ETHIO12.COM

የኦሮሚያ ክልል ከኦነግ ጋር እየተሸማገለ ነው፤ “ሸኔስ” አነጋጋሪው ጉዳይ

የኦሮሞ አባቶች፣ አባገዳዎች፣ አደ ስንቄዎችና ባለሃብቶች እንዲሁም ለሁለቱም ወገኖች ቅርብ የሆኑ ምሁራኖች ኦነግን ከቀድሞው ኦህዴድ ወይም ከአሁኑ ኦሮሚያ ብልጽግና ጋር ለማስማማት ብዙ ጥረት ሲያደርጉ ቆይተዋል። ጉዳይ በተለያዩ ምክንያቶች ቢሰናከልም የአሁኑ ለየት ያለ መሆኑን እየተሰማ ነው። “ሸኔስ?” የሚል ጥያቄ የሚያነሱ ደግሞ ጨዋታው ግልጽ እንዳልሆነላቸው እየገለጹ ሲሆን፣ በኦሮሚያ የኦነግና ገዢው ፓርቲ የሰላም ጅማሮ ስጋት የጣለባቸው ወገኖችም አሉ። ከቅርብም ከሩቅም!! የሰላሙ አግባብ የገባቸውም ያልገባቸውም አብረው ” የአማራና ኦሮሞ ብልጽግናን” የቃላት ንትርክ ሲያኝኩ ይውላሉ። ጉዳዩ የተወሰኑ ሰዎች ጩኸት እንደሆነ የገባቸው ደግሞ ጎንደር ትምህርት ቤት ያስመርቃሉ።

ማመላከቻ – ትህነግና መንግስት ከተስማሙ በሁዋላ የፖለቲካው ጎዳና ሰፊ ለውጥ አሳይቷል። ትህነግን በሃይል ለማንበርከክ ሰፊ የጦር ሃይል ተገንብቷል። የክልሎችን ልዩ ሃይል ሳያካትት ኢትዮጵያ ያላት መከላከያ በአፍሪካ ግንባር ቀደም ሆኗል። ይህ ብቻ አይደለም መከላከያ ሰራዊት የዘመኑ ቴክኖሎጂ ባለቤት ሆኗል። ዘመናዊ ጦርነት የማካሄድ ብቃትም እንዳለው አሳይቷል። ከዚሁ ጋር በተያያዘ ይመስላል ሱዳን እጇን ሰጥታለች። ኬንያ በሚገባ ወዳጅ ሆናለች። ጅቡቲና ሶማሌያም ያው ናቸው። ኤርትራ አሁን ላይ ያላት አቋም ባይታወቅም ለኢትዮጵያ በጦር ደረጃ ስጋትነቷ እዚህ ግባ የሚባል አይደለም። ኡጋንዳ እየረበሸች ቢሆንም ነገሮች መስመር እየያዙ እንደሆነ እየተሰማ ነው። ይህን የሰላም አካሄድ በዚህ ድፍን መረጃ ውስጥ መንዝሮ ማየት አግባብ ይሆናል።ከዚህም በተጨማሪ ህዝብ ስለችቶታል።

ኦነግ – የኦሮሞ ነጻ አውጪ ግንባር / የኦሮሞ ነጻ አውጪ ሰራዊት

ኦነግ ሶስት የተለያዩ መልኮች እንዳሉት በተደጋጋሚ ይገለጻል። አዲስ አበባ በሰላማዊ መንገድ እየሰራ እንደሆነ የሚናገረው ኦነግ፣ የዚህ ኦነግ ወታደራዊ ክንፍ የነበረና “ሰላማዊ መንገድ አያዋጣም” ብሎ “በሰላም ለመታገል ወስኛለሁ” ካለው ሃይል ጋር መለያየቱን የሚገልጸው ነፍጥ ያነገበ ቡድን፣ ኦነግ ሸኔ፣ ከዳውድ ኢብሳ በቅርቡ የተለዩት የእነ አቶ አራርሳ ቡድን፣ እንዲሁም ቀደም ሲል ” ኦነግ የኔ ነው” ብለው የወጡት አራት ወገኖች ይጠቀሳሉ። አሁን ላይ ዳውድ በተፈጥሮም ይሁን በሌላ ምክንያት ወደፊት የመምጣታቸው ጉዳይ ተስፋው አነስተኛ ሆኗል።

