Site icon ETHIO12.COM

መከላከያ የሃሰት መረጃ ለሚያሰራጩና የአመራሮችን ስም ለሚያጠለሹ ማሳሰቢያ ሰጠ

የሰራዊቱን የዕዝ ሰንሰለት የሚያናጉ እኩይ ዓላማ አንግበው በሚንቀሳቀሱ እና ሰራዊቱ ትናንት የፈፀማቸውን ተግባራት በሚያጥላሉ ጉዳዬች በተሰማሩ አካላት ላይ በህግ አግባብ አስፈላጊው እርምጃ ይወሰዳል።

ሀሰተኛ መረጃ በማሰራጨት የመከላከያ ሠራዊቱንና የሠራዊቱን አመራሮች ስም የሚያጎድፉ አካላት ከድርጊታቸው እንዲታቀቡ የኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት አሳሰበ፡፡

የመከላከያ ሠራዊት የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር ኮሎኔል ጌትነት አዳነ÷ የክልል ልዩ ኃይሎችን መልሶ ለማደራጀት እንቅስቃሴ መጀመሩን ተከትሎ አንዳንድ አካላት ሆን ብለውና በተቀናጀ አግባብ በሀሰተኛ መረጃ የመከላከያ ሰራዊትን እና የአመራሮቹን ስም እያጎደፉ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የእነዚህ ቡድኖች ዓላማ የሠራዊቱን ስም በማጥፋትና በሀሰት በመፈረጅ እርስ በርሱ እንዳይተማመን ማድረግ መሆኑን ጠቅሰው፣ይህም ፈጽሞ ሊሳካ የማይችል እኩይ ተግባር መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በተለይም በሠራዊቱ እና መሪዎቹ መካከል ያለውን ጠንካራ የዕዝ ሰንሰለት ለማላላት የጥፋት አጀንዳ እንደሚፈጥሩ የተናገሩት ኮሎኔል ጌትነት÷የዚህ ተልዕኮ ዋነኛ ዓላማም ሀገር ማፍረስ መሆኑን አብራርተዋል፡፡ ከዚህ በኋላ በአንድ እጅ ትጥቅ በሌላ እጅ ደግሞ ፖለቲካ ይዞ መንቀሳቀስ አይቻልም ነው ያሉት ኮሎኔል ጌትነት።

ህብረተሰቡ የኢትዮጵያ የመጨረሻ ምሽግ የሆነውን የመከላከያ ሰራዊትን ለመከፋፈል የሚጥሩ አካላት መኖራቸውን ተገንዝቦ÷ ከድርጊታቸው እንዲታቀቡ የበኩሉን ድርሻ ሊወጣ ይገባል ሲሉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

የሀገር መከላከያ ሠራዊት ማንኛውንም ዋጋ ከፍሎ የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት እና የግዛት አንድነት ለማስከበር ዝግጁ መሆኑን መግጻቸውንም ኢዜአ ዘግቧል፡፡

የኢፌዴሪ መከላከያ ሚያዚያ 07 ቀን 2015 ዓ.ም

”የክልል ልዩ ሀይሎችን መልሶ ማደራጀቱ ህብረ-ብሄራዊ ሰራዊት ለመገንባት ሚናው የጎላ ነው።”
ኮሎኔል ጌትነት አዳነ
የመከላከያ የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር

ወቅታዊ ሁኔታዎችን መነሻ አድርገው ኮሎኔል ጌትነት አዳነ በሚከተሉት ዋና ዋና ነጥቦች ላይ መግለጫ ሰጥተዋል።

~ በአሁኑ ጊዜ እየተተገበረ ያለው የየክልሎችን ልዩ ሀይሎች መልሶ የማደራጀት ተግባር በኢፌዴሪ ህገመንግስት በተቀመጠው አንቀፅ-87 መሰረት ሚዛናዊ ተዋፅኦን ያካተተ ህብረ-ብሄራዊ ሰራዊት ለመገንባት የሚያግዝ ሂደት ነው።

