Site icon ETHIO12.COM

የልጃቸውን መሞት የማያውቁት እናት

የምድራችንን ታላቅ ባለታሪክ የሰጡን እናት ግን የልጃቸውን መሞት ዛሬም ከቀናት በኋላ አያውቁም።
መላው አለም ሃዘኑን እየገለፀ እርሳቸው ግን ስለሆነው ፣ እየሆነም ስላለው ነገር አንዳችም የሚያውቁት የለም።


(ሰላም ሙሉጌታ)

ከአንድ ወር በፊት በህዳር ወር መጨረሻ ሴሊስቴስ አራሜንቶስ 100 አመት የሞላቸው ። እኝህ ሴት የኤዲሰን አራንቴስ ዶ ናሲሜንቶ -ፔሌ እናት ናቸው።

እናት ሴሊስቴስ 100 ኛ አመት በሞላቸው እለት ልጃቸው ፔሌ ደግሞ ሞት አፋፍ ላይ ካደረሰው የካንሰር ህመሙ ጋር ብርቱ ትግል ውስጥ ነበር። ይሁንና እርሱም ሆነ በዙሪያው ያሉ ሁሉ ቀኑን እንዲሁ ማለፍ አልተቻለቸውም ።

ፔሌ በዚያን ሰሞን አብዛኛው የሰውነት ክፍሎቹ ስራ እያቆሙ ፅኑ ህመም ላይ የነበረ ቢሆንም፣ ከህመሙ ጋር እየታገለ የእናቱን 100ኛ አመት የልደት በአል ከቤተሰቡ እና ወዳጅ ዘመዶቹ ጋር አክብሯል ።

ፔሌ በእለቱም የእናቱን ፎቶዎች በኢንስታግራም ገፁ ያጋራ ሲሆን ፣ እዚያው ላይ ተከታዩን መልዕክት በፅሁፍ ለእናቱ አስተላልፎ ነበር ፤ ” የፍቅር እና የሰላምን ዋጋ አስተምረሽ አሳድገሺኛል ፤ አንቺን ለመውደድ እና አንቺን ለማመስገን ከመቶ በላይ ምክኒያቶች አሉኝ። “

ይህ መልዕክቱ የብዙ አድናቂዎቹን ስሜት የነካ ነበር ፤ በህይወቱ ማብቂያ ጫፍ ላይ የሚገኝ መሆኑ ግልፅ እየሆነ በመምጣቱ።

ከአንድ ወር ከሃያ ቀን በኋላ የተፈራው ሆኗል ፤ ፈጣሪ የመረጠውን ነፍስ ወሰደ። ታላቁ ፔሌ እስከ ወዲያኛው አሸለበ !

አለም ስንብቱን የሰማው በጥቂት ደቂቃዎች ውስጥ ነበር። የምድራችንን ታላቅ ባለታሪክ የሰጡን እናት ግን የልጃቸውን መሞት ዛሬም ከቀናት በኋላ አያውቁም።
መላው አለም ሃዘኑን እየገለፀ እርሳቸው ግን ስለሆነው ፣ እየሆነም ስላለው ነገር አንዳችም የሚያውቁት የለም።

ሴሌስቴስ አራንቴስ የሶስት ልጆች እናት ሲሆኑ የበኩር ልጃው ፔሌ ነበር፤ ሶስተኛዋ ልጃቸው ደግሞ ማሪያ ሉሲያ ዳ ናሲሜንቶ ናት።

ሰሞኑን ብዙዎች ማሪያን ሲያስጨንቋት ነበር ። ፔሌ በ82 አመቱ ይህን አለም ሲሰናበት እናት 100አመት ሞልቷቸው ዛሬም በህይወት አሉና ፤ ሃዘኑ እንዴት አርጓቸው እንደሆነ በርካቶች ሲጠይቋት ሰንብተዋል።

እናም ማርያ ትላንት ለሚድያዎች ስለእናታቸው ሁኔታ የሰጠችው መረጃ የሃዘኑን ድባብ ከፍ ያደረገ ሆኗል።
እናታቸው ልጃቸው ፔሌ ቀድሟቸው ከቀናት በፊት ይህን አለም መሰናበቱን እንደማያውቁ ማሪያ ተናግራለች።

” ስለ ፔሌ መሞት ለእናታችን ብንነግራትም ስለሆነው ነገር ምንም አልተረዳችንም ” ብላለች ማርያ። እርሷ እንዳለችው እናታቸው ከእድሜ ጋር ተያይዞ የአይምሮ ንቃታቸው ተዳክሟል ፤ በዚህም ምክኒያት ነገሮችን መገንዘብ እያቆሙ ናቸው።

ፔሌ መሞቱን ማሪያ ለእናታቸው አራንቴስ ስትነግር የነበራቸውን ስሜት እና የሰጧትን ምላሽ ይበልጥ ስትገልፅ ” ጠጋ ብዬ በተኛችበት ‘ዴኮ’ የሚለውን የፔሌን የልጅነት ስም ስጠራላት አይኖቿን በትንሹ ገለጠች ፤ ቀጠልኩና ለእርሱ ፀሎት ለማድረግ ልንሄድ መሆኑንም ነገርኳት ። ሆኖም ምንም ያሳየችኝ ምላሽ የለም ፤ አይምሮዋ ንቁ አይደለም ” በማለት አሳዛኙን ታሪክ ተናግራለች።

ፔሌ የአለም ነው እና ሃዘኑም የአለም ነው ፤ በክብር ሊሸኝም ነገሮች ተሰናድተዋል።

ይህን ሁሉ የማያውቁት እናት ሴሊስቴስ በመኖር እና ባለመኖር መኸል ሆነው የበኩር ልጃቸውን አፈር ያለብሳሉ።

እድሜን ከጤና ጋር ይስጠን

Exit mobile version