Site icon ETHIO12.COM

በትግራይ ዩኒቨርሲቲዎችን ዳግም ስራ ለማስጀመር ዝግጅት ተደረገ

በትግራይ ክልል የሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎችን ዳግም ስራ ለማስጀመር አስፈላጊው ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን የትምህርት ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡

በሚኒስቴሩ የሕዝብ ግንኙነት እና ኮሙኒኬሽን ስራ አስፈጻሚ አመለወርቅ ሕዝቅኤል እንደገለጹት፥ የሰላም ስምምነቱን ተከትሎ በትግራይ ክልል የሚገኙ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማትን ዳግም ስራ ለማስጀመር በቅንጅት እየተሰራ ነው፡፡

በዚህም መሰረት መጀመሪያ የባለሙያዎችና ቀጥሎም አምስት አባላት ያሉት የአመራር ቡድን በክልሉ በሚገኙ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማትን በቦታው በመሄድ የጉዳት ዳሰሳ ጥናት ማድረጉን አንስተዋል፡፡

ልዑካኑ ከመቀሌ፣ አክሱም፣ አዲግራትና ራያ ዩኒቨርሲቲዎች አመራሮች ጋር በፍጥነት ስራ ማስጀመር በሚቻልባቸው ሁኔታዎች ላይ መምከሩን ጠቁመዋል፡፡

የመቀሌ፣ አክሱም፣ አዲግራትና ራያ ዩኒቨርሲቲዎች ያሉበትን አጠቃላይ ሁኔታ የሚገልጽ የዳሰሳ ጥናት በዩኒቨርሲቲዎቹ አመራሮች እና አባላት ቀርቦ ውይይት መደረጉንም ተናግረዋል፡፡

በተቋሙ የተቋቋመው ዓብይ ኮሚቴ ዩኒቨርሲቲዎቹ ወደነበሩበት እስከሚመለሱ የማያቋርጥ ክትትልና ድጋፍ እንዲያደርግ አቅጣጫ መቀመጡንም ስራ አስፈጻሚዋ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ተናግረዋል፡፡

ዩኒቨርሲቲዎች ከትምህርት ሚኒስቴር ጋር በጋራ በማቀድ በቀጣይ ወደ ስራ በሚገቡበት ሁኔታ ላይ ከስምምነት ላይ መድረሳቸውንም አረጋግጠዋል ሲል ኤፍቢሲ ዘግቧል፡፡

Exit mobile version