አሁን ላይ አራት ዋና መለያ መልኮች ያሉት ኦነግ ቀደ ሲል አምስት ጊዜ በመሰንጠቁ፣ ስሙን ይዘው ለመለያ በፈጠሩት ቅጥያ አቶ ዳውድ ኢብሳ የሚመሩት ” ኦነግ ሸኔ” ወይም ” አምስተኛው ኦነግ” ተባለ። አቶ ዳውድ ኢብሳ፣ አባ ነጋ፣ ገላሳ ዲልቦና ጄኔራል ከማል ገልቹ በየጊዜው እየተከፈሉ ኦነግን የተለያየ መልክ አሲዘውት ወደ አገር ቤት ሲገቡ “እንኳን ደህና መጣችሁ” የሚለው ጭብጨባ ጋብ እንዳለ ለውይይት ስብሰባ በጠሩበት ሁሉ ሕዝብ “ለምን አንድ አትሆኑም? አንድ ሁኑና ኑ” አላቸው። አንድ ከመሆን ይልቅ ብዙም ሳይቆዩ ፖለቲካውን የሚመሩትና ሰራዊቱን የሚመሩት መለያየታቸውን አስታወቁ። ሰሚው ጉዳዩን ” ይቺ ናት ጨዋታ” እያለ ዜናውን እንደየ አቋሙ በለተ።

ራሱን የኦሮሚያ ነጻ አውጪ ጦር የሚለውና በቪኦኤና ቢቢሲ በኩል ተደጋጋሚ እድል እየተሰጠው በገሃድና በውስጥ አዋቂ ስም ራሱን ” ሸኔ” ከሚለው ስያሜ በማራቅ ” ሸኔ መቆመሪያ” እንደሆነ አስታወቀ። ያመኑም፣ ያላመኑም ዜናውን እየሰሙ መሽቶ ሲነጋ አዳዲስ መረጃዎች ብቅ አሉ። በተለይም ኦሮሚያ ውስጥ አማራ በዘሩ እየተመረጠ የሚገደለው ለምንና ምክንያትና በተለየ በማን ነው? ለሚለው ግልጽ ምላሽ ባይሆንም ጨዋታው ሌላ ዕቅድ እንዳለው አመላከተ። በተለይም ከአባይ ማዶ የተነሱ ሃይሎች ምስራቅ ወለጋን ለወራት ተቆጣጥረው ብዙ ነብስ ማጥፋታቸው፣ ንብረት መዝረፋቸውና አካባቢውን ማስተዳደራቸው፣ ከዚያም በላይ ቭግር ባለባቸው የወለጋ ወረዳዎች አስተዳደሮች በአማራ ሃይሎች እንዲጠበቁ መደረጋቸው፣ ይህም ለሁለት ዓመት እንደዘለቀ ሲሰማ ” ሸኔ” የሚባለው ሃይል ከጀርባው ማን አለ? የሚል ጥያቄ አጎነ።

ሸኔ የትኛው ሃይል ነው?

በትክክል ይህ ነው ብሎ መናገር ቢያስቸግርም ” ሸኔ” የሚባለው ስያሜ ከአቶ ዳውድ ኦነግ የመለያ ስም ላይ ወይም ” ኦነግ ሸኔ” ከሚለው ላይ ተበጥሶ የተወሰደ ነው። አሁንም ድረስ የኦሮሞ ሰራዊት የሚል ክፋይ እንዳለ ይነገራል። አምስተኛው ክፋይ ለማለት ነው። አሁን እንደሚሰማው ይህ በሸኔ ስም የሚጠራው ሃይል በሰፈር ልጅ ተደራጅተው የሚዘርፉ፣ ያላቸውና ነገ እንጠየቃለን ብለው የሚፈሩ የሚረዷቸውና ዋናዎቹ ግን ከውጭ አገር ባለ ግንኙነት ስር ሆነው በየአካባቢ ማንነት ተደራጅተው በሚከፈላቸው መጠን ለልዩ የፖለቲካ ፍጆታ እርምጃ የሚወስዱ ናቸው።

እነዚህ ሃይሎች ትጥቅ፣ ገንዘብና ሌሎች አስፈላጊ ቁሶች የሚያቀርቡላቸውና አብረዋቸው የሚሰሩ የሌላ ብሄር አባላት አሉበት። በቅርቡ መከላከያ ድፍን ምስራቅ ወለጋን ሲያጸዳ በርካቶችን ይዟል። ደምስሷል። መሳሪያቸውን ከደበቁበት በጥቆማ አግኝቷል። ይህ መቼ ለህዝብ ይፋ እንደሚቀርብ ባይታወቅም፣ መከላከያ አገር ጉቲን ሲገባ ተኩስ ከተከፈተበት በሁዋላ ሃይል አስገብቶ በወሰደው እርምጃ ብዙ ጉድ መገኘቱን ስለ ጉዳይ የሚያውቁ አስታውቀዋል። የተያዙና እነ አቶ ክርስቲያን ታደለ ” የተከበሩ” እንዲፈቱ ሌት ከቀን የሚወተውቱላቸው ወገኖችም ምን ያህል ከዚህ የጸዱ እንደሆነ አፉን ሞልቶ የሚናገር ገለልተኛ ወገን አልተገኘም።

