Site icon ETHIO12.COM

የመንግስትና ኦነግ ሸኔ ድርድር የስሜት መላ ምቶች

ኦነግ ሸኔ “ሸኔ” የተባለው በመንግስት ወይም በየትኛውም ወገን ሳይሆን ድርጅቱ በተለያዩ ምክንያቶች ሲከፋፈል ቆይቶ አቶ ዳውድ ኢብሳ ጋር ሲደርስ አምስተኛ በመሆኑ በዋንኛነት በኦሮምኛ “ሸን” አምስት ማለት ከመሆኑ ጋር ተያያዞ ነው።እነ አቶ ሊንጮ ለታ፣ ዳውድ ኢብሣ ፣ አባ ነጋ፣ ገላሳ ዲልቦ፣ ጄኔራል ከማል ገልቹ የየራሳቸውን ኦነግ ለመለየት የተለያየ ተቀጽላ ሲያደርጉ፣ በትግራይ አድርጎ ከኤርትራ ወደ ኢትዮጵያ የገባው ኦነግ ሸኔ መሆኑን አ፣እራሮቹ ናቸው ይፋ ያደረጉት። የዚህ ምክንያቱ ደግሞ ደጋፊዎች እንዲለዩዋቸው ብቻ እንደሆነ በተለያዩ አውዶች ተገልጿል።

ኦነግ በታንዛንያ የሚደረገውን የሰላም ንግግር አስመልክቶ ለሰላም መስፈን አስፈጊውን ሁሉ እንደሚያደርግ መግለጹ ዜና መሆኑ ቀርቶ ” ለምን ሸኔ ተባልኩ አለ” ሲል “መግለጫ አወጣ” የሚል መሪ ርእስ ተመርጧል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለፓርላማ ሌሊት ህዝብ ተኝቶ ሳይሆን በቀን በጠራራ ጸሃይ ” ኦነግ ባለቤቱ መብዛቱ ችግር ሆኗል” በማለት መናገራቸው ተዘንግቶ “በአማፅያኑ በኩል አንድ ወጥ አቋም ስላልነበርና ድርጅቱ በነበረው የተበታተነ መዋቅር ድርድር ለመጀመር አስቸጋሪ ሆኖ መሰንበቱንም ስምተናል” ሲሉ ራሳቸውን ሚስጢር ፈልፋይ ለማድረግ የሚጋጋጡ ታይተዋል.።

ድርጅቱ ያቀርበው ቅድመ ሁኔታ በመንግስት ተቀባይነት ማግኘቱን ቢጠቅሱም ድርጅቱም ሆነ ዜናው ያጎሉት ሁሉ ኦነግ አቅርቦ ሙሉ በሙሉ ተቀባይነት እንዳገኘ የተጠቀሰው ዜና ዝርዝር የለውም። ድርድሩ እንዲካሄድ አብዝተው ከደከሙት መካከል እንዳሉት ” ምንም ልዩ ቅድመ ሁኔታ አልተቀመጠም” በገለልተኛ ስፍራ ከኬኛ ውጪ ለመነጋገር ኦነግ ባቀረበው መሰረት መንግስት ከመቀበሉ ውጪ በማንም ወገን የቀረበ ቅድም ሁኔታ የለም። ለጊዜው እንዲገለጽ ባይፈለግም ሁለቱም ወገኖች የንግግር መነሻ አጀንዳ ላይ ተስማምተዋል።

” ድርድሩ ከትህነግ ጋር እንደሆነው ቀላል አይደለም” የሚለውና ከስምምነቱ ውጤት ተስፋ ይልቅ ጨለማን አጉልቶ ለማሳየት መሞከሩ ያስገረማቸው እነዚህ ወገኖች ” ውጤቱን እናየዋለን” በሚል ለጊዜው ዝምታ መርጠዋል። እልቂትና መፈናቀል እንዲቆም ሰላምን ማበረታታና ተደራዳሪዎች ላይ ጫና ማድረግ ሲገባ አንዳንድ ሚዲያዎች በዚህ ደረጃ ክፉውን ነቃሽ መሆናቸው “ምንድን ነው ፍላጎታቸው” አሰኝቷል።

