Site icon ETHIO12.COM

የሁለት ዓመት ልጅ ይዛ የተሰወረችው “ሞግዚት” ህጻኗ ይዛ ከመሸገችበት ገጠር ተያዘች

ከቀናት በፊት በሞግዚቷ ተሰርቃ የተወሰደችው የ2 ዓመቷ ህፃን ሶሊያና ዳንኤል ከብሄራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ጋር በመተባበር ባደረገው ጠንካራ ክትትል ሱሉልታ ከተማ ላይ መገኘቷን የአዲስ አበባ ፖሊስ አስታወቀ፡

የ2 ዓመት ዕድሜ ያላት ህፃን ሶሊያና ዳንኤል ሳሪስ አዲስ ሰፈር ተብሎ ከሚጠራው አካባቢ ሃሙስ መጋቢት 7 ቀን 2015 ዓ/ም ረፋድ ላይ ቤዛ በቀለ በተባለችው የቤት ሰራተኛቸው ተሰርቃ ስለመወሰዷ በተለያዩ ማህበራዊ ትስስር ገፆች መረጃው ሲሰራጭ መቆየቱ ይታወሳል፡፡

የአዲስ አበባ ፖሊስ በህፃኗ ወላጆች የቀረበለትን አቤቱታ ተቀብሎ ከብሄራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ጋር በመቀናጀትና ከአዲስ አበባ ውጪ ወደተለያዩ የሃገራችን ከተሞች እና አካባቢዎች በመሄድ ጭምር አስፈላጊ መረጃዎችን በፖሊሳዊ ጥበብ በማሰባሰብ ከፍተኛ ጥረትን የጠየቀ ክትትል ሲያደርግ ቆይቷል፡፡

የክትትል ስራው ቀንና ሌሊት ደጅ ውሎ ማደርን የግድ የሚል እጅግ አድካሚ እንደነበር ያስታወሰው የአዲስ አበባ ፖሊስ በስተመጨረሻም ቤዛ በቀለ ዛሬ መጋቢት 12 ቀን 2015 ዓ/ም ሱሉልታ ከተማ “ኖኖ መና አቢቹ” ተብሎ በሚጠራው ቀበሌ በአንድ መኖሪያ ቤት ውስጥ ህፃን ሶሊያና ዳንኤልን ሸሽጋ በተቀመጠችበት በቁጥጥር ስር መዋሏን አስታውቋል፡፡

ተጠርጣሪዋ በፖሊስ ቁጥጥር ስር ከዋለች በኋላ እንደተናገረቸው 40 ሺህ ብር ይከፈልሻል ብለው ሰዎች ስላግባቧት ህፃኗን ሰርቃ ልትሰወር ችላለች፡፡ በወንጀሉ ላይ ተሳትፎ አላቸው የተባሉ ሌሎች ተጠርጣሪዎችን በቁጥጥር ስር ለማዋል ምርመራው መቀጠሉን የአዲስ አበባ ፖሊስ ገልጿል፡፡
መረጃው የአዲስ አበባ ፖሊስ ነው

Exit mobile version