Site icon ETHIO12.COM

በትግራይ የሽግግር መንግስት ምስረታ ዋዜና ብልጽግና ከህጋዊ ፓርቲዎች ጋር በጋራ ለመስራት ዝግጁ መሆኑን አስታወቀ

የትግራይ ብልጽግና ስምና ማንነትን ስይጠቅስ በትግራይ ጉዳይ ከሚሰሩ፣ በክልሉ ካሉም ሆነ አዲስ አበባ ካሉ ፓርቲዎች ጋር በጋራ ለመስራት ዝግጁ መሆኑንን በሽግግር መንግስት ዋዜማ አስታወቀ።

የትግራይን ሕዝብ ከችግር ለማላቀቅና በክልሉ ዘላቂ ልማትን ለማረጋገጥ በክልሉ ጉዳይ ላይ ከሚሰሩ ሕጋዊ ፓርቲዎች ጋር በትብብር ለመስራት ዝግጁ መሆኑን የብልጽግና ፓርቲ የትግራይ ቅርንጫፍ አስታወቀ፡፡ በትግራይ የሚመሰረተው የሽግግር መንግሥት ከትግራይ ውጭ ያሉ ፓርቲዎችን ያቀፈና በውይይት የተመሰረተ ሊሆን እንደሚገባም ጠቁሟል፡፡

የብልጽግና ፓርቲ የትግራይ ቅርንጫፍ የፖለቲካ ዘርፍ ኃላፊ አቶ ጎይቶኦም በርሀ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለጹት፣ የትግራይ ክልል የሽግግር መንግሥት የሚመሰረተው በትግራይና አዲስ አበባ ያሉ ፓርቲዎች በጋራ በሚያደርጉት ውይይት ሲሆን ሁሉንም እኩል ያቀፈ መሆን አለበት፡፡

በትግራይ ችግር በተፈጠረበት ጊዜ ለውጡን በመደገፍ ሲሰሩ የነበሩ ፓርቲዎች እና ኃይሎችአሁንም በአዲስ መንፈስ ሕዝባቸውን ለማገልገል ዝግጁ ናቸው ያሉት አቶ ጎይቶኦም ፣ በትግራይ ከወረዳ እስከ ክልል በሚሰጠን ኃላፊነት ትግራይ ውስጥ ካሉ ፓርቲዎች ጋር ተቻችለን የምንሰራበት ዕድል ለመፍጠር ዝግጁ ነን ብለዋል፡፡

“በትግራይ ያሉት ፓርቲዎች ጤናማ ያልሆነውን ፉክክር ወደ ጎን በመተው ከሌሎች ፓርቲዎች ጋር በመሆን የትግራይን ሕዝብ ከችግር ማላቀቅ አለባቸው” ያሉት አቶ ጎይቶኦም፣ የፖለቲካ ልዩነት ያለና ወደፊትም የሚኖር ቢሆንም ለሕዝብ መስራት ግን የግድ እንደሆነ አመልክተዋል።

የሽግግር መንግሥቱን ሁሉንም ያቀፈ በማድረግ ሕዝባችንን ወደ መደበኛ ኑሮው ለመመለስና የተሻለ እድገት ለማስመዝገብ ሁላችንም ግዴታችንን መወጣት አለብን ሲሉም ጥሪ ማቅረባቸውን ያመለከተው የኢዜአ ዘገባ ብልጽግና በገሃድ በትግራይ የሽግግር መንግስት ምስረታ እንደሚሳተፍ ያስረዳል። ይሁን እንጂ ብልጽግና ለትግራይ ሕዝብ ጥቅም ሲባል በህግ ከተመዘገቡ ፓርቲዎች ጋር አብሬ እሰራለሁ ሲል ትህነግን ስለማጠቃለሉ ቃለ በቃል ያለው ነገር የለም። ትህነግ በምርጫ ቦርድ የተነፈገው እውቅና እስካሁን እንዳልተመለሰለት ይታወቃል።

Exit mobile version