Site icon ETHIO12.COM

የምርመራ [ጋዜጠኝነትን]- የጸረ ሙስና ትግል?

– ኢትዮጵያን እግር ከወርች ከያዛት የሙስና ችግር ለማላቀቅ የምርመራ ጋዜጠኝነትን ማጎልበት ያስፈልጋል
– ሙስናን ለመከላከል የሚያስችል የኤሌክትሮኒክስ የግዢ ሥርዓት ተግባራዊ መሆን ጀምሯል
– የተጀመረውን የጸረ ሙስና ትግል ሚዲያዎች ሊያግዙ ይገባል

ለጋራ እሴቶቻችን እድገት እና ለሕዝብ ተጠቃሚነት እንቅፋት የሆነውን ሙስና ለመዋጋት ሚዲያዎች የጸረ ሙስና ትግሉን መቀላቀል እንዳለባቸው የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ለገሰ ቱሉ (ዶክተር) ገለጹ፡፡

የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ስልጠና ማዕከል በአዳማ ከተማ ከተለያየ የግልና የመንግሥት ሚዲያዎች ለተውጣጡ የሚዲያ ኃላፊዎችና ባለሙያዎች በምርመራ ዘገባ ዙሪያ ያዘጋጀው ሥልጠና ቀጥሏል።

በስልጠናው መክፈቻ ላይ የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ለገሰ ቱሉ (ዶክተር) እንደገለጹት፤ መንግሥት ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት መጎልበት፣ ለጋራ እድገትና አገራዊ እሴቶች እድገት በርካታ ስራዎችን እያከናወነ ይገኛል፡፡ በተለይ ኢትዮጵያን እግር ከወርች ከያዛት የሙስና ችግር ለማላቀቅ የምርመራ ጋዜጠኝነትን ማጎልበት ያስፈልጋል፡፡

በተለይ ከለውጡ ወዲህ የተጀመሩ የሪፎርም ስራዎች የታለመላቸውን ስኬት እንዲያስመዘግቡ ለማድረግ ጥረቶች ሲደረጉ መቆየታቸውን የተናገሩት
ሚኒስትሩ፣ ይሁን እንጂ ይህንን ለማደናቀፍ የውስጥና የውጭ ሃይሎች ተቀናጅተው ሲሰሩ መቆየታቸውን ጠቁመዋል።

ሙስናን ለመከላከል የተጀመሩ ስራዎች ከዳር እንዳይደርሱ የውስጥና የውጭ ጠላቶች በየደረጃው እንቅፋት ሲፈጥሩ መቆየታቸውን ጠቁመው፤ እነዚህን ችግሮች ለመከላከል በተለይ የምርመራ ጋዜጠኝነት ወሳኝ መሆኑን ተናግረዋል።

ሙስናን የመታገል ስራዎች ግን በሁለት ዋና ዋና ጉዳዮች እንቅፋት ይገጠማቸዋል ያሉት ሚኒስትሩ፤ አንደኛው በክህሎት ማነስ፣ ሙስናን መከላከል የሚያስችል የአሰራር ሥርዓት ያለመዘረጋት እና በሎጂስቲክስ አቅም ምክንያት የሚፈለገው ውጤት ማምጣት አደጋች መሆኑን ጠቅሰዋል።

እንደ ሚኒስትሩ ገለጻ፤ የጸረ ሙስና ትግሉ በፖለቲካ ተጽዕኖ፣ በአክራሪነትና በጽንፈኝነትና በብልሹ አሰራር ምክንያት የተፈለገው ውጤት ሳይመጣ ቆይቷል። እነዚህ ተጽዕኖዎችን ለመዋጋት በርካታ ስራዎች ቢሰሩም በተለያዩ ምክንያቶች ከዳር ሳይደርሱ ቀርተዋል።

ኢትዮጵያን እግር ከወርች ከያዛት ችግሮች ውስጥ አንዱ ሙስና መሆኑን የጠቆሙት ዶክተር ለገሰ፣ ከዚህ አንጻር ሥልጠናው እንደመነሻ ጠቃሚ መሆኑን ጠቁመዋል።
በአሁኑ ወቅት የሰላም ማስከበሩ ስራ በጥሩ ሁኔታ እየሄደ ቢሆንም በአንጻሩ በመልካም አስተዳደር እንዳይሰፍን ለማድረግ ሙስና ትልቅ እንቅፋት መሆኑን ተናግረዋል።

በመድረኩ ላይ የመነሻ ጽሁፍ ያቀረቡት የመንግሥት ግዢና ንብረት ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ሃጂ ኢብሳ እንደገለጹት፣ በአገራችን ከሚመደበው በጀት ውስጥ 70 ከመቶ የሚሆነው ለግዢ የሚወጣ ነው።ይህንን ሀብት ከሙስና በጸዳ መልኩ ማንቀሳቀስ ካልተቻለ እንደአገር የሚደርሰው ኪሳራ የከፋ ይሆናል።

