Site icon ETHIO12.COM

“የትናንት ዘር፣ የዛሬ ፍሬ፣ የነገ ስንቅ!” ዐቢይ አሕመድ

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አሕመድ ኢትዮጵያ ውስጥ አሁን ላይ ይፋ እየወጡ ያሉ ችግሮች አስመልክቶ ጽሁፍ አሰራጭተዋል። ለውቅቱ ችግር ሰሞኑንን ይፋ የሆነውን የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ውጤት እንደ ምሳሌ አድርገው ያነሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ “አለባብሰው ቢያርሱ በአረም ይመለሱ” እንደሚባለው ነውና ልክ የትምህርት አውዱ ላይ በድፍረት የሚሰሩ እንድተገኙ ሁሉ በሌሎችም የተጠራቀሙ ስብራቶች ላይ ተመሳሳይ ስራ መስራት አማራጭ የሌለው ጉዳይ እንደሆነ አስገንዝበዋል።

ለካቢኒያቸው ከሰጡት ማብራሪያ ቀጥሎ ባሰራጩት ጽሁፍ የተከማቹ ችግሮች፣ በአንድ ጀንበር መፍትሄ ባይሰጣቸውም፣ በድፍረት ስብራቶችን በሙሉ ለማስተካከል እንደሚሰራ አስገንዝበዋል። ለዚህም ውጤታማነት ሁሉም የበኩሉን እንዲያበረክት ጠይቀዋል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በወቅታዊው ጉዳዮች ላይ ያስተላለፉት መልዕክት እንደሚከተለው ቀርቧል፦

አንድ ነገር የሚፈጠርበትና የሚታወቅበት ወቅት ሊለያይ ይችላል። ጽንስ ከተፈጠረ ከወራት በኋላ እርግዝና ሆኖ ይታያል፤ ሕጻን ሆኖ ለመወለድ ደግሞ ተጨማሪ ጊዜያትን ይወስዳል። የተወለደ ሕጻን አድጎና ጎልብቶ፣ ስብዕናውና ባህርይው ሙሉ ለሙሉ የሚታወቀው ደግሞ ከዓመታት በኋላ ነው። የሕይወት ትልቁ ምስጢር፣ ትናንት በማይታየው ጽንስና በጨቅላው ሕጻን ውስጥ የዛሬው ትልቅ ሰው ተሰውሮ መኖሩና ማደጉ ነው። የነገውን ማንነትና ውጤት ዛሬ የሚደረጉ እርምጃዎችና ማስተካከያዎች ሊቀርጹትና ሊያርሙት መቻላቸው ደግሞ ተስፋ የሚሰጥ እውነታ ነው።

የሰብልም ሆነ የአረም ዘር በእርሻ መሬት ውስጥ የሚኖርበትና፣ በቅሎና አድጎ የሚገለጥበት ጊዜ የተለያየ ነው። ዛፉ በዘሩ ውስጥ ይኖራል፤ እንደሚያገኘው አፈር፣ አየር፣ ብርሃንና እንክብካቤ በጊዜ ሂደት ውስጥ ሙሉ ማንነቱ ይገለጣል። ልክ እንደ ሥነ ሕይወታዊ ዘር ሁሉ፣ በማኅበረሰብ ውስጥ የሚዘራ የሐሳብ ዘርም አድጎና ጎልብቶ፣ አብቦና አፍርቶ በሰዎች ዙሪያ ተጨባጭ ሆኖ ለመገለጥ ዘለግ ያለ ጊዜ ይፈጃል። ለዚያም ነው ያልተገለጠን ነገር እንደሌለ አድርጎ የመውሰድ፣ አልፎ ተርፎም ነገሩ በተገለጠበት ጊዜ እንደ ተፈጠረ አድርጎ የመገንዘብ ዝንባሌ ስህተት የሚሆነው።

