ETHIO12.COM

በ “ጦርነት ይብቃ ሰላማችን እናጽና” ስነ ስርዓት ላይ ምን ተባለ? “ኢትዮጵያዊያን ፈጣሪን አመስግኑ”

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አሕመድ እጅግ አብዝተው ጦርነትንና አለመግባባትን በስለጠነ መንገድ የመፍታት ባህል እንዲዳብር ደጋግመው በተማጸኑበት ንግግራቸው ” ኢትዮጵያዊያን ፈጣሪያችሁን አመስግኑ” ሲሉ በይፋ ጥሪ አስተላልፈዋል። አቶ ጌታቸው ረዳን ባህር ዳር በመሄድ ጀግንነት እንዲፈጽሙ፣ ዶክተር ይልቃልም ይህንኑ ተግባር መቅለ በመሄድ እንዲደግሙት ያሳሰቡት አብይ አህመድ የክልል መሪዎች በሙሉ ወደ መቀለ እንደሚሄዱና ለትግራይ ህዝብ ያላቸውን ፍቅር እንደሚገልጹ አስታወቀዋል።

እንደ ፖለቲከኛ ሳይሆን እንደሰው የተናገሩት አብይ አህመድ ጦርነት አድቃቂ፣ አውዳሚ፣ ገዳይ ሲሉ የክፋቱን መጠን ዘርዝረው “አ፤ጠቀመንምና ዲሞትፎሩን አገራቸውን ለሚወዱ አስተማማኝ የመከላከያ ሰራዊት በመተው ሞፈር እናንሳ” ሲሉ አጽንዖት ሰጥተው ተናግረዋል። አቶ ጌታቸውም “መርዝ የሚተፉ አንድበቶች” ሲሉ የግጭት ወቅቱን ፕሮፓጋንዳ አስታውሰው “መልካም ነገርን ከአፋችን እናውጣ” ብለዋል።

በሚሊዮን ህይወት የተገበረበት፣ ከ27 ቢሊዮን ዶላር በላይ ኪሳራ ያከናነበውና በርካቶችን ቤትና ንብረት አልባ ያደረገው የዕብሪት ጦርነት ከቆመ በሁዋላ ” ጦርነት ያብቃ፣ ሰላማችንን እናጽና በሚል በተዘጋጀው የዕውቅና መርሃ ግብር ላይ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ድመቀ መኮንንም በተመሳሳይ ሰላም እንዲጸና መስራት የሁሉም ግዴታ መሆኑንን በአደራ አመልክተዋል። ከታች ያለው ከኢዜአ እና ፋና የተወሰደ ነው።

የኢትዮጵያ የጦርነትና የመከራ ጊዜ አብቅቶ፤ ትናንትን ተሻግረን ለነገ የተሻለ ለመስራት መዘጋጀት አለብን ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ ተናገሩ። የፕሪቶሪያውን የሰላም ስምምነት ተከትሎ በሂደቱ አስተዋጽኦ ላደረጉ ሁሉ የእውቅና እና ምስጋና መርሃ ግብር በአዲስ አበባ ተከናውኗል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ፤ በሰላም ሂደቱ ተሳትፎ ለነበራቸው አካላት ሁሉ እውቅና በመስጠት ምስጋናቸውንም አቅርበዋል። በመድረኩ ላይ ባስተላለፉት መልእክትም ከጦርነት ወጥተን በሰላምና መልሶ ግንባታ ላይ እየተነጋገርን በመሆኑ የዛሬው እለት ለኢትዮጵያ ልዩ ቀን ነው ብለዋል።

ሰላም የተለየ ጊዜ አይፈልግም፣ የሰላም መቋጫ የምስጋናና የአዲስ ቀን ማብሰሪያ ናት በማለት እለቱ የመላ ኢትዮጵያውያን የደስታ ቀን መሆኑን ገልጸዋል። ሰላም ጥላቻን ያፈርሳል፣ ጦርነት ደግሞ ጨለማ ነው፣ ያወድማል ይገድላል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ኢትዮጵያ ከነበረችበት ጨለማ ወጥታ ወደ ሰላም ሂደቱ ፈቅዳ የጀመረችው ጥረት ፍሬ ማፍራቱን ጠቅሰዋል፡፡

