የለውም። የተበተኑና ዘር ለይተው የተጫረሱ የጀመሩት በዚሁ መልኩ ነው።

ላለፉት አራት ዓመታት ዕለት ዕለት ስድብ፣ ተንኮል፣ ሴራ … እየተለማመዱ ሲገቱን የከረሙ የዘር ፖለቲካ አራማጅ ካድሬዎች ዓላማቸው ግማሽ አካላን የማስወገድ ጉዳይ ነውና ጠንቀቅ ማለት ይበጃል። ትናንት በትህነግ ጫማ ውስጥ ሆኖ ወታቶች ሲረሸኑ ” ሌቦች ናቸው” ብሎ መግለጫ ሲሰጥ በነበረ፣ የትህነግ የወጣቶች መልማይና አደረጃጀት ሃላፊ የነበረ፣ በግል በገሃድ ኢትዮጵያን እንደሚያፈርሱ ሲዝቱ በነበሩ፣ እያማተቡና የማሪያምን ስም እየጠሩ የደም ፖለቲካን ከሚሰብኩ፣ አገር ቤት ሆነው የተገዙ ሚዲያዎችን ሰብስክራይብ መማድረግና በየማህበራዊ ገጹ በማሰራጨት ኢትዮጵያን የደም ማዕበል ለማድረግ የተነሱትን የምትደግፉ፣ የምትከታተሉ፣ የምታሰራጩ አስቡበት የሚል አሳብ ያላቸው እየወተወቱ ነው።

ኢትዮጵያ የብዙ እሳቤና የብዙ እሳቤ ያላቸው ስብስብ ነችና “እኔ የምለው ብቻ” በሚል ያረጀ አስተሳሰብ መንጎዱ አገር አልባ ከመሆን አይድንምና ” በጋራ ያልነው” በሚል አስፍቶና አጥርቶ ማሰብ የዚህ ወቅት ጥያቄ ነው።

የአማራ ሸኔም ሆነ የኦሮሞ ሸኔ አክርረው ለኢትዮጵያም ሆነ በስሙ ለሚምሉለት ብሄር ከሞት ውጭ የሚያመጡለት አንዳችም ፋይዳ የለም። አሁን ያለው የአማራ ክልል እንዲፈርስ ፓርላማ ሆነው በኮድ ሽብር የሚረጩ፣ ኦሮሚያ እሳት ሆና ልማቷ እንዲጋይ የሚሰሩ ብዙ ናቸና “ጨው ለራስህ ስትል” እንዲሉ ነውና ረጋ ብሎ ማሰብ እንደሚያስፈልግ በሰፊው የገባቸው እየጮሁ ነው።

የእርቅ ኮሚሽኑ ህገ መንግስት እስከመቀየር የሚደርስ ሃላፊነት ይዞ እየሰራ መሆኑና፣ አድማሱን አስፍቶ አገር የምትቀጥልበት ጅማሬውን ከማገዝ ይልቅ የኮሚሽኑ አካሄድ የሚቀብ ራቸው ዘረኞች በስጋት ከወዲሁ አገሪቱን ለመቅበር በሚቀብሩት ፈንጂ ላይ መራመድ ትርፉ ሞት ብቻ እንደሆነም እየተገለጸ ነው።

አሁን ላይ ኦሮሞ በጠብ መንጃ ትግል የሚያገኘው ያልተመለሰ ጥያቄ አለው? ሲሉ የሚጠይቁ “ወለጋ የተለየ ጥያቄ ካለው ግልጽ ያድርግ” እያሉ ነው። በአማራ ክልል አክራሪ ሆኖ በሚከበር ስም የሚነግደው የድርቷሞች ንቅናቄ ዓላማው ምንድን ነው? ምንድን ነው የሚፈልገው? ምን ሲደረግለት ያርፋል የሚለውንና የሚመኘው ከታወቀ በሁዋላ “የሚሳካ ነው?” ብሎ መጠየቅ በእጅ የያዙትን ከመጣል በፊት ለጥንቃቄ የሚረዳ ጉዳይ ይሆናል።

ፎታቾች የችግኝ ተከላውን ” የደም ዘመቻ” ብለው ቀለም ቢቀቡትም፣ ዛሬ ጫካ ሆኗል። እዚህ ጫካ ጀርባ ሆነው፣ ዳቦ ቤት ሲያስመርቁ “ብዙ ቀዳማዊ እመቤቶች አይቻለሁና” በማለት ዘናሽ ታያቸውን በአደባባይ ላበረከቱት ሁሉ አመስግነዋል። አያይዘውም መከፋፈልን እየረገሙ ስጋታቸውንና ተስፋቸውን አስታውቀዋል። ምርጫው ከስውጋቱና ከተስፋው አንዱን መምረጥ ነው።

ጃዋር መሃመድ የዛሬ ሶስት ዓመት ገደማ በራሱ ሚዲያ ቀርቦ ” በዘር መቀስቀስ ድጋፍ ለማግኘትና ለማነሳሳት ይጠቅማል። መንግስት ሲኮን ግን ጣጣው ብዙ ነው” ብሎ እንደመሰከረው “መጠቀሚያ” ከመሆን ለመዳን ” ማሰብና ረጋ ብሎ መመርመር ግድ ነው” ከሚሉት ወግኖች ተርታ መሰለፉ ግማሽ አካልን ቆርጦ ከመጣል፣ ራስንም ከማጥፋት ይታደጋል።

“ዘረኛነት ላይ የተመሰረተ ግድያ ሆን ብሎ የአንድን ዘር የማጥፋት ዘመቻ ነው። አንድን ሰው ወይም ማህበረሰብ በዘሩ፣ በጎሳው፣ በእምነቱ፣… ምክንያት መግደል ጂኖሳይድ ነው። እናም በዘር ተደራጅተው የሚመጡ ሁሉ ይህን የሚያደርጉ ወንጀለኞች ናቸው። ማንም ይሁን ማን በዘሩና እምነቱ፣ በጎሳውን ማንነቱ ምክንያት ሊጎዳ አይገባም። ከሆነ ቀንይቆጥራል እንጂ በህግ የሚያስጠይቅ የወንጀሎች ሁሉ ቁንጮ ወንጀል ነው። እዚህ ውስጥ ገብቶ በማወቅም ይሁን ባለማወ የሚንቦጫረቁ፣ የሚቀሰቅሱና የሚያደራጁ፣ በገንዘብ የሚደግፉ ራሳቸውን ሊሰበስቡ ይገባል። በኢትዮጵያ በአቋራጭ የበለጸጉ ሌቦች ከዚህ ዓይነቱ ወንጀሎች ጀርባ አላችሁበት። እርፉ” ሲሉ ምጽላል ሃይሉ አዳማ ላይ ቀደም ባለው ጊዜ ተናግረው ነበር።

Exit mobile version