በተለይ ሥርዓታዊ ለውጥ፣ በጎም ሆነ ክፉ ውጤቱ በአጭር ጊዜ አይታይም፤ አይመዘንምም። ለለውጡ መነሻ የሆኑ ሐሳቦች በግለሰቦች ውስጥ ሠርጾ፤ ልማድና ሥርዓት ሆኖ፤ የማኅበረሰቡ ማንነት መገለጫ ባህል እስከሚሆን ድረስ ዘመናት ይፈጃል። ለውጡ የሚያስከትላቸው ስብራቶችም ሆኑ ትሩፋቶች የሚታወቁት በትውልድ ቅብብሎሽ ውስጥ ነው። ጉዳዩ ከግለሰቦች ሐሳብነት ተነስቶ ፖሊሲ፣ ስትራቴጂና ዕቅድ ሆኖ ሲተገበር÷ ቀስ በቀስ እየተዋሃደ አሠራር፣ አኗኗር፣ ልማድና ባህሪይ ይሆናል። እንደ ወረርሽኝ በጥቂቶች ጀምሮ ብዙኃንን ይወርሳል። ከአንድ አካባቢ ተነስቶ ሀገርን ያዳርሳል። ይሄንን የለውጥ ሂደት መረዳት ላልቻሉ፤ ጅማሬውንና ዕድገቱን በትክክል ለማያስተውሉ የሚፈጠሩ ለውጦች ሁሉ ድንገቴና ማኅበረሰባዊ ድንጋጤን የሚያስከትሉ ናቸው።

በቅርቡ በሁለተኛ ደረጃ ትምህርት የመልቅቂያ ፈተና የተገኘው ውጤት ለዚህ ጥሩ ማሳያ ነው። ከብዙ ጥናትና ሙግት በኋላ ኩረጃና ሥርቆትን በከፍተኛ ሁኔታ ለመቀነስ ተግባራዊ የተደረገው የተማከለ የፈተና ስልት ያስገኘው ውጤት ከፍተኛ ማኅበረሰባዊ መደናገጥን ሲፈጥር ታይቷል። ከተፈታኞቹ ሃምሳ ከመቶና ከዚያ በላይ ጥያቄዎቹን መልሰው ለማለፍ የቻሉት ተማሪዎች ቁጥር እጅግ አናሳ ናቸው። በሺህ የሚቆጠሩ ትምህርት ቤቶች አንድ ተማሪ እንኳን ለማሳለፍ ያልቻሉበት ሁኔታ ተፈጠረ። ይህም የትምህርት ጥራት ላይ ያሉብንን ችግሮችና ያለንበትን ቀውስ ፍንትው አድርጎ አሳየን። የችግሩን ልክ በአግባቡ፣ በአሐዝ መረጃ የተገነዘበነው እና ያየነው አሁን ቢሆንም፣ ችግሩ ግን በፈተናው የተገለጠ እንጂ የተፈጠረ አይደለም። የትምህርት ሥርዓቱ ስብራት ዛሬ የተፈተኑትን ተማሪዎች የሚያስተምሩ አስተማሪዎች ከተመለመሉበት፣ ከሠለጠኑበት መንገድ፣ አጠቃላይ የትምህርት ሥርዓቱ ከተመራበት ፖሊሲና አቅጣጫ እና ከሌሎች ብዙ ጉዳዮች ጋር የተያይዘ፤ ባለፉት አሥርት አመታት የሄድንበት የተንሻፈፈ ጉዞ ውጤት ነው። ዛሬ የችግር ሰብሉን ብናጭድም ዘሩ አፈር ነክቶ መብቀል ከጀመረ ዘመናት ተቆጥረዋል። ከዚህ ጋር ተያይዞ አንድ እውነት ማወቅ አለብን፤ ችግሩ በአንድ ሌሊት እንዳልተፈጠረ ሁሉ መፍትሔውም በአንድ አዳር ሊመጣ አይችልም። ዛሬ ከአበባ አልፎ ፍሬውን ያየነውን የትምህርት ችግር ቀልብሶ ለማስተካከል ረጅም ጊዜና ከባድ ዋጋ ይጠይቃል። እንዲህ ያለው ስብራት በአንድ ዘርፍ ብቻ ያለ ችግር ነው ብሎ ማሰብ ሥህተት ነው።

ልክ በትምህርት ዘርፉ ላይ መዛነፎች እንዳሉብን ሁሉ÷ በፖለቲካው፣ በኢኮኖሚው፣ በማኅበራዊው፣ በፍትሕም ሆነ በጸጥታ ዘርፍ በተመሳሳይ ለረጅም ጊዜ የዘለቁ ስብራቶች አሉብን። ዘላቂነትንና አዋጪነትን ታሳቢ ያላደረጉ ብድሮች፣ ደካማ የፕሮጀክት አፈጻጸሞች፣ ብክነትና ሥርቆት፣ የተቋማት መቀንጨር፣ እጅግ ከፋፋይ የፖለቲካ ትርክትና ጽንፍ የወጣ ብሔርተኝነት፣ በእምነት ተቋማትና በማኅበራዊ ተቋማት ውስጥ ያሉ ፈተናዎች፣ በውጭ ግንኙነት የነበሩ ድክመቶች፣ በሞራልና ዕሴቶች ላይ የደረሱ ስብራቶች፣ ወዘተ. ባለፉት ብዙ አሥርት ዓመታት በሂደት ተፈጥረውና ተንሰራፍተው ቆይተዋል። እነዚህን ስብራቶች ልክ እንደ ትምህርት ሥርዓቱ የሚጋፈጣቸው ካላገኙ ሳይገለጡ የመኖርና ለድርብርብ ችግሮች መነሻ የመሆን ዕድላቸው ሰፊ ነው።

