Site icon ETHIO12.COM

ትግራይ – ችግር ፈጣሪው ትህነግ መፍትሄ ሆነ፤ መንግስት “ራሳችሁ ጨርሱ” ብሏል

ትግራይ የጊዚያዊ አስተዳደር እንዲሰየምላት የማቋቋሚያ ሰነድ ተዘጋጅቶ ድልድል ቢደረግም የካቢኔ ወንበር ከተመደበላቸው ፓርቲዎች ሁለቱ ሥልጣኑን አንደማይቀበሉት ይፋ አድርገዋል። ትህነግ በትግራይ ህዝብ ላይ ለደረሰው መከራና ችግር ተጠያቂ ሆኖ ሳለ የመፍትሄ አካል ሊሆን እንደማይገባም ጠቅሰዋል። መንግስት ከትግራይ ስልጣን እንደማይፈልግና ራሳችሁ ጨርሱ ማለቱን የትህነግ ሰዎች ተናግረዋል።

ስልጣኑን አንደማይቀበሉ ያስታወቁት ሳልሳይ ወያነ ትግራይና ውድብ ናፅነት ትግራይ ናቸው። የሳልሳይ ወያኔ ትግራይ አመራር አቶ አሉላ ሃይሉ ለቪኦኤ ሲናገሩ በሌሉ ተቋማት ላይ ሃላፊ ሆነው እንዲሰሩ መደረጉን አውግዘዋል። የቱሪዝም፣ የቴክኖሎጂና የእንሳሳት ጥበቃ ቢሮን እንዲመሩ በስልጣን ክፍፍሉ መደረጉን ገልጸው ተቃውሞ ያሰሙት ” በሌሉ ቢሮዎች ለስድስት ወር መስራት የልጅ ጨዋታ ነው። አንቀበለውም” ነው ያሉት። ቢሮዎቹ ስራ ላይ ያሉ ባለመሆናቸው መቃወሚያ ቢያቀርቡም የተሰጣቸው ምላሽ ምን እንደሆነ በሪፖርቱ አልተካተተም።

ሁለቱም ፓርቲዎች “የተያዘው መንገድ የሕዝባችንን መከራ የሚያራዝም ነው” በማለት ተቃውሞ አሰምተዋል። የውድብ ናጽነት ትግራይ አመራር አቶ አለምሰገድ አረጋይ በበኩላቸው ትህነግ የችግሩ ሁሉ አካል መሆኑንን አመልክተው የመፍትሄው አካል መሆኑንን እንደማይቀበሉ ገልጸዋል።

ትህነግን መታገል የሕዝብ ጥያቄ እንደሆነ ያመለከቱት አቶ አለምሰገድ፣ ጥያቄው የወጣቱም እንደሆነ በማስታወቅ ስልጣን ወስደው ወደ ጓሮ እንደማይደበቁ ተናግረዋል። እሳቸው ይህን ቢሉም በክልሉ የሚመሰረተው ጊዜያዊ አስተዳደር የካቢኔ ክፍፍል ሰነድ ይፋ የተደረገው ለሁለት ቀናት በመቀሌ ከተማ የተካሄደው ኮንፍራንስ መጠናቀቁን ተከትሎ እንደሆነና አካሄዱ ዴሞክራሲያዊ መሆኑንን አዘጋጆቹ የትህነግ አመራሮች ገልጸዋል።

ጊዜያዊ አስተዳደሩን ለማቋቋም የተመሰረተው ኮሚቴ ሰብሳቢ ሌተና ጄነራል ታደሰ ወረደ “ወደፊት ጊዜያዊ አስተዳደሩን የሚመሩ ባለሥልጣናት ከሁሉም የፖለቲካ ድርጅቶች ተውጣጥተው የሥልጣን ክፍፍል ይደረጋል” ያሉ ሲሆን “የስልጣን ክፍፍሉ ሲጠናቀቅ ከፌዴራል መንግሥቱ ጋራ በጉዳዩ ላይ ድርድር ይካሄዳል” ማለታቸው ይታወሳል።

ጉባዔው “በአንድ ፓርቲ የበላይነት የሚካሄድ ነው” በሚል በትግራይ የሚንቀሳቀሱ ሦስት የፖለቲካ ፓርቲዎች ተሳትፎ እነደማይኖራቸው አስታውቀው ነበር። ሌተናል ጀነራል ጻድቃን በእንግሊዘኛ ባሰራጩት ጽሁፍ አካሄዱ መስመር የሳተ እንደሆነ ዝርዝር መረጃ በማቅረብ ቀደም ብለው ሞግተው እንደነበርም አይዘነጋም።

