Site icon ETHIO12.COM

አማራ ” የሰውነት ውሃ ልክ” ሲመሳሰል ” ወርቅ ሕዝብ”

አባቶቻችን ችግር ቢኖርባቸውም በአሁኑ ደረጃ እንደሚታየው ሴረኞች አልነበሩም። ሞራላቸውን የላሸቀና ለብልጭልጩ ሁሉ የሚቃዡ የበዙባቸውም አልነበሩም። ጥቂት ባንዳዎች ቢኖሩም ለአገራቸውና ለወዳጆቻቸው ሁሉ ሟቾች ነበሩ። ከምንም በላይ እምነት ነበራቸው። ፈጣሪያቸውንም ይፈሩ ነበር። የዕምነት ደጅ ላይ ቸርቻሪዎችም አልነበሩም። አሁን ላይ እንደሚታየው የሃሰት ካባ፣ የነብይነት ማዕረግ ተሸክመው የሚወሰልቱ አልነበሩም። ዛሬ ድረስ የሚያወዛግበንን ጥፋት ያኖሩልን ጥቂት አጥፊዎች ቢኖሩም የሚልቁት የሚወደስ እንጂ የሚኮንን ስብዕና ባለቤት አልነበሩም።

አንድ ህዝብ፣ ወይም የህብረተሰብ ክፍል፣ ወይም ጎሳ፣ ወይም ዘር በጅምላ የተለይ ጥፋተኛ፣ የተለየ አልሚ፣ የተለየ ቀዳሽ፣ የተለየው ተወዳሽ ወይም ተወቃሽ ሊሆን እንደማይችል እየታወቀ፣ ዛሬ ላይ በጅምላ ህዝብን መዝለፍ፣ ማውገዝና መፈረጅ ተለምዷል። በተቃራኒው በተመሳሳይ በተዘረዘሩት የህብረተሰብ ዓይነቶች መርጦ “ወርቅ ህዝብ፣ የሰውነት ውሃ ልክ” በሚል ማወደስም የእለት ተእለት ስራ ሆኗል። በተለይ ኦሮሞን ” ተረኛ የጋላ መነግስት” በማለት ለማሸማቀቅ የሚምከረውን ያህል አማራውን ” የሰው ውሃ ልክ” በሚል እያሞካሹ ልዩ ተጨቋኝ፣ በኦሮሞ ወይም ” በጋላ መንግስት” በደል እየደረሰበት በመሆኑ ነጻ እንዲወጣ በተደጋጋሚ እየተወተወተ ነው። ከሆነ ያሳፍራል። የመታገያ መንገዱ ደግሞ ይበልጥ ያሳፍራል። ሁለቱም ወገኖች ግን ምስኪኑንን ህዝብ ይነግዱበት ካልሆነ በቀር አይጠቅሙትም።

የትግራይን ሕዝብ ነጻ እንደሚያውጣ አስቦ ትግል የገባው “ነጻ አውጪ” የትግራይን ህዝብ ” ወርቅ ሕዝብ” እያለ ልክ እንደ ጎማ ሲነፋው ኖረ። ጦርነትን ሰሪ እንደሆነና ጦርነት የባህል ጨዋታው እንደሆነ ሲነገረው ኖረ። ተራራ የሚያንቀጠቅጥ ትውልድ እንደሆነ በቃላት ብቻ ሳይሆን በፊልምና በተውኔት ደጋግሞ ጋተ። በመጨረሻም ጥይት የሚመታቸው የማይመስላቸው፣ ድሮን ጢንዚዛ የምትመስላቸውና ከፈለጉ ሩቅ ምስራቅን ዘልቀው አገር መያዝ የሚችሉ የሚመስላቸው ዜጎችን አምርቶ የሳት እራት አደረጋቸው።

በተመሳሳይ “አማራ የሰውነት ውሃ ልክ” የሚል አስተምህሮ በመያዝ ምስኪኑን፣ ሰራተኛውን፣ ሰው አፍቃሪውን፣ በሄደበት ሁሉ ጥሮ ግሮ ሃብት የሰብሰበውን ህዝብ የማይጠቅመው፣ ይልቁኑም የሚለየው ፖለቲካ መስማት ተለምዷል። ችግርን፣ ወይም የፍትህ ጉድለትን ሌሎችን በማያስቀይም መልኩ ማቅረብና መታገል እየተቻለ፣ የተመረጠው ሌሎችን የማቃለለ አካሄድ በምን ሂሳብ ልክ እንደሚሆን ለብዙዎቹ ታዛቢዎች ግልጽ አይደለም። ለእኛም!!