ከኦነግ ሸኔ ጋር ለሚኖረው ድርድር ወደ ታንዛኒያ ያቀኑት የኢትዮጵያ ተደራዳሪዎች ማንነት ከመንግስት ወገን በይፋ አንድ ሁለት ተብለው እነ አምባሳደር ሬድዋን ሑሴን፣ ዶክተር ጌድዮን ጢሞቴዎስ፣ አቶ ከፍያለው ተፈራ ፣ጄነራል ደምሰው አመኑ፣ አቶ ቦንሳ እውነቱ መሆናቸው ገሃድ ሆኖ ሳለ “ሮይተርስ ውስጥ አዋቂዎችን ጠቅሶ” በሚል ሬድዋን ሁሴን የተደራዳሪዎች መሪ መሆናቸው ለመገለጽ የሞከሩ፣ ድርድሩ ውጤት አልባ የመሆን አዝማሚያ እንዲላበስ ያላቸውን ስሜት እየደፉበት ነው።

የኦፌኮ ከፍተኛ አመራር ” ዳውድ ኢብሳን በንግግሩ ቢያካትቱ ጥሩ ነበር። ባለኝ መረጃ ጥሩ ውጤት ይመዘገባል” ብለዋል። “በግል በኦሮሚያም ሆነ በሌሎች የአገሪቱ ክልሎች የተከሰተው እልቂትና መፈናቀል በምንም ሁኔታ እንዲቆም ምኞት አለኝ፤ የፖለቲካ ፍላጎትን በምስኪን ዜጎች ሞት ማስላትና ማወራረድ ሊያበቃ ይገባል” ሲሉ ሁሉም ወገን ለጊዜው የሰላም ንግግሩን በገሃድ ሊደግፉ እንደሚገባ አሳስበዋል።

አቶ ጃዋር ድርድሩ እንደሚደረግ ይፋ መሆኑንን ተከትሎ ” ከሰላም ውጪ ምንም አማራጭ የለም” ሲል ድጋፉን ሰጥቷል። ቀደም ሲል የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሽመልስ አብዲሳ ከታጣቂው ቡድን ጋር መንግሥት ሰላም ለማውረድ ፍላጎት እንዳለው በይፋ ሲያስታውቁ ጃዋር ድጋፍ የሰጠ ሲሆን በርካት ሚዲያዎችና የማህበራዊ ሚዲያ አዝማቾች አቶ ሽመልስን ሲያበሻቅጡ ነበር። አንድ ነጥብ አምስት ሚሊዮን ህዝብ ተፈናቅሎ ባለበት ሁኔታ እርቁን ማጣጣልና በመላ ምት ለማምከን መላላጥ “ትግሉ የትኛው ፕላኔት ላይ ላለ ህዝብ ነው?” አሰኝቶ ነበር።

ክልሉን የሚመራው ብልጽኛ ኦሮሚያም ሆነ በክልሉ ስም የሚጠሩ ተቀናቃኞች “ለምን አንድ አትሆኑም” የሚል ጫና የበዛባቸው በመሆኑ ጉዳያቸውን በውይይት የመፍታት ግዴታም እንዳለባቸው የሚነገሩ አሉ። “በኦሮሚያ ብዙ የፖለቲካ ድርጅቶች መኖር የለባቸውም” በሚል የኦሮሚያ ምሁራኖች በስፋት እየገለጹና እየመከሩም እንደሆነ ተስምቷል።

ንግግሩ ዛሬ እንደተባለው የተጀመረ ሲሆን ኢጋድ የጠብመንጃው ትግል ወደ ፖለቲካ እንደሚቀየር እምነቱን አስቀምጧል። ይህን ያሉት የኢጋድ ቃል አቀባይ ኑር ሙሀሙድ ሼይኽ ናቸው።

ሮይተርስ እንዳለው ሁለቱም ተደራዳሪ አካላት ንግግር መጀመሩን አሳውቀዋል። ዝርዝር መረጃ ኝ ይፋ አላደረጉም።

Exit mobile version