ከዚህ መነሻነትም በዘርፉ ሙስናን ለመከላከል ዘርፈ ብዙ ጥረቶች እየተደረጉ መሆኑን የጠቆሙት አቶ ሃጂ፣ ከእነዚህም መካከል አንዱ የመንግሥት የኤሌክትሮኒክስ ግዢ ተጠቃሽ ነው ብለዋል።፡

የመንግሥት የኤሌክትሮኒክስ ግዥ ከሙስና መከላከያ መንገዶች አንዱ መሆኑን አቶ ሃጂ ጠቁመው፣ በአሁኑ ወቅትም 72 የፌዴራል ተቀማት በዚህ ሥርዓት ግዢ ለመፈጸም ወደዚህ አሰራር ገብተዋል ብለዋል።

ይህ ሥርዓት ዘርፈብዙ ጠቀሜታዎች አለው ያሉት አቶ ሃጂ ለምርመራ ዘገባውም መረጃን በቀላሉ ተደራሽ እንዲሆን በማድረግ ግልጽነትን ለመፍጠር ትልቅ አቅም እንደሚሆን ጠቁመዋል።

እስከ መጪው የካቲት ወር 2015ዓ.ም ድረስም ሁሉም የፌዴራል ተቋማት በዚህ ሂደት ውስጥ የሚያልፉበት አሰራር እንደሚፈጠር እና በቀጣዩ ዓመት የክልልና የከተማ አስተዳደሮችም ወደዚህ ሥርዓት እንዲገቡ እንደሚደረግ ተናግረዋል።

በአገራችን በሕግ በተደነገገው መሰረት እያንዳንዱ ተቋም የግዥ እቅድ እስከ ሃምሌ 30 ድረስ ማቅረብ ቢኖርበትም እስከ አለፈው መስከረም 30 ድረስ 60 ተቋማት አለማቅረባቸውን የጠቆሙት አቶ ሃጂ፣ ያለእቅድ የሚደረግ ግዢ ለሙስናና ብልሹ አሰራር በር የሚከፍት መሆኑን ተናግረዋል።

የኤሌክትሮኒክስ አሰራር እቅድ ያላቀረቡትን ስለማያስተናግድ ሙስናን ለመከላከል ትልቅ አቅም እንደሚሆን ጠቁመው፤ የኤሌክትሮኒክስ የግዢ ሥርዓት ከ20 እስከ 25 ከመቶ ሙስናን ለመከላከል እንደሚያስችልም አቶ ሃጂ አመልክተዋል።

የፍትህ ሚኒስትር ዴኤታው አቶ ፍቃዱ ጸጋ በበኩላቸው በአገራችን የመልካም አስተዳደር ችግር ከሪፎርም በፊትም የነበረና አሁንም እንደአገር መሻገር ያልቻልነው ትልቅ የልማት እና የእድገት ጠንቅ መሆኑን ጠቁመዋል።

ከለውጡ ወዲህ መንግሥት እድገትን ለማስመዝገብ በተለይ በሙስና ላይ ሰፊ ስራ ለመስራት ቢወጥንም ከቅርብም ሆነ ከሩቅ ይህንን ኃላፊነተ በአግባቡ እንዳይወጣ ማሰናከያዎች ሲደረጉ ነበሩ ብለዋል።

በተጨማሪ የኮቪድ 19 እና የሰሜኑ ጦርነት ተጨምሮ በሙስና ላይ በሚገባው ልክ ሳይሰራ መቆየቱን የተናገሩት አቶ ፍቃዱ፤ ብዙ ተስፋ የተደገረገበት የጸረ ሙስና ትግል መንግሥት ቃል በገባው ልክ ሳይፈጸም መቆየቱን ተናግረዋል። ያም ሆኖ ግን ፀረ ሙስና ትግሉ አለመቆሙን ጠቁመዋል።

በቅርቡም መንግሥት ሰባት አባላት ያሉት ኮሚቴ በማዋቀር ወደ ስራ መግባቱን አቶ ፍቃዱ አውስተው፣ ይህ ኮሚቴ ትኩረት የሚያደርግባቸው ዋና ዋና ዘርፎች ተለይተዋል ብለዋል። በዚህም መሰረት መሬት፣ ፍትህና ጸጥታ ዘርፍ፣ ገቢ፣ ፋይናንስ ጉዳዮች እና አገልግሎት አሰጣጥ ከተለዩ ዋና ዋና ዘርፎች ግንባር ቀደም መሆናቸውን ተናግረዋል።

ያም ሆኖ ግን ሙስና ዘርፈ ብዙና ውስብስብ በመሆኑ በኮሚቴና በመንግሥት ብቻ የሚሰራ ባለመሆኑ ሚዲያውና መላው ህብረተሰብ ማገዝ እንደሚኖርበት ጥሪ አቅርበዋል። በውይይቱም ከተሳታፊዎች ጥያቄዎችና አስተያየቶች የቀረቡ ሲሆን ከመድረኩም ምላሽ ተሰጥቶባቸዋል።

በወርቁ ማሩ
አዲስ ዘመን ታህሳስ 16/2015

Exit mobile version