በዚህና በበርካታ መነሻዎች ገለልተኛ ወገኖች የሸኔን ማንነት በትክክል ለመረዳት ይቸገራሉ። ለዚህም ይመስላል አንዳንዴ ” መንግስት ያደራጀው” ሲሉት ይሰማል። የኦነግ ነጻ አውጪ መሪ እንደሆነ የሚነገርለት መሮ እንደሚለው ሸኔ ላይ ሲገኝ እርምጃ ይወሰድበታል። ታዲያ ከላይ በተገለጸው መሰረትና በዚህ ደረጃ የአፈጣጠሩና ማንነቱ ጉዳይ፣ ከዚያም በላይ ዓላማው አነጋግሪ የሆነው ሸኔ መሪው ማን ነው? መንግስት ” መሪውና ዓላማው የማይታወቅ” ሲል በተደጋጋሚ የሚገልጸው ሸኔ፣ በማንና እንዴት ለድርድር ይጋበዛል? ማንስ ለዚህ ሁሉ ነብስ ሃላፊነት ወስዶ በሸኔ ስም ለድርድር ይመጣል? የቁማሩ ውስብስብነት!!

በቅርቡ እጃችን የገባ አንድ መረጃ እንደሚያሳየው መሮ የሚመራው ክፍል እርዳታ ጠይቆ ደረሰኝ እየቆረጠ ገንዘብ ይሰበስባል። ደረሰኙ ላይ ስልክ ቁጥር አለው። ስልክ ቁጥሩ የኢትዮጵያ ህጋዊ ቁጥር ነው። ሸኔ ሰዎችን አፍኖ ገንዘብ ሲጠይቅ በዛ አድራሻ ይደወላል። እናም እነ መሮ ሃይል ለከው የሸኔን ታጣቂዎች አድፍጠው በመያዝ እርምጃ ይወስዱባቸዋል። አምቦ ዙሪያም አምስት የሸኔን ታጣቂዎች ህዝብ ፊት አቅርበው እርምጃ እንደወሰዱ ያዛቢ መሆናቸውን የተናገሩ ገልጸውልናል። እዚህ ላይ አንዱን ኮንኖ ሌላውን ለማጽዳት ሳይሆን የነሮችን መመሳቀል ለማሳየት ነው።

በርካታ ኦሮሞዎች ለዜና ፍጆታ በሚገባው መጠን ባይበቁም በዚህ ቡድንም ሆነ አብሮት ተናቦ እንደሚሰራ በሚነገርለት የአንድ አካባቢ አጎራባች ሃይል አልቋል። ተዘርፏል። ንብረቱ ወድሟል።ይባስ ተብሎ በወረራ የታዙ አካባቢዎችን ” ልዩ ዞን እንሁን” የሚል ጥያቄ አቅርበውባቸዋል። አንዱ የሰሞኑ የኦሮሞና የተወሰኑ የአማራ ብልጽግና ውዝግብ መነሻው ይህ እንደሆነ የሚናገሩ አሉ። እነዚሁ ክፍሎች ከልዩ ዞንነትም በላይ ወረው የያዙትን ቦታ ” አማራ ክልል ስር እንተዳደር” የሚል ጥያቄ በተወሰኑ የአካባቢው ተወላጆች አማካይነት ከፍ አድርገው የክልሉ ጥያቄ አድርገው ማቅረባቸው ተሰምቷል። ሸኔ ይህን አሳብ አንዴም አልተቃወመም። ኦፌኮና ኦእነግ ግን ገና ከጅምሩ ድምጻቸውን አሰምተዋል። ይህንን የሚያውቁ ሸኔን የሚመድቡት ከላይ በተቀመጠው አግባባ በሶስተናው ረዳፍ ነው። እናም መንግስት ከሸኔ ጋር ምን ይነጋገራል? እንዴትስ ይነጋገራል? እንዲነጋገርስ ማን ይፈቅድለታል? ቢፈቀድለትስ ለጨፈጨፈው ነብስ ማን ይቆምለታል?

