Site icon ETHIO12.COM

ወርቁ አይተነው የዘይት ፋብሪካቸውን እየሸጡ መሆኑ ተሰማ

ፎቶ አቶ ወርቁ አይተነው፣ ከሪፖርተር የተወሰደ

አቶ ወርቁ አይተነው ደብለው ኤ ሲሉ የሰየሙት ዘይት ማምረቻ 5.2 ቢሊዮን ብር እንደፈጀ በምረቃው ላይ መናገራቸው ይታወሳል። ይህ በደብረማርቆስ ከተማ በ17 ሔክታር ቦታ ላይ የሚገኝ ፋብሪካ ለአንድ የውጭ ዜጋ ለማስተላለፍ የሽያጭ ሂደቱ እየተጠናቀቀ መሆኑ ተሰማ።

“ጥራት ያለው የምግብ ዘይት በማምረት በዚህ ዓመት 40 በመቶውን የሐገር ውስጥ ፍላጎት ለማቅረብ እየሠራን ነው” በማለት ግንቦት 30 ቀን 2013 ዓም በምረቃው ስነ ስርዓት ላይ የተናገሩለትን ፋብሪካ አቶ ወርቁ አይተነው ለሌላ የውጭ አገር ባለሃብት ለማስተላለፍ የወሰኑበት ምክንያት ዝርዝር ባይገለጽም ከገንዘብ ወይም የስራ ማስኬጃ ችግር የተነሳ መሆኑ ተመልክቷል።

በምን ያህል እነደተሸጠና በድርጅቱ ላይ ያለው የባንክ እዳ በምን መልኩ እንደተላለፈ ወይም ሊተላለፍ እንደተፈለገ በዝርዝር ያላብራሩት የመረጃው ምንጮች፣ የሽያጭ ሂደቱ በመጠናቀቅ ላይ ስለመሆኑ ግን እርግጠኛ መሆናቸውን ተናግረዋል። ፋብሪካው ከተመረቀ ሁለት ዓመት ቢሆነውም በተባለው መሰረት ወደ ስራ አለመግባቱን አስታውሰው ቢሸጥም ሊገርም እንደማይችል ገልጸዋል።

የደብሊው ኤ ኢንቨስትመንት ግሩፕ ባለሐብት አቶ ወርቁ አይተነው የምረቃ ሥነ ሥርዓቱን በተመለከተ በሰጡት መግለጫ እንዳሉት ፋብሪካው በሙሉ አቅም ማምረት ሲጀምር የተለያዩ የቅባት እህሎችን በመጠቀም በቀን የጥራት ደረጃውን የጠበቀ ከአንድ ሚሊየን 350 ሺህ ሊትር በላይ ዘይት የማምረት አቅም አለው። በአሁኑ ወቅት ለአንድ ሺህ 500 ዜጎች የሥራ እድል በመፍጠር ተጠቃሚ ማድረግ እንደቻለ የተናገሩት ባለሐብቱ በሙሉ አቅሙ ወደ ማምረት ሲገባ በአንድ ፈረቃ ብቻ ከ3 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ዜጎች የሥራ እድል እንደሚፈጥርም አሚኮ በወቅቱ ዘግቦ ነበር።

በትምህርት ባይገፉም በንግድ እሳቤያቸው “ልበ ብርሃን” የሚባሉት አቶ ወርቁ አይተነው ግዙፋ የምግብ ዘይት ማምረቻው በቀን 18 ሺህ ኩንታል የቅባት እህል እንደሚጠቀም፤ በዓመትም ከ18 ቢሊዮን ብር በላይ ወጭ የሚደረግበት 6 ሚሊዮን ኩንታል የቅባት እህል እንደሚፈልግ፣ በየዓመቱ የሀገር ውስጥ የምግብ ዘይት ፍላጎትን ለማሳደግ በትኩረት እንደሚሰራ፣ ከዚህ ጎን ለጎን የውጭ ምንዛሬ ለማግኘት ወደዓለም አቀፍ ገበያ የማቅርብ እቅድ እንዳላቸው አስታውቀው ነበር።

