ETHIO12.COM

ምርጫ ቦርድ ለአብን ህጋዊ ዕውቅና ሰጠ፤ ክርስቲያን ታደለ ዕውቅና መነፈጉን አድንቀው ነበር

ምርጫ ቦርድ የአማራ ብሄራዊ ንቅናቄ አብንን በሚመለከት ቀደም ሲል አልሰጥም ያለውን እውቅና መቀየሩንና ይፋ አደረገ። ታህሳስ 24 ቀን 2015 ዓ.ም ምርጫ ቦርድ ዕውቅና መንፈጉን አስመልክቶ ድርጅቱን ወክለው ፓርላማ የተመረጡትና የድርጅቱ ስራ አስፈጻሚ አቶ ክርስቲያን ታደለ ምርጫ ቦርድን አድንቀው በማህበራዊ ገጻቸው ሲጽፉ፣ ሌሎች ምርጫ ቦርድ ውሳኔውን እንዲያጤን እንደሚጠይቁ በፓርቲው ህጋዊ የማህበራዊ ገጽ ላይ ተጽፎ ነበር።

ህዝበኝነት፣ ድርጅታዊ ማዕከላዊነት መጣስ፣ መናበብ በሚገባን ጉዳይ ክህደት በሚመስል መልኩ የተደረጉ እቅስቃሴዎች እንዳሉ። በድርጅቱ ስብሰባ ላይ ግልጽ አቋም እንዲወሰድ ማቅረብ ሲገባ በግል ሌሎችን ማጠልሸት፣ የወደፊት የፖለቲካና ማህበራዊ ምንነትን በሚነካ መልኩ ስም ማጥፋት፣ ለሚዲያ ፍጆታና የራስን ስም ለመገንባት ሲባል የሚደረግ ዘመቻ አብን ውስጥ የነገሰ ችግር እነደሆነ፣ ከዚሁ ጎን ይህ ግለሰቦች ላይ ያነጣጠረ የማጠልሸት ዘመቻ በዝምታ ዝም የሚባልበት፣ ለድርጅቱ ህልውና ሲባል በትዕግስት የሚታለፍበት አግባብ እንደማይኖር፣ ደርጅቱም በዝምታ ሊያልፍ እንደማይገባ፣ ይህ ከሆነ ራስን ከመከላከል አንጻር ሁሉም የሚለው እንዳለው እጅግ በተሰላቸና በምሬት በአብን ስብሰባ ላይ ተስተውሏል።

አብን ብዙ ዋጋ ከፍሎ ያሳደጋቸውና ያበቃቸውን ፖለቲከኞችን ማሸማቀቅ እጅግ አሰልቺና፣ በማድበስበስ የታለፉ ጉዳዮችን አንስቶ ሲመክር የተሰማው አብን የምርጫ ቦርድን ውሳኔ እንደሚቃወም ባቀረበው መሰረት ምርጫ ቦርድ ውሳኔውን መቀየሩን ይፋ አድርጓል።

ምርጫ ቦርድ አብን የካቲት 14 እና 15 ባካሄደው ጠቅላላ ጉባኤ ለተመረጡት የፓርቲው አመራሮችና ጉባዔው ላሳለፋቸው ውሳኔዎች እንዲሁም ለውሳኔዎቹ ውጤቶች እውቅና አልሰጥም በማለት ሰሞኑን ያሳለፈውን ውሳኔ መቀልበሱን ይፋ ያደረገው የቀርበለትን አቤቱታ ተመልክቶ ነው።

ቦርዱ የፓርቲውን ሕልውና ለማስቀጠልና ፓርቲው ሲያከናውናቸው የቆዩ ተግባራት ዋጋ አልባ እንዳይሆኑ በማሰብ ውሳኔውን መቀየሩን የቀየረው በቀረበለት የመከራከሪያ አቤቱታ እንደሆነ ነው የተሰማው። ዋዜማ ባያብራራውም ዜናውን ይፋ ለማድረግ ቀዳሚ ነው።

ሕዝበኝነትና ተራ ታዋቂነት ማራመድ፣ ከጀርባ ሆኖ ድርጅቱን መብላት፣ ድርጅቱ የማያምንበትንና ከድርጅቱ አቋም በዘለለ ደንብና መመሪያ እየጣሱ ልዩ ተቆርቋሪ በመምሰል የግል ፍላጎትን ማራመድ፣ የአብን ችግር እንደሆነ በርካታ አመራሩ ሲናገሩ ከርመዋል። ድርጅቱ አጀንዳ እንዲይዙ ሲማጸን ዝምታ መርጠው ውይይት ሲጀመር፣ ” አጀንዳ ማስያዝ ባይቻልም ለታሪክ እንዲሆን” በሚል አዲስ አሳብ በማራመድ፣ ይህንኑ ቪዲዮ ሆን ብሎ ለታች አመራር በማሰራጨት ሌሎችን ለማጠልሸት የተካሄደበት አግባብ የተስተዋለበት አብን፣ ምርጫ ቦርድ ውሳኔውን ማሻሻሉን አስመልክቶ ይህ ዜና ሲጻፍ ይፋ አልሆነም።

የአብን ዳግም ልደት!” ሲሉ አቶ ክርስቲያን ምርጫ ቦርድን አወድሰው የሚከተለውን በማህበራዊ ገጻቸው አስፍረው ነበር።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ እጅግ ዘግይቶም ቢሆን የወሰነው ውሳኔ ንቅናቄያችንን የሚታደግና ወደ ትክክለኛው መስመር የመለሰ ሆኖ አግኝቼዋለሁ።