ግብግቡ

ሰሞኑን አሽሙር አይሉት ስድብ አማራና ኦሮሞ ብልጽግና በቃላት እየተነታረኩ ነው። አቶ ሽመልስ ለሸኔ ትጥቅና ስንቅ የሚያቀርቡ ሃይሎች “ኦሮሞን ለማሸማቀቅ ሸኔን ይፈለጉታል” ባሉ የቀናት ዕድሜ ” የሰላም ጥሪ ማሰማታቸው ይታወሳል። የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳደር አቶ ሽመልስ አብዲሳ የክልሉ መንግሥትን የስድስት ወራት የሥራ አፈጻጸምን በተመለከተ ለምክር ቤቱ አርብ የካቲት 10/2015 ዓ.ም. ሪፖርት ባቀረቡት ወቅት ነው “ታጥቀው የሚንቀሳቀሱ እንደ ሸኔ ያሉ ኃይሎችን በንግግር ወደ እርቅ ኑ” ነው ያሉት።

ይህን ተከትሎ ” ሸኔ ነን” ያሉ ሳይሆኑ የኦሮሞ ነጻአውጪ ሰራዊት ኧራር የሆኑ ምላሽ ሰጥተዋል። ይህ በተሰማ ቀናት ውስጥ አማራ ብልጽግና ስም ሳይጠራ ኦሮሞ ብልጽግናን በከባድ ቃላቶች ” ቆሞ ቀርና ጎታች” ሲል አውግዞታል። በኦርቶዶክስ ዕምነት ቀኖና ተጣሰ በሚል የተነሳውን ውዝግብ ተከትሎ ድጋፉን ያሳየው አማራ ብልጽግና መዛም መግለጫው ላይ ” አካሄዱ ለሌሎች ትምህርት የሚሰጥ” ሲል ማድነቁና ከሚዲያ አጠቃቀም ጀመሮ የታዩት መዥጎርጎሮች ችግር እንዳለ የሚያሳዩ ቢሆኑም ፓርቲው በገሃድ ቅሬታውን ማሰማቱ ከኦነግ የእርቅ መቀበል ጋር የተገጣጠመ መሆኑ እያነጋገረ ነው።

ከትህነግ ጋር የፈጠረውን ህብረት በአደባባይ ያላነሳውና መንግስት ” አሸባሪ” ያለው ኦነግ የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት ፕሬዝዳንት ሽመልስ አብዲሳ የካቲት 10/2013 ለክልሉ ምክር ቤት ባደረጉት ንግግር፣ በኦሮሚያ ክልል ለሚንቀሳቀሰው ታጣቂ ቡድን የእርቅ ጥሪ ማቅረባቸውን አስታውሶ። ታጣቂ ቡድኑ “የኦሮሞ ነጻነት ግንባርና የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት” አቋም ብሎ ባወጣው መግለጫ፣ በኦሮሚያ ክልል የሚካሄደውን ጦርነት በድርድር ለመፍታት ዝግጁ መሆኑን ይፋ አድርጓል።

ጉዳዩን የሚከታተሉ እንደሚሉት የኦሮሚያ ባለስልጣናት ድርድር ከጀመሩ ሰነባብተዋል። አቶ ሽመል አሁን በድንገት ይናገሩት እንጂ ነገሩ እየበስለ ነው። አቶ ጃዋር መሃመድም ይህ ዕርቅ መላክም እንደሆነና ሊተገበር እንደሚገባው ገልጾ ድጋፍ እየሰጠ ነው። አቶ ታከለ ኡማም ከእነ አቶ ለማ ጋር በመገናኘት ይህንኑ የሰላም ሂደት ለማስፈጸም ከሚቀርቧቸው ጋር ሆነው ደፋ ቀና እያሉ እንደሆነ ኢትዮ12 ሰምታለች።

ከትህነግ ጋር የተደረገው የሰላም አማራጭ ስምምነት አራት ወራትን ካስቆተረ በሁዋላ እንዳላስደሰታቸው የገለጹት ፕሬዚዳንት ኢሳያስ ወደፊት ምን እንደሚሉ ባይታወቅም፣ በመቀለ በኩል ከገባው የኦነግ ሃይል በተጨማሪ በአውሮፕላን በዩጋንዳ በኩል እንዲገቡ ማድረጋቸው ከተሰማ በሁዋላ፣ ሰዎች የበዓሉ ግርማን ኦሮማይ ዳግም ማንበብ እንደሚገባቸው እየተመከሩ ነው።