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይና ምክትላቸው አቶ ደመቀ መኮንን ጨምሮ ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናት በተገኙበት የተመረቀው ይህ ፋብሪካ ለሙከራ ያመረተው ምርት ተውዳጅና ጥራቱ “ድንቅ” ተብሎ ነበር። ምክንያቱ ከባለሃብቱ ቃል በቃል ባይነገርም እንደተባለው ግን ማምረት ሳይችል ቆይቷል። ይፋ ያልወጡ ወገኖች እንደሚሉት ግን ባለሃብቱ ከፈተኛ የሆነ የገንዘብ ችግር ገጥሟቸዋል። ከበርካታ ባንኮች ብድር ስለወሰዱ ተጨማሪ ማግኘት አልቻሉም። ጠይቀውም ተከልክለዋል። ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁ የክልሉ ከፍተኛ አመራር ባለሃብቱን ለመርዳት አሁን ጸደይ ባንክ ከተባለው የአማረ ብድርና ቁጠባ ተቋም (አብቁተ) ብድር ተፈቅዶላቸው ነበር።

እንደተባለው በገንዘብ ችግር ይሁን በሌላ የዘይት ማምረቻው መሸጡን ከክልሉ አመራሮች ለመረዳት ተችሏል። ለግዜው የገዢውን ስምና የመጡበትን አገር መጠቀስ ያልፈለጉት የመረጃው ምንጮች አቶ ወርቁ ይህን ግዙፍ ፋብሪካ በባንክ የብድር ጫና ሳቢያ ይሽጡ ወይም በሌላ ያሉት ነገር የለም። ይህንኑ ለማጣራት በባለሃብቱ የእጅ ስልክ በተደጋጋሚ ብንደውልም ምላሽ አልሰጡም።

የኢትዮ 12 ተባባሪ ያነጋገራቸው ለባለሃብቱ ቅርብ የሆኑ ሰዎች የሽያጭ ሂደት መጀመሩን ያውቁ እንደነበር ምስክረነት ሰጥተዋል። ይሁን እንጂ ሽያጩ መጠናቀቁን እንዳልሰሙ አመልክተዋል።

አቶ ወቁ አይተነው ግምቱ አንድ ቢሊዮን ዶላር የሚዘለቅ በቀን 12 ሺህ ቶን ሲሚንቶ የሚያመርት የሲሚንቶ ፋብሪካ ለመገንባት ስራ መጀመራቸውን በሪፖርተር እንግሊዝኛ ጋዜጣ ኦገስት 20, 2022 ዕትም ይፋ ተደርጎላቸው እንደነበር ይታወሳል። ሪፖርተር በዘገባው ግንብታውን “ታይቶ የማይታወቅ” ሲል አምስት ቢሊዮን ወጪ እንደወጣበት የተነገረለትን የዘይት ፋብሪካ አስታውሷል።

ደብሊው ኤ የሚባለው ይህ የሲሚንቶ ፋብሪካ በ150 ሄክታር መሬት ላይ ተንጣሎ የሚገነባና በሁለት ዓመት ጊዜ ውስጥ ወደ ምርት ስርጭት እንደሚዛወር ጊዜ ቆጥሮ የተጀመረ ፕሮጀክት እንደነበረም የሪፖርተር ዘገባ ያስረዳል። ይሁን እንጂ አሁን ላይ ምን ደረጃ እንደደረሰ እስካሁን ይፋ የተገለጸ ነገር የለም።

አቶ ወርቁ በተመሳሳይ በሪፖርተር ጋዜጣ በኩል በአቬየሽን ኢንቨስትመንት ለመሰማራት ዝግጅት ማጠናቀቃቸው ተገልጾላቸው ነበር። አቶ ወርቁ ይህን ካስታወቁ በሁዋላ በተከትታይ ፕሮጀክታቸው እመን ደረጃ ላይ እንደደረሰ ይፋ አልሆነም።

አቶ ወርቁ ደግ፣ ለጋስ፣ በሚኖሩበት አካባቢ ህዝብ የሚወደዱ እንደሆኑ በርካቶች ይመስከራሉ።

Exit mobile version