“ከምክር ይልቅ መከራ የሚያስተምርን መሆን ስለሌለበት የጦርነትና የመከራ ጊዜ አብቅቶ፤ትናንትን ተሻግረን ለነገ የተሻለ ለመስራት መዘጋጀት አለብን” ብለዋል። ከጦርነት ወጥተን በሰላምና መልሶ ግንባታ ላይ እየተነጋገርን በመሆኑ እለቱ የተለየ ቀን መሆኑን ጠቅሰው በቀጣይ በብልፅግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዝዳንት መሪነት የሁሉም ክልል ርዕሳነ መስተዳድሮች ወደ መቀሌ ይጓዛሉ ሲሉም ተናግረዋል። ሰላማችንን በማቅናት በትብብርና አብሮነት ኢትዮጵያን በፅኑ መሰረት ላይ አኑረን ማስቀጠል አለብን ብለዋል።

ከትግራይ ሕዝብ የሰላም እና የፍቅር መልዕክት ይዤ መጥቻለሁ – አቶ ጌታቸው ረዳ

ከትግራይ ሕዝብ የሰላም እና የፍቅር መልዕክት ይዤ መጥቻለሁ፤ የትግራይ ሕዝብም ጦርነት ሰልችቶታል ሲሉ የትግራይ ክልል ጊዜያዊ መስተዳድር ርዕሰ መስተዳድር ጌታቸው ረዳ ተናገሩ፡፡

በአዲስ አበባ ከተማ ወዳጅነት አደባባይ ‘ጦርነት ይብቃ፤ ሰላም እናጽና’ በሚል መሪ ሐሳብ የምስጋና እና የዕውቅና ሥነ ስርዓት እየተካሔደ ነው፡፡

በሥነ ስርዓቱ ላይ ንግግር ያደረጉት አቶ ጌታቸው ረዳ÷ ከፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት በኋላ በስምምነቱ መሠረት ሕዝቡን እና ክልሉን የሚጠቅሙ ተግባራት መከናወናቸውን ተናግረዋል፡፡

ለስምምነቱ በፍጥነት መተግበር ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ላሳዩት ከፍተኛ ድፍረት የተሞላበት ቁርጠኝነት በትግራይ ሕዝብ ስም እናመሰግናለን ብለዋል፡፡

ቀሪ ሥራዎችም በተያዘው ፍጥነት ልክ እንዲከናወኑ ጠይቀዋል፡፡

በትናንትናው ዕለትም የሕዝብ ትራንስፖርት በአፋር በኩል መጀመሩን ጠቁመው ይኸው አገልግሎት በአማራ ክልል በኩል እንዲጀመርም በጋራ መሥራት እንደሚገባ አመላክተዋል፡፡

ችግሮችን በሰለጠነ መንገድ መፍታት እተቻለ በክፉ የጠብ መንጃ ማንሳት አባዜ ላለፉት ሁለት ዓመታት እጅግ ደም አፋሳሽ ጦርነት ተደርጓል ነው ያሉት፡፡
ከፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት በኋላ ብዙ መሻሻሎች እንዳሉ ገልጸው÷ በቀጣይም የተቀሩት የስምምነቱ አካላት በሚገባ ተፈፃሚ እንዲሆኑ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

የትግራይ ሕዝብ ጦርነት እንደሰለቸውና ከዚህ በኋላ ጠብመንጃ የማንሳት ፍላጎት እንደሌለው አንስተዋል፡፡

እስካሁን ከቤት ንብረታቸው የተፈናቀሉ ወገኖች የሚመለሱበት እና በክልሉ የተቋረጠው የመማር ማስተማር ሥራ በተቻለ ፍጥነት ወደነበሩበት እንዲመለስ ጠይቀዋል፡፡
በወንድም የአማራና የአፋር ሕዝብ መካከል ሳይገባ የተፈጠረው ግጭት ታሪክ የማይሽረው ጠባሳ አሳድሮ አልፏል ያሉት አቶ ጌታቸው÷ አሁን ግን ሰላም በሚጸናበት ጎዳና መራመድ ይገባል ብለዋል፡፡

ግጭትና ጦርነትን ወደ ጎን ትቶ የሁሉም አካባቢ በተለይም የትግራይ አርሶ አደር የናፈቀውን ግብርና ማከናወን እንደሚፈልግም ነው የተናገሩት፡፡

