Site icon ETHIO12.COM

ሰብለ ንጉሴን  ሳኒታይዘር በማርከፍከፍ ተቃጥላ  እንድትሞት ያደረገው ዳግማዊ አራጋው  በሞት ተቀጣ 

በኢ.ፌ.ዲ.ሪ ፍትህ ሚኒስቴር የጠቅላይ ዐቃቤ ህግ ዘርፍ በሴቶችና ህጻናት ላይ የሚፈጸሙ ወንጀል ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዐቃቤ ህግ ዳግማዊ አራጋው በተባለው ግለሰብ ላይ በፈጸመው ከባድ የግድያ ወንጀል በፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 1ኛ የሰው ግድያና ከባድ ውንብድና ወንጀል ችሎት ክስ መስርቶ የክርክር ሂደቱን ሲያካሂድ ቆይቷል፡፡

ተከሳሽ በፍቅር ግንኙነት አብራው የምትኖረውን ሟች ሰብለ ንጉሴን በመካከላቸው በተፈጠረ አለመግባባት በእጁ ይዞት በነበረው የቤት ቁልፍ ደጋግሞ ግንባሯ ላይ እንዲሁም ፊትዋንም ደጋግሞ በጥፊ መምታቱን በክሱ ላይ ተመላክቷል፡፡

በቢላ የግራ እግሯ የታችኛው ክፍል ወይም መርገጫዋን እና የቀኝ እጅ ትንሽዋ ጣቷ ላይ በመውጋት ጥልቀት የሌለው የቆዳ መቆረጥ እንዲደርስባት ካደረገ በኃላ ሳኒታይዘር ሰውነትዋ ላይ በማርከፍከፍ ክብሪት ለኩሶ ፊትዋ፣ አንገትዋ፣ የደረት ሶስተኛ ክፍሏ፣ ሆዷ፣ እጆቿ እና እግሮቿ በእሳት እንዲቃጠል ማድረጉንም የወንጀል አፈጻጸም ድርጊቱ ያስረዳል፡፡
በአደጋ ምክኒያትም የተቃጠለው ሰውነትዋ ኢንፌክሽን ፈጥሮ ኢንፌክሽኑ ወደ ሳምባዋ እና አእምሮዋ ተዛምቶ የደም ዝውውሯና የእስትንፋስ ስርዓቷ ተቋርጦ ህይወትዋ ሊያልፍ ችሏል፡፡
ተከሳሽ ክሱን ማስተባበል ባለመቻሉ ጥፋተኛ ነህ በማለት የፍርድ ውሳኔውን ያስተላለፈ ሲሆን በዛሬው ዕለት የተሰየመው የፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 1ኛ የሰው ግድያና ከባድ ውንብድና የወንጀል ችሎትም በከሳሽ ዐቃቤ ህግ የቀረቡ ማስረጃዎችን እና በተከሳሽ የቀረቡ የመከላከያ ማስረጃዎች መዝኖ ተከሳሹ ጥፋተኛ መሆኑን የዐቃቤ ህግ ማስረጃ በበቂ ያስረዳ በመሆኑ  ተከሳሽ በሞት እንዲቀጣ ሲል የቅጣት ውሳኔውን አስተላልፏል፡፡

Exit mobile version