ሁሉም ሆኖ አሁን የተቋቋመው ጊዜያዊ አስተዳደር ከስድስት ወር እስከ አንድ ዓመት ስልጣን የሚኖረው ሲሆን ስራውን ሲጀምር ከፌደራል መንግስት ጋር ድርድር እንደሚያደርግ ታውቋል። ድርድሩ ምን እንደሆነ በዝርዝር ባይገለጽም የድንበርና የመልሶ ማቋቋም እንደሚሆን ተገምቷል።

ግፋ ቢል የአንድ ዓመት እድሜ ይኖረዋል የተባለው የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳድር 28 አባላት ያሉት ምክር ቤት ይኖረዋል። ሪፖርተር “ሚስጢር ሰማሁ” ብሎ እንደዘገበው ጊዜያዊ አስተዳደሩ አንድ ፕሬዚዳንት፣ ሁለት ምክትል ፕሬዚዳንቶችና በምክትል ፕሬዚዳንት ማዕረግ የሚሾሙ አራት የዘርፍ አመራሮች እንደሚኖረው ገልጸዋል። ከዚህ በተጨማሪም በጊዜያዊ አስተዳደሩ ሥር 17 የቢሮ ኃላፊዎች የሚኖሩት ሲሆን፣ ከላይ የተጠቀሱትን ጨምሮ 28 አባላትን የያዘ ካቢኔ እንዲደራጅ መወሰኑን ገልጸዋል። ከተገለጸው የካቢኔ አባላት ቁጥር ውስጥ 50 በመቶው ከሕወሓት የሚወከሉ ሲሆን፣ የጊዜያዊ አስተዳደሩ ፕሬዚዳንትና የካቢኔው ሰብሳቢ ከሕወሓት የሚወከሉ ይሆናል።

ጊዜያዊ አስተዳደሩ ሁለት ፕሬዚዳንቶች እንዲኖሩት፣ሁለቱ ፕሬዚዳንቶች ከትግራይ ሠራዊትና ከሲቪክ ተቋማት እንደሚወከሉ፣ ትህነግ በጊዜያዊ አስተዳደሩ ካቢኔ ውስጥ 50 በመቶ ድርሻ እንዲኖረው፣ የተቀረው 50 በመቶ ደግሞ ለትግራይ ሠራዊት፣ ለሌሎች የትግራይ ፖለቲካ ፓርቲዎችና ለትግራይ ሲቪክ ተቋማት መደልደሉን ነው ሪፖርተር የዘገበው።

በዚህም መሠረት ሌሎች የክልሉ ፖለቲካ ፓርቲዎች በድምሩ በ21 በመቶ ውክልና የካቢኔ አባል እንዲሆኑ፣ በተቀረው 29 በመቶ ካቢኔ ወንበር ላይ ደግሞ የትግራይ ሠራዊትና የሲቪክ ተቋማት በእኩል እንዲወከሉ መወሰኑን ገልጸዋል።

በዚህ ሕዝባዊ ኮንፍረንስ የተላለፉ ውሳኔዎች ወደ ትግበራ የሚገቡት በፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት መሠረት፣ የፌዴራል መንግሥትን ይሁንታ ሲሰጥ መሆኑን የጠቀሱት ምንጮቹ፣ ይህንን ይሁንታ ለማግኘትም የትግራይ ተደረዳሪ ቡድን በጥቂት ቀናት ውስጥ ከፌዴራል መንግሥት ጋር ተገናኝቶ እንደሚወያይ አስረድተዋል።

‹‹በሕዝባዊ ኮንፈረንሱ ውሳኔ ለሚቋቋመው የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር የኢፌዴሪ መንግሥት፣ መላው የኢትዮጵያ ሕዝቦችና የዓለም ማኅበረሰብ ሙሉ ድጋፍና እገዛ እንዲያደርጉ እንጠይቃለን፤›› ሲል የአቋም መግለጫው ጥሪ አቅርቧል።

ስለጊዜያዊ አስተዳደሩ አደረጃጀትና አጠቃላይ ሒደትን በተመለከተ ከሕወሓት ተጨማሪ መረጃ ለማግኘትና የፌዴራል መንግሥትን አስተያየት ለማከል ያደረግነው ሙከራ አልተሳካም።

መንግስት በትግራይ ክልል ምንም ዓይነት ስልጣን እንደማይፍለግና “ራሳችሁ ጨርሱ” ብሏል በሚል ቪኦኤ ከመዘገቡ ሌላ መንግስት ራሱ በገሃድ የተነፈሰው ነገር የለም። ይሁን እንጂ እውቅና እንደሚጠብቁ የትህነግ ሰዎች ተናግረዋል።

በትግራይ የሰላም አየር ሲወርድ “ለዚህ ነበር ያ ሁሉ ሰው ያለቀው” የሚል ጥያቄ ከዛም ከዚሁም እየተሰማ መቆየቱና አሁን ላይም ይህ ጉዳይ እየገነነ መሄዱን የሚጠቁሙ ወገኖች አሉ።

Exit mobile version