የአፍሪካ ህብረት ከሚሽን ሊቀ መንበር ሙሳ ፋኪ መሃማት

በአዲስ አበባ ከተማ ወዳጅነት አደባባይ ‘ጦርነት ይብቃ፤ ሰላም እናጽና’ በሚል መሪ ሐሳብ የምስጋና እና የዕውቅና ሥነ ስርዓት እየተካሔደ ነው፡፡

በሥነ ስርዓቱ ላይ ንግግር ያደረጉት የአፍሪካ ህብረት ከሚሽን ሊቀ መንበር÷ በክርስትናና በእስልምና እምነት ተከታዮች ዘንድ ታላቅ ስፍራ ባላቸው በትንሳኤ እና በዒድ አልፈጥር በዓላት ማግስት ይህን ለመሰለ የሰላም ጉዳይ መሰባሰባችን ትልቅ ትርጉም አለው ብለዋል፡፡

አፍሪካውያን ከነበረው ክስተት በሁለት መንገድ ተምረናል ያሉት ሊቀመንበሩ÷ ከጦርነቱ ጥፋቱን ከስምምነቱ ደግሞ መፍትሄ መኖሩን ነው ብለዋል፡፡

ኢትዮጵያውያን የጦርነትን አስከፊነት እና የሰላምን ጥቅም በሚገባ ያውቁታል ያሉት ሙሳ ፋኪ መሃማት ለችግሮቻቸው በጥበብ እልባት ከማምጣት አንፃርም የከፍተኛ ልምድ ባለቤት ናቸው ነው ያሉት፡፡

ለዚህም ያላቸው የትብብር ጥንካሬና የአመራር ብቃት ናቸው ሲሉ ገልጸዋል፡፡

የአፍሪካ አህጉር ከመሰል ግጭቶች ልትፀዳ ይገባል ያሉት ሙሳ ፋኪ÷ ሱዳናውያንም ከዚህ ትልቅ ትምህርት በመውሰድ ግጭትን በማስወገድ ችግሮቻቸውን በሰከነ መንገድ ሊፈቱ እንደሚገባ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡

የሱዳን ተቀናቃኝ ሀይሎች ከኢትዮጵያ የሰላም ስምምነት ተምረው በውይይት ወደ ሰላም አማራጭ ሊመጡ ይገባል – ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ የሱዳን ተቀናቃኝ ሀይሎች ከኢትዮጵያ የሰላም ስምምነት ተምረው በውይይት ወደ ሰላም አማራጭ እንዲመጡ ጥሪ አቀረቡ።

የፕሪቶሪያውን የሰላም ስምምነት ተከትሎ በሂደቱ አስተዋጽኦ ላደረጉ ሁሉ በአዲስ አበባ የእውቅና እና ምስጋና መርሃ ግብር ተካሂዷል። በመርሐግብሩ ላይ በመገኘት መልእክት ያስተላለፉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ፤ የኢትዮጵያ የሰላም ስምምነት ለጎረቤት አገራትና ለመላው አፍሪካውያን ትምህርት መሆኑን ተናግረዋል።

ሰላም ምክንያት አይፈልግም ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ አገርና ህዝብን ከሚያፈርስ ጥላቻ በመላቀቅ ፍቅርን ለሚገነባው ሰላም ቅድሚያ መስጠት ያስፈልጋል ብለዋል። ሱዳናውያንም ከኢትዮጵያ የሰላም ሂደት ተምረው ያጋጠማቸውን ወቅታዊ ችግር በንግግር እንዲፈቱ ጥሪ አቅርበዋል።

ኢትዮጵያ ለሱዳን ወንድም ህዝብ ያላትን አጋርነት ለማሳየት ወደ ሱዳን በቅርቡ ሰብአዊ ድጋፍ ለመላክ መዘጋጀቷን ጠቁመዋል። ኢትዮጵያ ወደ ተለያዩ አገራት ሰላም አስከባሪ በመላክ ለሰላም ዘብ መቆሟን ጠቅሰው ፍቅርና አብሮነትን ለማጽናትም ካለን ላይ ቀንሰን ለሱዳናውያን ወገኖች አብሮነታችንን እናሳያለን፣ ሰላማቸውንም እንመኛለን ብለዋል።

All reactions:

7272

Exit mobile version