Site icon ETHIO12.COM

3.8 ኪሎ ግራም ወርቅ በህገወጥ መንገድ ከአገር ይዞ ሲወጣ የተያዘው ቻይናዊ ክስ ተመሰረተበት

ፈቃድ ሳይኖረው ከ18 ሚሊዮን ብር በላይ የሚያወጣ 3 ነጥብ 8 ኪሎ ግራም ጥፍጥፍ ወርቅ በህገ-ወጥ መንገድ ከአገር ይዞ ሲወጣ የተያዘው ቻይናዊ ላይ ክስ መመስረቱ በኢፌዲሪ ፍትሕ ሚኒስቴር የጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ዘርፍ የኢኮኖሚ ወንጀል ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዐቃቤ ሕግ አሰታወቀ።

ፈቃድ ሳይኖረው ከ18 ሚሊዮን ብር በላይ የሚያወጣ 3 ነጥብ 8 ኪሎ ግራም ጥፍጥፍ ወርቅ እና ኮፐር፣ ዚንክና ሲልቨር የያዘ 2 ኪሎ ግራም የሚመዝን ማዕድን በህገ-ወጥ መንገድ ይዞ ሲወጣ የተያዘው ቻይናዊ ተከሳሽ ላይ የኮንትሮባንድ ወንጀል ክስ ተመሰረተበት፡፡

የዐቃቤ ሕግ የክስ መዝገብ እንደሚያስረዳው ሚስተር ፓን ችዋን የተባለው ቻይናዊ ተከሳሽ ገደብ የተደረገበት መሆኑን እያወቀ/ማወቅ ሲገባው የብቃት ማረጋገጫ እና ፈቃድ ሳይኖረው የዋጋ ግምቱ 18 ሚሊዮን 5 ሺ 939 ብር የሚያወጣ ቀረጥና ታክስ 12 ሚሊዮን 824 ሺ 53 ብር የሚከፈልበት 3.8 ኪሎ ግራም ጥፍጥፍ ወርቅ እና 2 ሺ 196 ብር ቀረጥና ታክስ የሚከፈልበት በውስጡ ኮፐር፣ ዚንክና ሲልቨር የያዘ 2 ኪሎ ግራም የሚመዝን ማዕድን የሻንጣ የብረት ዘንግ ውስጥ አድርጎ ከኢትዮጵያ ወደ ቻይና አገር ይዞ ሲወጣ ጥር 16 ቀን 2015 ዓ.ም አዲስ አበባ ቦሌ አለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ የወጪ መንገደኞች የደህንነት ኤክስሬይ መፈተሻ ቦታ ላይ ተይዟል።

በፈፀመው ገደብ የተደረገበት ዕቃን በህገ-ወጥ መንገድ ይዞ መውጣት የኮንትሮባንድ ወንጀል የማዕድን ግብይት አዋጅ ቁጥር 1144/2011 አንቀጽ 12/1/፣ 5፣ እና 36/1/ እንዲሁም የጉሙሩክ አዋጅ ቁጥር 859/2006 (በጉሙሩክ ማሻሻያ አዋጅ ቁጥር 1160/2011 አንቀጽ 2/44/ እንደተሻሻለው) አንቀጽ 168/1/ ስር የተደነገገውን ተላልፎ የኮንትሮባንድ ወንጀል መፈፀም ክስ ቀርቦበታል፡፡

የፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 5ኛ ወንጀል ችሎትም ተከሳሹ የተከሰሰበትን ክስ ለመስማት ለየካቲት 28 ቀን 2015 ዓ.ም ቀጠሮ መሰጠቱን ከፍትህ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመለክታል። 

(ኢ ፕ ድ)

Exit mobile version