Site icon ETHIO12.COM

“ሸገር ከተማ በመጪዎቹ 50 ዓመታት በአፍሪካ ከሚታወቁ ከተሞች አንዷ ትሆናለች”

የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ፕሬዝደንት አቶ ሽልስ አብዲሳ የሸገር ከተማ በይፋ ስራ መጀመሯን አብስረዋል፡፡ሸገር ከተማ በመጪዎቹ 50 ዓመታት ታሪካዊ እና በአፍሪካ ከሚታወቁ ከተሞች መካከል አንዷ ትሆናለች ነው ያሉት፡፡

አቶ ሽመልስ በዚህ ወቅት እንዳሉት ያለፉት ስርዓቶች የኦሮሞን ህዝብ ከፍተኛ መስዋትነት አስከፍሏል ፤ ህዝቡም ትዕግስት ፣ባህል እና እሴቶች ያሉት በመሆኑ ተስፋ ሳይቆርጥ በተለያዩ ትግል እዚህ ደርሷል፡፡

በተለይ የቱለማ ህዝብ ለየትኛውም ችግር ሳይነበረከክ ለዛሬው ድል በቅቷል ብለዋል፡፡

የሸገር ከተማ መመስረት በኦሮሞ ህዝብ ታሪክ ዘንድ ታሪካዊ ድል እና አዲስ ምዕራፍ ነው ያሉት አቶ ሽመልስ የቀድሞ ታጋዮች የኦሮሞ ህዝብ የራሱ ባንዲራ ፣ የራሱ መንግስት እንዲኖረው ላደረጋችሁት መራር ትግል በህዝቡ ዘንድ ከፍተኛ አክብሮች እና ፍቅር አላችሁ እንኳን ታገላችሁ እናንተ የጀመራችሁት ነው ዛሬ ፍሬ አፍርቶ ያየነውም ብለዋል፡፡

ዛሬ በይፋ ስራ ያስጀመርናት ሸገር ከተማ ወዳጆቻችንን ያስደሰተ እና የኦሮሞን ህዝብ የበታችነት የሚመኙትን ደግሞ አስደንግጧል ነው ያሉት አቶ ሽመልስ፡፡

የኦሮሞ ህዝብ ስኬት አይደናቀፍም ምክንያቱም ህዝቡ እውነት ያለው የሰው ፈላጊ ሳይሆን የራሱ በሆነው ነገር ላይ ባለቤትነቱን ለማረጋገጥ በስርዓት የታገለ እና የሚታገል በመሆኑ ነው ብለዋል ፡፡

ሸገር ከተማ በመጪዎቹ 50 ዓመታት ታሪካዊ እና በአፍሪካ ከሚታወቁ ከተሞች መካከል አንዷ ትሆናለች ነው ያሉት፡፡

ሸገር ከተማ ሁለት ትላልቅ ተልዕኮችን አንግቦ የተመሰረተ ከተማ ነው ያሉት ፕሬዝዳንቱ የመጀመሪያው ፊንፊኔን መጠበቅ ሌላው ደግሞ በማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ ዘርፎች ላይ ለኦሮሞ ህዝብ ምሰሶ ሆኖ ማገልገል ነው ብለዋል፡፡

ከተማዋ ተልዕኮዋን እንድትወጣ የክልሉ መንግስት በጀት በመመደብ በሁሉም አቅጣጫዎች ድጋፍ በማድረግ በትኩረት እንደሚሰራ ገልፀዋል፡፡

የከተማዋ አመራሮች በቅነት እንዲያገለግሉ ህዝቡም የሚጠበቅበትን እንዲያደርግ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡

ፀዳለ ፀጋዬ OBN

Exit mobile version