ዛሬ በአማራ ክልል ውስጥ የሚካሄደው እንቅስቃሴ መሪውና ዋንኛ ፍላጎቱ ለሌሎች ግራ እንደሆነ ነው የሚሰማው። “አማራ ነጻ ይውጣ” የሚል መፍክርም ይደጋገማል። ይህ መፍክር ግን ግልጽ አይደለም። አማራ ከማን ነው ነጻ የሚወጣው? እንዴት ነው ነጻ እንዲሆን የሚፈለገው? ነጻ ከሆነ በሁዋላ ምን ይሻል? ከሁሉም በላይ አማራ የተጨቆነውና ነጻ ለመውጣት መታገል ያስፈለገው ከምን ዓይነት ጉዳዮች ታግዶ ወይም ባይተዋር ተደርጎ ነው? የሚለው ግልጽ ሊሆን ይገባል።

በግልጽ በሚታይ የስልጣን እርከን አማራ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር፣ ውጭ ጉዳይ፣ ደህንነት፣ ጉምሩክ፣ በሄራዊ ባንክና ልማት ባንክን፣ ኢንዱስትሪ ሚኒስትርን ወዘተ ይዟል። በአገሪቱ የጸጥታ ምክር ቤት ውስጥ አብላጫ ድምጽ አለው። የመከላከያ ምክትል ኤታማዦር ሹምም አማራ ናቸው። ወደ ዝርዝር መግባት ሳያስፈልግ ጥያቄው በፌደራል መንግስት ውስጥ በሚገባው መጠን አልተወከለም የሚል ነው? ወይስ ሌላ? ይህ ሊመለስ ይገባል።

ችግሩ ያለው በፌደራል መንግስት ውስጥ ካልሆነ ምንድን ነው ከሌሎች ክልሎች ጋር ንትርክ ውስጥ የሚከታቸው? ችግሩ ከፌደራል ሳይሆን ከክልል ከሆነ የክልሉን መንግስት ቢሆን በውይይት፣ ካልሆነም በህዝብ ጫና ወይም በመረጡት ሰላማዊ መንገድ መታገልና ማሸነፍ ቀዳሚ ተግባር ሆኖ ሳለ በሌሎች ጉዳይ ውስጥ ቀድሞ ለመግባት መሞከሩ አግባብነቱም ሆነ ጠቀሜታው ሊገባቸው ያልቻሉ ዜጎች “ምን እየሆነ ነው?” እያሉ ነው። እርግጥ በሴራ የአማራን ህዝብ ፈርጆ ጠላት በማድረግ ትህነግ የፈጸመው ወንጀልና ያንኑ ሴራውና አሁን ላይ ለሰሚ ግራ በሚገባ መልኩ በሰላም ከሚኖሩበት የተገደሏን የተፈናቀሉ አማራዎች ጉዳይ ፍትህ የሚሻ እንደሆነ መካድ አይቻልም። ፍትህ እንዲበየን የተመረጠው አግባብና አድሮ የሚጠራው የሸኔና የሸኔ ስፖንሰሮች ጉዳይ እንዳለ ሆኖ የሚያስማማ አይመስልም። ብዙዎችን ቀና ሰዎችም አሳዝኗል። “ጋላ” ብሎ መሳደብ ፍትህን ሳይሆን ሌላ ደም የሚያቃባ እንዳይሆን ስጋት አለን።