አንድ ገበሬ ዘሩን ከመዝራቱ በፊት በእርሻ ወቅት ነቅሎና ጎልጉሎ ያልጣላቸው የአረም ሰርዶዎች ሥርአቸውን ከመሬት በታች ቀብረው የሌሉ ቢመስሉም፤ ዋናውን ችግር የሚፈጥሩት የኋላ ኋላ ለመልካም ዘሩ የሚፈስሰውን ውሃና ማዳበሪያ ተሻምተው ካደጉ በኋላ ነው። በዚህም የተነሳ ያ ገበሬ ቀድሞ መንቀልና መጎልጎል በተገባው ጊዜ ከሚያፈስሰው ጉልበት በላይ ዋጋ ከፍሎ በአረም ወቅት ለዳግም ልፋት ይዳረጋል። ለዚያም ነው ማኅበረሰባችን ለረጅም ዘመን ካዳበረው እውቀት ተነስቶ “አለባብሰው ቢያርሱ በአረም ይመለሱ” የሚለው። ትናንት እንደ ሀገር ነቅሰን ያልጣልናቸው ፖለቲካዊና ማኅበራዊ አረሞች የሌሉ እስኪመስሉ ድረስ ሥራቸውን ደብቀው በመቆየታቸው፣ አሁን ምቹ አጋጣሚዎችን እየጠበቁ ለመልካም ልምምዶች የሚንፈስሳቸውን ፖለቲካዊ ወረቶች ሲሻሙ እያስተዋልን ነው።

ባለፉት ብዙ አሥርት ዓመታት በአፈናና በጉልበት ችግሩን ሸፋፍነነው የሌለ ቢመስለንም፣ ከፋፋይ የሆነው ትርክትና ጽንፍ የረገጠው ብሔርተኝነት ወርሶን ነበር። ዛሬ አንጻራዊ ነጻነት ሲኖር የችግሩን ልክ አካል ነሥቶ አየነው። የጸጥታና የፍትሕ ተቋሞቻችን በአግባቡ ተቋም ሆነው ተገቢው ዐቅምና ቁመና ሳይኖራቸው፣ በማስፈራራትና በአምባገነናዊ ዐውድ ልክ እንደ ፀጉራም ውሻ ከባድ ጡንቻ ያላቸው መሰለው ይኖሩ ነበር። በነጻነትና ዴሞክራሲያዊ ዐውድ ሲፈተኑ ግን ስብራታቸው ጎልቶ ፈጥጦ ወጣ። በምዝበራ ተቦጥቡጦ፣ በብድር ጫና ደቅቆ የነበረው ኢኮኖሚ በዕድገት አመላካች ቁጥሮች ተጀቡኖ ሲጨበጨብለት ነበር፤ የተበደራችሁትን ክፈሉ ሲባል፣ የሕዝን ኑሮ ማሻሻል ሲሳነው፣ የሥራ ፈላጊዎችን የሥራ ፍላጎት በከፊል እንኳን ማሟላት ሲያቅተው የስብራቱ ልክ ተጋለጠ። ችግሮቹ ሥር የሰደዱ ቢሆኑም፤ ልካቸው ጎልቶ የታየውና የወጣው ሥርዓቱ በአንፃራዊ ነጻነት ሲፈተሽ ነው። ነጻነት በሌለበት፣ ሁሉም ታፍኖና ተዘግቶ በፍርሃት በተሸበበበት፣ ጭራሽ ችግሮቹ ጌጥ መስለው ሊታዩ ይችላሉ። እውነቱ ግን ውስጥ ለውስጥ ሥሩ መሬት ሲቆነጥጥና ድር ሲያደራ ቆይቶ የሀገርን ህልውና ሊገዘግዝ ጥርስ ሲያበቅል ነበር።

