ኑሀሚን ” ማጥናት ብቻ” ስትል የሰቀለችበትን ልምድ አካፈለች

ኑሀሚን ደምበል ተወልዳ ያደገችው በኦሮሚያ ክልል፣ አሰላ ከተማ ነው። በትምህርቷ ሰቃይ ከሚባሉ ተማሪዎች መካከል አንዷ ናት። በ2014 ዓ.ም የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ብሔራዊ ፈተና 650 ውጤት አስመዝግባለች። ይህ ውጤት በአገር አቀፍ ደረጃ በሴቶች ከፍተኛው ነው። ሒሳብ 100፣ ፊዚክስ ደግሞ 96 ነው ያመጣችው። ኑሀሚን የሥነ ከዋክብት ተመራማሪ [አስትሮኖመር] የመሆን ህልም አላት።

በትምህርቷ ቀልድ አታውቅም

አትሌት ኃይሌ ገ/ሥላሴ ለእናቱ አየለች ደገፋ መታሰቢያ ባሠራው ትምህርት ቤት የ11ኛ ክፍል ተማሪ ሳለች ከፍተኛ ውጤት በማምጣቷ በትምህርት ቤቱ ውስጥ ካሉት ብሎኮች አንደኛው በስሟ እንደተሰየመላትም ትናገራለች። ኑሀሚን በወቅቱ ከፍተኛ ደስታ ተሰምቷት እንደነበር ትናገራለች።

“ 11ኛ ክፍል 99.3 አምጥቼ ክብረ ወሰን ይዤ ነበር።ያኔ ነው በስሜ ብሎክ የተሰየመው። ስሜን ስመለከት በጣም ነው ደስ ያለኝ። ይህም ሌሎች ተማሪዎች በትምህርታቸው እንዲበረቱ መነሳሳትን ፈጥሯል። እኔ የያዝኩትን ክብረ ወሰን ሌሎች እንዲሰብሩት ያበረታል” ስትልም የዚያን ቀን በደስታ ስታለቅስ እንደነበር ታስታውሳለች።

ኑሀሚን በቅርቡ ይፋ በተደረገውና በአስደንጋጭ ሁኔታ ጥቂት ተማሪዎች ብቻ 50 ከመቶ በላይ ባመጡበት ፈተና 650 ነው ያመጣችው።በዚህ የፈተና ዘመን ከፍተኛ ሆኖ የተመዘገበው ውጤት 666 ነው።

ለዚህ ውጤት የበቃችው በደንብ በማጥናቷ እንደሆነም ኑሀሚን ትናገራለች። ቤተሰቦቿ፣ አስተማሪዎቿ እና ትምህርት ቤቷም ድጋፍ ያደርጉላት ነበር።

“ለዚህ ውጤት ለመብቃትም የእነርሱ ድጋፍ ከፍተኛ ድርሻ አለው” ትላለች ኑሃሚን።

የኑሀሚን አባት የሆኑት አቶ ደምበል ገመዳ በልጃቸው ውጤት እጅግ ነው የተደሰቱት። “ ውጤቱን ስሰማ እንደገና የተወለድኩ ያህል ነበር የተሰማኝ” ይላሉ።

አቶ ደምበል የልጃቸውን ውጤት ለመስማት ውጤት የሚነገርበትን ጊዜ ሲጠባበቁ ነበር የቆዩት።

“የዚያን ቀን ሥራ ውዬ፣ ማታ ቤት ስገባ ‘ውጤት ወጥቷል’ የሚል ጭምጭምታ ነበር” የሚሉት አቶ ደምበል፣ ቁጭ ብለው የተለያዩ መገናኛ ብዙኃንን እየተከታተሉ መጠባበቅ እንደጀመሩ ይናገራሉ።

ምሽት አምስት ሰዓት ላይ በጉጉት ሲጠበቅ የነበረው የኑሀሚን ውጤት ታወቀ።

“ከዚያ በኋላ ያለንበትን አናውቅም፤ በደስታ ቁጭ ብለን አደርን” ይላሉ።

ከአገር ውጭም ከአገር ውስጥም “የእንኳን ደስ አላችሁ እና ‘ስንት አመጣች?’ ጥያቄ” በርካታ ጥሪዎችንም አስተናግደዋል።

ኑሀሚን እንደምትለው የተለየ የአጠናን ስልት ባይኖራትም ሳይገባት የምታልፈው ነገር ግን የላትም። ያልገባትን ግን ለነገ አታሳድርም። በዛሬ ታምናለች።

“ብዙ ጊዜ ለትምህርት አስቀድሜ ተዘጋጅቼ ነው የምሄደው። ዛሬ የተማርኩትን ትምህርት ዛሬውኑ አጠናለሁ እንጂ ለነገ ብዬ አላሳድርም።አስተማሪ ሲያስተምርም በአግባቡ ነው የማዳምጠው።ያልገባኝን ነገር እዛው ትምህርት ቤት እያለሁ ነው አስተማሪዬን ጠይቄ፣ ከገባኝ በኋላ ነው ወደ ቤቴ የምገባው።የማስተማሪያ መጻሕፍት በደንብ አነባለሁ። የሚያግዙኝ አጋዥ መጻሕፍትንም በደንብ ነው የማነበው።የሒሳብ ስሌቶች ሲኖሩ ጥያቄውን አይቼ በራሴ ሠርቼ መልሱን እዛው ላይ አመሳክራለሁ።” ትላለች።

አባቷ አቶ ደንበል ገመዳም ከልጃቸው የታዘቡት ይህንኑ ነው።

“እሷ ብዙ በጥናት የሚያግዛት ሰው አትፈልግም።ውጭ አስተምሩኝ እያለችም አታስቸግርም። ሌላ ቦታ ሄጄ እማራለሁ አትልም” የሚሉት አቶ ደምበል፣ ኑሀሚን መጽሐፍ ግዙልኝ ከማለት ውጭ ሌላ የምታስቸግረው እንደሌላት ይናገራሉ።

“መጽሐፍ እንገዛላታለን። ቴክኖሎጂ ነክ ነገር ደግሞ ስልክ እና ዋይፋይ አሟልተናል። ከትምህርት ቤት ስትመለስ ታጠናለች። እንደ ሌላው ልጅ ወጥታ ሌላ መዝናኛ ቦታ አትገኝም” ብለዋል።

ኑሀሚን አስትሮኖመር የመሆን ህልሟ እንደምታሳካው እምነት አላት።

የ2014 ዓ. ም. የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና ውጤት ከወሰዱት ከ900 ሺህ በላይ ተማሪዎች መካከል ከ50 በመቶ በላይ ውጤት ያስመዘገቡት ከ30 ሺህ በታች የሚሆኑት ናቸው።

ከ700 ከተያዘው አጠቃላይ የፈተና ውጤት 666 ሆኖ የተመዘገበ ሲሆን ኑሀሚን 650 በማምጣት በሴቶች ከፍተኛውን ውጤት አስመዝግባለች።

ቢቢሲ አማርኛ

የዝግጅት ክፍሉ – ቢቢሲን ያምሰግናል።በወንዶች ከፍተኛ ውጤት ያመጣውን ተማሪ መረጃ ወይም ዝርዝር ለሚያካፍሉን ምስጋናችን ትልቅ ነው

Leave a Reply