Site icon ETHIO12.COM

ኦሮሚያ በአራት ወር መቶ ሺህ ዘመናዊ የገጠር መኖሪያ ቤቶች ሊገነባ ነው

በቀጣዮቹ አራት ወራት በኦሮሚያ ክልል 100 ሺህ ዘመናዊ የገጠር መኖሪያ ቤቶች ግንባታ የሚከናወን መሆኑን የክልሉ ምክትል ፕሬዝዳንት አቶ አወሉ አብዲ ገለፁ። ዘመናዊ የገጠር ቤቶች ልማት የግንባታ ማስጀመሪያ የንቅናቄ መርሓ ግብር የተለያዩ አካላት በተገኙበት በአዳማ ከተማ ተካሄዷል።

የክልሉ ምክትል ፕሬዝዳንት አቶ አወሉ አብዲ በተለይ ለኢዜአ እንደገለጹት በክልሉ የአርሶ አደሩንና አርብቶ አደሩን የአኗኗር ዘይቤ ለመለወጥ እየተሰራ ነው።

ዘመናዊ የገጠር ቤቶች ልማት መርሓ ግብር አርሶ አደሩና አርብቶ አደሩ የተሻለ ህይወት እንዲኖር ለማስቻል ያለመ ነው ብለዋል።

በተጨማሪም መርሃ ግብሩ የአርሶ አደሩ የአኗኗር ዘይቤ ከመለወጥ ባለፈ ለሌሎች ሀብቶች ተጨማሪ ምንጭ እንዲሆን ለማድረግ እንደሆነ ገልጸዋል።

አርሶ አደሩ ቤቱን አስይዞ ከባንክ የብድር አገልግሎት የሚያገኝበትና ተጨማሪ ሀብት ማፍራት የሚችልበት ሂደትና አሰራር ጨምር ለመዘርጋት እንደሆነም አስረድተዋል።

መርሓ ግብሩ በሙከራ ደረጃ በኦሮሚያ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን ውጫሌ ወረዳ መጀመሩን የገለጹት ምክትል ፕሬዚዳንቱ በተለይ አርሶ አደሩ ዘመናዊ መኖሪያ ቤት ኖሮት ንፅህናውን በጠበቀ መልኩ የተሻለ ህይወት እንዲመራ ነው ብለዋል።

”መርሓ ግብሩን ውጤታማ ለማድረግ ብሎኬት ማምረቻ ማሽነሪዎችንና ሌሎች የግንባታ ግብዓት ተሟልተዋል” ያሉት አቶ አወሉ የግንባታ ሙያተኞች ስልጥነው መዘጋጀታቸውንም ተናግረዋል።

በመርሃ ግብሩ ከባለ አንድ መኝታ ጀምሮ እስከ ሶስት መኝታ ያሉት 100 ሺህ የሞዴል አርሶ አደሮችና አርብቶ አደሮች ቤቶች ይገነባሉ ብለዋል።

በዚህም 1ሺህ 500 ካሬ ሜትር ቦታ ላይ የይዞታ ማረጋገጫ ካርታና ፕላን ለአርሶ አደሮቹ እንደሚዘጋጅም ጨምረው ገልጸዋል።

በተያያዘም በመድረኩ ላይ የኦሮሞ ህዝብ የመረዳዳትና የመተጋገዝ ባህል የሆነው ቡሳ ጎኖፋና የበጎ ፈቃድ አገልግሎት አጠናክሮ ለማስቀጠል ያለመ ውይይት መደረጉንም ተናግረዋል።

በዚህም አሁን ከ9 ሚሊዮን በላይ የደረሰውን የቡሳ ጎኖፋ አባል በቀጣይ በእጥፍ ለማሳደግ መታቀዱን ጠቅሰው በዚህም የሀብት አሰባሰቡን 3 ቢሊዮን ለማድረስ ግብ ተቀምጧል ብለዋል።

እስከ አሁን ቡሳ ጎኖፋን ለማጠናከር በተሰሩ ስራዎች የኦሮሞ ህዝብ ወደ ነበረበት የመረዳዳት ባህል እንዲመለስና ባህሉ እንዲዳብር የሚያስችሉ ስራዎች መስራታቸውን ተናገረዋል።

በዚህም የቦረና ዞንን ጨምሮ በክልሉ በሚገኙ 10 ዞኖች ለድርቅ የተጋለጡና በተለያዩ ሰው ሰራሽ ችግሮች ለተፈናቀሉ ወገኖች የምግብ እህልና የቁሳቁስ ድጋፍ በዘላቂነት ማድረግ መቻሉን አስታውቀዋል።

በተመሳሳይ በመድረኩ የ2015/16 ዓ.ም የምርት ዘመን የመኸር አዝመራ ዝግጅት፣ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብርና የበጎ ፍቃድ አገልግሎት መቀጠል በሚቻልበት ሁኔታ ላይም ውይይት መደረጉን ጠቁመዋል። ኢዜአ

Exit mobile version