Site icon ETHIO12.COM

ጎርጎራ – የዐቢይ ሙሽራ

የገበታ ለሀገር ፕሮግራም አካል የሆነው የጎርጎራ ፕሮጀክት የማጠናቀቂያ ምዕራፍ ሥራዎች እየተከናወኑ መሆኑን የፕሮጀክቱ ሥራ አስኪያጅ ዶክተር ፍስሐ አሰፋ ገለፁ።

በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ ሃሳብ አመንጪነት ከሚከናወኑ የገበታ ለአገር ፕሮጀክቶች መካከል የጎርጎራ ፕሮጀክት አንዱ መሆኑ ይታወቃል።

የጎርጎራ ፕሮጀክት በተለይም የሰሜን ኢትዮጵያን የቱሪዝም መዳረሻነት ይበልጥ በማስፋትና በማጠናከር ጉልህ ፋይዳ ይኖረዋል የተባለ ሀገራዊ የልማት ፕሮጀክት ነው።

የፕሮጀክቱን አጠቃላይ ክንውን እና አሁን ያለበትን ደረጃ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የሥራ ኃላፊዎች፣ የሚሲዮን መሪዎችና የተጠሪ ተቋማት የሥራ ኃላፊዎች በስፍራው በመገኘት ጎብኝተዋል።

የፕሮጀክቱን በጥራትና በፍጥነት መከናወን ያደነቁት አምባሳደሮቹ ለኢትዮጵያ የቱሪዝም እድገት ወደ ፊት መራመድ የሚችል ቋሚ ቅርስ መሆኑንም ተናግረዋል።

የጎርጎራ ፕሮጀክት ሥራ አስኪያጅ ዶክተር ፍስሐ አሰፋ፤ የፕሮጀክቱ ክንውን በጥራትና በፍጥነት በጥሩ ሁኔታ እየተከናወነ መሆኑን ገልጸዋል።

በጣና ሐይቅ ላይ የተገነባውን አንፊ ቴአትር ጨምሮ ሬስቶራንቶች፣ ወደብ እና ሌሎች አገልግሎት መስጫ ግንባታዎች መጠናቀቃቸውንም አብራርተዋል።

የፕሮጀክቱ አካል የሆነው የመንገድ ግንባታ መጠናቀቁን ጠቅሰው፤ ቀሪ የግንባታ ስራዎችም የማጠናቀቂያ ምዕራፍ ላይ ይገኛሉ ነው ያሉት።

የማጠናቀቂያ የግንባታ ስራዎች በአጭር ጊዜ የሚከናወኑ መሆኑን ጠቁመው፤ አጠቃላይ ሥራውን በሶስት ወራት ውስጥ አጠናቆ ለማስረከብ ሌት ከቀን እየተሠራ ነው ብለዋል።

የጎርጎራ ፕሮጀክት ሲጠናቀቅ ዘመናዊ ግንባታ ታክሎበት በማራኪ ገጽታና የመልክአ ምድር አቀማመጡ በኢትዮጵያ አስደናቂ ከሚባሉ ስፍራዎች መካከል አንዱ እንደሚሆን ሠራ አስኪያጁ ተናግረዋል።

በጣና ሐይቅ ምዕራባዊ ዳርቻ የሚገኘው ጎርጎራ፣ በደቡብ ምዕራብ ሸዋ የሚገኘው ወንጪ እና በኮንታ የሚገኘው ኮይሻ የገበታ ለሀገር ፕሮጀክቶች መሆናቸው ይታወቃል ሲል ኢዜአ እና አሚኮ ዘግበዋል።

ጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ

Exit mobile version