የዕምነት ነጻነትን ፈጽሞ የማታከብረው ኤርትራ “ቀኖና ተጣሰ” በሚል ተነስቶ የነበረውን አለመግባባት ተንተርሶ ግብጽ ተገኝተው ከመከሩ አገራት መካከል መሆኗ፣ አቋም መግለጫ ማውጣቷና ረብሻው እንዲበርድ ከመደገፍ ይልቅ ” አይዙእችሁ” የሚል ይዘት ያለው አቋም መያዟ ” ኢሳኡን ምን ነካቸው” የሚል ጥያቄ አስነስቷል። ይህ ከመሆኑ በፊት ” ባህር በር ሳይኖራችሁ ጠንካራ ባህር ሃይል እንዴት ታቋቁማላችሁ የሚሉን ያልገባቸው ናቸው” ሲሉ የባህር ሃይል ዋና አዛዥ መናገራቸው በተመሳሳይ ቅሬታ አስነስቶ እነድነበርም አይዘነጋም።

ብዙም ድምጻቸው የማይሰማ፣ ነገር ግን ሁኔታውን የሚያጤኑ እንደሚሉት ከሆነ ኦሮሚያ ላይ ተኩስ ቆመ ማለት ድፍን ኢትዮጵያ ሰላም ሰፈነ ማለት ነው። አሁን ላይ መከላከያ በግዘትና በጥራት ዘምኖ መሰራቱ ስጋት የሚፈጥርባቸው ጎረቤት አገራትም ሆኑ ወዳጆች ብዙም ደስተኛ እንደማይሆኑ የሚገልጹት ክፍሎች ” የኢትዮጵያ ህዝብ የጸብ አጀንዳውን ሳይሆን፣ የጸቡን አጀንዳ ተካዮችን ዓላማቸውን ሊያጤን ይገባል” ባይ ናቸው።

በየተኛውም ዘመን የአማራና የኦሮሞ ህዝብ፣ በህዝብ ፍላጎት ወደ ግጭት እንደማይገቡ በመረዳት ፖለቲከኖች ችግራቸውን በራቸውን ዘግተው ከመነጋገር በዘለለ፣ የሌሎችን አጀንዳ በመሸከም ህዝብ ላይ ከመድፋት እንዲቆጠቡ የሚመክሩ፣ የክልል አመራሮችም ሆኑ የፓርቲ ቁልፍ ሰዎች በአክቲቪስት፣ በባለሃብትና በተቃዋሚ ድርጅት አንዳንድ አመራሮች ከተመሩ በሁሉም አቅጣጫ ችግር እንደሚፈጠር፣ የመስንጠቅ አደጋም ሊከሰት እንደሚችል፣ ይህ ልዩነትና መከፋፈል ለሌሎች ማገገም በር እንደሚከፍት፣ ሰላማዊውን ህዝብም ዳግም ለጉዳት እንደሚዳርግ ሂሳቡን ሊያሴሉ እንደሚገባ ይናገራሉ።

ኦነግ በመግለጫው “ትርጉም ያለው የሰላም ሂደት ለመፍጠር የቡድኑ አዛዦች እና ተደራዳሪዎች ከግጭት ቀጠናዎች መውጣት እና መግባት አለባቸውም ብሏል” ለዚህም አስፈላጊዎቹ የደህንነት ዋስትናዎች እና ሎጅስቲክስ ሊገኙ የሚችሉት በአለም ዓቀፍ ደረጃ ብቻ ነው ሲል ቡድኑ አስታውቋል። ይህ የሚያሳየው የሰላም ንግግሩ ከፍ ወዳለ ደረጃ መዳረሱን እንደሆነ በክልሉ የፖለቲካ ተሳትፎ ያላቸው ይገልጻሉ። አክለውም ይህን እርምጃ ሁሉም ዜጋ ሊደግፈው፣ ከዛም በሁዋላ በሂደት የፍትህ ጥያቄ ሊነሳ እንደሚችልም አክለዋል። ቢያንስ የወደፊቱን ዕልቂት ማስቆም አንድ ጥበብ እንደሆነም አመልክተዋል። ግድያ አስቁሞ፣ መገዳደልን አስቁሞ ስለጠፋው ህይወት ፍትህ ጉዳይ መነጋገርና የሚሆነውን ማድረግ ደግሞ ሌላው ትልቁ ጥበብ ስለሆነ እርቁን መደገፍ እንጂ ግብግብ ውስጥ መግባቱ እንደማይጠቅም በርካቶች ይናገራል። ያምናሉ።

Exit mobile version