መሪዎች በሁሉም ህዝብ ሊወደዱ አይጠበቅም። ሊጠሉም አይጠበቅም። የመጥላት መብት የተጠበቀ እንዲሆን የሚፈለገውን ያህል የመውደድም መብት እንደሚከበር ማወቅ አግባብ ይመስለናል። ይህ ካልሆነና የራስን ስሜት አክብሮ ሌሎች ስሜት አልባ እንደሆኑ አድርጎ ማሰብ ስህተት ይሆናል። ስለሆነም በአብዛኞች ውሳኔና ፍላጎት መመራት ግድ ወይም ተፈጥሯዊ መሆኑን ማመን፣ አምኖም በዛ ቅኝት መጓዙ ለሁሉም ጠቃሚ ነው።

በተደጋጋሚ የገባቸው እንደሚሉት ኢትዮጵያ የተሰራችበት ጡብ የትኛውም አካል ተነስቶ ለውጥ እንዲመኝ አይፈቅድም። በተለይ ኦሮሞና አማራ ስምምነት ከሌላቸው መንግስትን በሃይል የመናድ ጉዳይ ሌላ ጣጣ ካላስከተለ በቀር በስኬት የሚጠናቀቅ አይሆንም። አሁንም የገባቸው እንደሚሉት ይህን እውነት ይዞ አማራጭን በቅጡ በማሰብ ማስኬድ አግባብ ይሆናል።

ብልጽግና የሚመራት ኢትዮጵያ ገና ከጅምሩ አንስቶ አሁንድረስ አልረጋችም። ዘግናኝና ለሰሚው ግራ የሚያጋባ የዕልቂት መርዝ ከሩቅና ከቅርብ እየተረጨባት ነው። አንዳንዴ የሚረጨው መርዝ ዜጎች ሌላ ተጠባባቂ ወንበር ላይ የተቀመጠች አገር የተዘጋጀላቸው ይመስላል። እናስብ በኢቶጵያ አብሮ የኖረ ህዝብ እንዲባላ ምን ያልተባለ ነገር አለ? ምን ያተቆፈረና ያልተናደ የክፋት ኩያሳ አለ? ሴራ የወለደው ምን ያልተሰራ የግፍና የዕልቂት አይነት አለ? ምንስ ያልደረሰብን በደል አለና ነው ዳግም ለመጫረስ ያዙኝ ልቀቁኝ የምንለው? ምንስ በፈርደበት ነው ምስኪኑ ህዝብ ስልጣን ላናወዛቸው እርጉሞች የመስዋዕትነት በግ የሚሆነው? ለምንድን ነው ደሃው እንዲያልቅና እንዲጫረስ ከሃይማኖቱ ጀምሮ ሴራ የሚደገስለት? ለየትኛው ጻድቅና መክልካም አባት ሲባል ነው ጥቁር ተለብሶ ህዝብ እንዲማገድ ሃያ አራት ሰዓት የሞት ነጋሪት ሲታወጅ የከረመው? ብዙ ማንሳት ይቻላል። ቢሰፍሩት የማይልቅ የእልቂት ድግስ በምስኪን እናቶች የየዋህነት ጸሎት ከሸፈ እንጂ ይህኔ አገር አልባ በሆን ነበር። ማንስ ነው እንደዚህ በትርምስ የሚነዳን? ለምን “ባለቤቱ እኔ ነኝ” ብሎ በአሽምርና በተዘዋዋሪ ሳይሆን በገሃድ አይመጣም? እኛስ “ማን ነህ አንተ” ለምን አንልም? ምንድን ነው እንዲህ ያዞረብን? እስለመቼስ ነው እንዲሁ እያሰከርን የምንዘልቀው? ምንድን ነው ያስመኘን?