~ በሁሉም ክልሎች እየተከናወነ ባለው መሰረት የየክልሉ ልዩ ሀይሎች ወደመረጡት እንዲገቡ ከተደረገ በኋላ አስፈላጊውን የማዋሃድ ስልጠና ተሰጥቷቸው እንደየ አደረጃጀቱ በሚሰጣቸው መሰረት የሚሰማሩ ይሆናል።

~ የክልል ልዩ ኃይሎችን መልሶ ለማደራጀት እንቅስቃሴ መጀመሩን ተከትሎ አንዳንድ አካላት በተቀናጀ መልኩ የህዝባችንን አንድነት የሚሸረሽሩና የፀጥታ ሀይሎችን የተልዕኮ አፈፃፀም የሚያናጉ ሀሰተኛ መረጃዎች በማሰራጨት ላይ ናቸው፡፡

~ ከክቡር ፊልድ ማርሻል ብርሀኑ ጁላ እና ከክቡር ጄኔራል አበባው ታደሰ ጀምሮ የመከላከያ ከፍተኛ ወታደራዊ አመራሮችን የትውልድ አካባቢ እና የወጡበትን ህዝብ በማንሳት በመለየት የማጥላላትና አላስፈላጊ ተቀፅላ በመስጠት ላይ የተሰማሩ አፍራሽ አካላት በተቋሙ መሪዎች ላይ የሚሰነዝሩት ማንኛውም የስም ማጥፋት ዘመቻ አገር እንደማፍረስ ይቆጠራል።

~ የሁሉም ክልሎች የሚመለከታቸው አካላት የእስካሁኑን ሂደት ገምግመው በደረሱበት ውሳኔ መሰረት ከዛሬ ጀምሮ የየትኛውንም ክልል ልዩ ሀይሎች ወታደራዊ አልባሳት ፣ ስምና መለዬ የሚሰጥና የሚፈፀም ግዳጅ አይኖርም።

~ የመከላከያ ሰራዊቱ ከቦታ ቦታ ተንቀሳቅሶ ግዳጁን እንዳይፈፅም የሚያደርጉ ተግባራት በመፈፀም ላይ ሲሆኑ ሰራዊቱ ከዚህ በፊት በፈፀማቸው አገር የማዳን ተልዕኮዎች ሁሉ ሲደግፈው የነበረው ህዝብ በሰራዊቱ ላይ መጠራጠር እንዲያድርበት የሚያደርጉ ነጣጣይ ዝንባሌዎች ላይ የተሰማሩ አካላት ከድርጊታቸው ሊቆጠቡ ይገባል።

~ በአንዳንድ ሀላፊነት በጎደላቸው የማህበረሰብ አንቂ ነን ባዬች በሚዘወሩ የማህበራዊ ትስስር ገፆች አማካኝነት እየተሰነዘሩ ያሉ አፍራሽ ትችት ፣ ወቀሳና አላስፈላጊ የሆኑ ስም መስጠቶች ተቀባይነት የላቸውም።

~ ከዚህ በኋላ ማንኛውም የማይመለከተው አካል በየትኛውም አካባቢ የመከላከያ ሰራዊቱን የደምብ አልባሳት ይዞ ወይም ለብሶ መገኘት የሰራዊቱን ተልዕኮ እንደመቃረን ይቆጠራል።

~ የሰራዊቱን የዕዝ ሰንሰለት የሚያናጉ እኩይ ዓላማ አንግበው በሚንቀሳቀሱ እና ሰራዊቱ ትናንት የፈፀማቸውን ተግባራት በሚያጥላሉ ጉዳዬች በተሰማሩ አካላት ላይ በህግ አግባብ አስፈላጊው እርምጃ ይወሰዳል።

በመጨረሻም:-
~ የኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት ልክ እንደወትሮው ሁሉ አሁንም ወደፊትም ማንኛውንም የመስዋዕትነት ዋጋ ከፍሎ የአገራችንን ሉዓላዊነት ለማስከበር እና የህዝባችንን ዙሪያ መለስ ክብርና ጥቅም ለማስጠበቅ የተሟላ ብቃት ላይ እንደሚገኝ አረጋግጠዋል።

መላክ በቃሉ የኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት

Exit mobile version