አሁን ከትምህርት ሥርዓቱ አንፃር ላለፉት ብዙ ዓመታት የሄድንበት መንገድና ውጤቱን መረዳት ብንችልም፣ ችግሩን ለማሻሻል ግን ገና ብዙ ጊዜ የሚፈጅ ሥራ ይጠብቀናል። ችግሩን ዐውቀነዋል ማለት ዛሬዉኑ ፈትተን እንጨርሰዋለን ማለት አይደለም። በኢኮኖሚውምና በፖለቲካ ሥርዓታችን ተመሳሳይ ሥራ ይጠብቀናል። በዴሞክራሲና በነጻነት ጥያቄዎች ምክንያት ሲንገዳገዱ ያየናቸው ፖለቲካዊና ማኅበራዊ ተቋሞቻችን አቅማቸው የት ድረስ እንደሆነ እያየን ነው። የሥራ ፈጠራና የብድር አከፋፈል አቅማችንም የኢኮኖሚያዊ ሥርዓታችንን ደካማነት ቁልጭ አድርገው አሳይተውናል። የችግሩን ልክ ዛሬ ብንረዳም፣ ችግሩ ዛሬ እንዳልተፈጠረ እያሰብንና የመፍትሔ ምንጮች እኛ የዛሬዎቹ ትውልዶች መሆናችንን እያመንን በኃላፊነት እንሠራለን። የስብራቶቻችንን ልክና የችግሮቻችንን ጥልቀት በሚገባ ተረድተን የማሻሻያ ርምጃዎችንም ተግባራዊ በማድረግ ላይ እንገኛለን።

ለረዥም ዘመን ሳይገለጥ፣ አልፎ ተርፎም እንደ ትክክለኛ ነገር ሲቆጠር የኖረን ማኅበራዊ ስብራት በሆነ አጋጣሚ ተገልጦ ፊት ለፊት ሲጋፈጡት በመጀመሪያ በድንጋጤ ተውጦ የሚያደርጉት ቢጠፋ እምብዛም አይደንቅም፤ ተፈጥሯዊ ምላሽም ነው።

ነገር ግን ጉዳዩንና የነገሩን መሠረት ለመካድ መሞከር ወይም ሰንካላ ሰበብ እያስቀመጡ ማለፍ ለችግሮች ዘላቂ መፍትሔ አያመጣም። ለወባ በሽታ የወባ መድኃኒት እንጂ፣ ገና ለገና በሽታው እንደ ራስ ምታትና ብርድ ብርድ የማለት ምልክቶችን አሳየ ተብሎ የብርድና የራስ ምታት ማስታገሻ መድኃኒቶችን እንደ ዘላቂ መፍትሔ አይወሰድም። ችግሮች ሲገጥሙ ጣት መጠቆምና በቀዳዳ ሾልኮ ማምለጥ የሞኞችና የፈሪዎች መፍትሔ ሲሆን፤ ትክክለኛው የብልህና የጀግኖች መንገድ የሚያጋጥሙ ችግሮችን ፊት ለፊት ተጋፍጦ በጥበብ ለመርታት መፍጨርጨር ነው።

የትናንት ሥህተታችን የፈጠረውን የዛሬ ስብራታችንን ተረድተን ዘላቂ መፍትሔ ከሚፈጥሩት ወገን ለመሆን መዘጋጀት አለብን። በቅርብ ጊዜያት የሚያጋጥሙን ችግሮች ጥልቀታቸው በሙሉ ዐቅምና ቆራጥነት ወደ መፍትሔው እንድንገባ ሊገፋፉን ይገባል። በአዲስ ሃሳብና ጉልበት ለመገስገስ ተስፋ ሰንቀን እንነሳ፤ ለላቀ ለውጥና ለተሻለ ነገ እንትጋ። እንደ ሀገርና እንደ ማኅበረሰብ የሚያዋጣን መንገድ ይሄ ነው። ከትናንት የወረስናቸውን ሥህተቶች ነቅሰን ከጣልንና በምትኩ ዛሬ መልካም ዘር ከዘራን÷ ያለ ጥርጥር ልፋታችን መልካም ፍሬ ያፈራል፤ ለልጅ ልጆቻችንም የተስፋ ስንቅ ይሆናቸዋል።

ኢትዮጵያ በልጆቿ ጥረት ታፍራና ተከብራ ለዘላለም ትኑር!!
ፈጣሪ ኢትዮጵያና ሕዝቦቿን ይባርክ!
ጥር 25፣ 2015 ዓ.ም

Exit mobile version