የብልጽግናን መንግስት አልሞና ፕሮግራም ነድፎ መታገል፣ ማረቅ፣ ማጋለጥ አግባብ ነው። ተደጋግፎ በሰላማዊ ስልት ከስልጣን ማስወገድም ዴሞክራሲያዊ አካሄድ ነው። ከዚህ በዘለለ ግን የብልጽግና መሪ የወጣበትን ሕዝብ በጅምላ መሳደብ ተቀባይነት የሚኖረው አይመስለንም። ሊኖረውም አይችልም። ይልቁኑም መሪውን ይጠቅመው ካልሆነ በቀር ለተቃዋሚው አካል ኪሳራ ነው።

ትህነግ በሴራ ተጸንሶ፣ በሴራ ጎልብቶ፣ ከነሴራው ተወልዶ፣ ሴራ ጠንቶበት፣ በሴራው ጣጣ ህዝብ አንድ ሆኖ ያነተበው ድርጅት ነው። የትግራይ ህዝብ ግን ወገን ህዝብ ነው። ኢትዮጵያ ካልን የትግራይንም ህዝብ አቅፈን ነው። እርቅ ዋጋ ስለሚያስከፍል በጥንቃቄ ለሰላም ዋጋ መክፈል ግድ ይሆናል። ሁሉንም በወጉና “ነግ በኔ” በሚል የጨዋ ብሂላችን ማስኬድ ሲገባ “ኢትዮጵያ አንድ ናት” እያልን አንድ የማይደርግ ማጥ ውስጥ ከዳከርን የምናታልለው ራሳችንን ይሆናል። ድምሩም የዜሮ ጨዋታ ከሚያደርገን ውጭ ሌላ ውጤት አያመጣም። እንጠንቀቅ። ለመጠፋፋት እየጋለብን ነውና!!

መንግስት “ጥሪ አልቀበልም” የሚለውን የደነዘዘ አቋም ወደ ጎን በማለት በጎደለና ዜጎች በሚያሰሙት ድምጽ ውስጥ ራስህን ከተት። ሆድህን አስፍተህ ሁሉንም እኩል ዕቀፍ። ባንተ አልጠግብ ባይ ካድሬዎች ሳቢያ ህዝብ ጥርስ እንዲነከስበት አታድር። በአጉል እብሪትና ተራ የተረኝነት ስሜት የሚወቀሱትን አርቅ። ምከር። ውጣ!!

በጥላቻ ጥግ ልክ ትህነግ እንዳደረገው ህዝብን ምሬትና ቁጣ ውስጥ በመክተት ስልት የዕልቂት አቡሸማኔ ላይ የተሳፈራችሁ አካላትም እባካችሁን ከግልቢያው ላይ ውረዱ። ኢትዮጵያ የተሰራችበትን ጡብ በመረዳት ለህዝብ ቂምና ስቃይ የማያተርፍ የትግል ዘዴና የተመረጠ ቅስቀሳ ተጠቀሙ። በተራ ስድብና አዋጅ በኪሳራ መንገድ አትንጎዱ። በኢትዮጵያ የሰው ልክም፣ የሰውነት ልክም የጎደለበት ህዝብ የለምና። መንግስት መሆን የሚቻለውም በአብላጮች ፈቃድ የሚሆንበትን አግባብ ዛሬ በመስራት አገራችን በምርጫ ብቻ መንግስት የምትቀይር አገር እንድትሆን እንስራ። አጉል ቀረርቶ ለትህነግ እንዳልጠቀም ሁሉ ለአማራም ሆነ ለኦሮሞ ወይም ሊሎች ጽንፈኞች አይሰራላቸውም። ኢትዮጵያ ትቅደም። ምክንያታዊነት ይለምልም። ሁሉም እኩል የሆኑባት ኢትዮጵያ!! የአባቶቻችንን ጨዋነትና አብሮ መኖር ጌጥ እናድርግ። በህዝብ ስቃይና ዕልቂት ወደ ስልጣን ለመንደርደር የሚደረገው ሩጫ ይብቃ። አልመንና አስበን ጨዋ የፖለቲካ ጨዋታ እንጀምር። ሶስት ዓመት ነገ ነው። ጊዜ እንደሆነ ይነጉዳል። በስድብም፣ በጥላቻ ዘመቻም ሆነ በሰከነ መንገድ ለሚጠቀሙበት ጊዜ እኩል ይከንፋልና ምርጫ ሲመጣ ቋት ባዶ እንዳይሆን አደራ!!

Exit mobile version