በዚህ የምርጫ ቦርድ ውሳኔ መሰረት አብን ወደ መስራች ጉባዔው ውሳኔዎች በመመለስ የኢትዮጵያ የምርጫ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባና የምርጫ ስነምግባር አዋጅ 1162/2011 የሚጠይቀውን ፎርማሊቲ ለማሟላት አዲስ ጠቅላላ ጉባኤ የሚጠራ ይሆናል።

የምርጫ ቦርድ ውሳኔ በተለይም በየደረጃው ላሉ ለውጥ ናፋቂ የንቅናቄያችን አመራሮች፣ አባላትና ደጋፊዎች ፓርቲውን ወደፊት በማስቀጠል ለአገርና ሕዝብ የሚያደርገውን ትግል በአዲስ ተስፋ እና በጽኑ ቁርጠኝነት እንዲነሳሱ የሚያስችል ነው።

አቶ ክርስቲያን ምርጫ ቦርድ ውሳኔውን መቀየሩን አስመልክቶ ለጊዜው ያሉት ነገር የለም።

አጭር ማብራሪያ” በሚል ምርጫ ቦርድን ተቃውሞ የሚከተለውን ጽፎ ነበር።

ምርጫ ቦርድ በቁጥር አ1162/11/812 ታኅሣሥ 14 ቀን 2015 ዓ.ም በጻፈው ደብዳቤ የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) ፓርቲው የፊታችን ታህሳስ 22 እና 23 2015 ዓ.ም ለማካሄድ እየተዘጋጀበት ያለውን ጠቅላላ ጉባኤ አስመልክቶ የውሳኔ ሀሳብ በደብዳቤ ገልጾልናል። የድርጅታችን ከፍተኛ አመራሮች ዛሬ ታኅሣሥ 14 ቀን 2015 ከቦርዱ ከፍተኛ አመራሮች ጋር በደብዳቤው መንፈስና ይዘት ላይ ውይይት አድርገዋል። በዚሁ መሠረትም ከቦርዱ የተገለጸልን:-

1) የካቲት 14-15/2012 ዓ.ም በደብረብርሀን ከተማ ድርጅታችን ያካሄደውን 2ኛ መደበኛ ጉባኤና ውጤቱን ያላጸደቀው መሆኑን፤

2) በደብረብርሀን ጉባኤ የጸደቀውን የድርጅታችን ህገደንብ፣ የተቋቋመውን ማዕከላዊ ኮሚቴ፣ ኦዲትና ቁጥጥር እና የብሄራዊ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴውን እውቅና እንዳልሰጡት፤

3) እውቅና የሚሰጡት አብን ሰኔ 3 ቀን 2010 ዓ.ም ያጸደቀውን ህገደንብ፣ ብሄራዊ ምክር ቤት እና ሌሎች የፓርቲው አካላትን እንደሆነ አሳውቀውናል።

በዚሁ መሠረት የድርጅታችን ማዕከላዊ ኮሚቴ ነሀሴ 7 ቀን 2014 ዓ.ም ያደረገው አስቸኳይ ስብሰባ ላይ ከተገኙት 23 አብላጫ የማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት ውስጥ የተገኙት 8 የቀድሞው የብሄራዊ ምክር ቤት አባላት ብቻ ናቸው በማለት የስብሰባውን ውጤት ያልተቀበሉት መሆኑንና አብን ብሄራዊ ምክርቤት እንጅ ማዕከላዊ ኮሚቴ የሚባል በምርጫ ቦርድ የታወቀ አካል እንደሌለው ተገልጾልናል።

ይህ ማለት ከደብረብርሀን ጉባኤ( የካቲት 14-15/2012 ዓ.ም) ጀምሮ ድርጅታችን ሲገዛበት የቆየው ህገደንብ፣ ደንቡን መሠረት አድርገው የተቋቋሙ አካላት ማለትም የማዕከላዊ ኮሚቴ፣ ኦዲትና ቁጥጥር ኮሚሽን፣ የብሄራዊ ሥራ አስፈጻሚ እና ፓርቲው ላለፉት ሶስት አመታት ያካሄደው ትግልና ያሳለፋቸው ታሪካዊ ውሳኔዎች፣ በ6ኛው አገርአቀፍ ምርጫ ድርጅታችን ያደረገውን ተሳትፎና ያስመዘገበውን ውጤት ጨምሮ እንዳልነበሩና እንደሌሉ የሚያስቆጥር ሆኖ አግኝተነዋል። ቦርዱ ላለፉት ሶስት አመታት ከድርጅታችን ጋር ሲያደርጋቸው የነበሩ ሰፊ ህጋዊና አስተዳደራዊ ግንኙነቶችን ፣ ትዕዛዞችና አቅጣጫወችን ጭምር ጨርሶ እንዳልነበሩ የቆጠረ ሆኖ አግኝተነዋል።

በዚሁም መሠረት ንቅናቄአችን በቦርዱ የተሰጠው አስተዳደራዊ ውሳኔ በአስቸኳይ ታይቶ ይታረም ዘንድ ማስረጃወችን አጠናቅሮ ለማስገባት በዝግጅት ላይ መሆኑን ለአባላትና ለደጋፊወቻችን ማሳወቅ ይወዳል።

የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን)

ታህሳስ 14 ቀን 2015 ዓ.ም

አዲስ አበባ ፣ ሸዋ ፣ ኢትዮጵያ

Exit mobile version