Site icon ETHIO12.COM

የእነ መስከረም አበራ መዝገብ ወደ ሽብር ክስ ተቀየረ፤ ጠበቃ መቃወሚያ አቅርቧል

መስከረም አበራን ጨምሮ ስድስት ግለሰቦች ቀደም ሲል በተጠረጠሩበት መዝገብ ማጣራት ሲደረግ ህጋዊውን ስርዓት በኢመደበኛ አደረጃጀት ለመናድ ሲሰሩ መቆየታቸውን የሚያረጋግጥ መረጃ ማግነቱን ገልጾ ፖሊስ ክሱን ወደ ሽብር ክስ መዛወሩ ተሰማ። የተጠርጣሪዊች ጠበቃ በሌላ ክስ ተከሰው ሳለ ክሱን ማዘዋወሩ አግባብ አለመሆኑን ጠቅሶ ተቃውሞ አሰምቷል።

ዛሬ ባስቻለው ችሎት “ምርመራ ስናደረግ ያገኘነው መረጃ የሽብር ስለሆነ አዲስ የሽብር ክስ ለንመሰርት እንፈልጋለን” በሚል መርማሪ ፖሊስ ባቀረበው የክስ ማሻሻያ ማብራሪያ መሰረት የጠየቀው የአስራ አራት ቀን ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ ተፈቅዶለታል።

የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 1ኛ ጊዜ ቀጠሮ ችሎት ፖሊስ ያቀረበውን የሽብር ወንጀል የጥርጣሬ መነሻን እና የተጠርጣሪዎችን የመከራከሪያ ነጥብ ተመልክቶ ነው ለተጨማሪ ምርመራ ለፖሊስ 14 ቀን መፍቀዱን የመንግስትና የግል ሚዲያዎች አስታውቀዋል።

በሸብር ወንጀል ተጠረጠረው ዛሬ ከሰዓት በኋላ ፍርድ ቤት የቀረቡት ተጠርጣሪዎቹ መስከረም አበራ፣ ሳሮን ቀባው፣ ዮርዳኖስ አለሜ፣ ቢሰጥ ተረፈ፣ ዶ/ር አሰፋ አዳነ እና ታደሰ መንግስቱ እንደሆኑ በችሎት ተዘርዝሯል።

ተጠርጣሪዎቹ ህገ መንግስቱንና ህገመንግስታዊ ስርዓቱን በኃይል ለማፍረስ በማሰብ ኢ – መደበኛ አደረጃጀት በመፍጠር ፣ወጣቶችን በመመልመል፣ ለሽብር ወንጀል የሚውል ገቢ በማሰባሰብ ተግባር ተሳትፈዋል ሲል መርማሪ ፖሊስ የጥርጣሬ መነሻውን በዝርዝር ጠቅሶ ለጊዜ ቀጠሮ ችሎቱ አቅርቧል።

በዚህ የሽብር ወንጀል የመነሻ ጥርጣሬ ተጨማሪ ማስረጃ ሰብስቦ ለመቅረብ 14 ቀን እንዲሰጠው ጠይቋል።

የተጠርጣሪ ጠበቆች በበኩላቸው ” ሁሉም ተጠርጣሪዎች ከዚህ በፊት በሌላ ፍርድ ቤት በሁከትና ብጥብጥ ማስነሳት ወንጀል ተጠርጥረው በጊዜ ቀጠሮ መዝገብ እየቀረቡ ባለበት ሂደት ላይ ዛሬ የሽብር ወንጀል ተብሎ መቅረባቸው ተገቢነት የለውም ”ሲሉ ተከራክረዋል። የተጠርጣሪዎቹ ዋስትና መብት እንዲከበር ጠይቀዋል።

መርማሪ ፖሊስ በበኩሉ ከዚህ በፊት በተጠረጠሩበት ሁከትና ብጥብጥ አመጽ ማስነሳት ወንጀል ላይ በተደረገባቸው የማጣሪያ ምርመራ የሽብር ወንጀል መፈፀሙን የሚያመላክቱ ተጨማሪ ማስረጃዎች በመገኘታቸው ምክንያት በሽብር ወንጀል መዝገብ እንዲቀርቡ ማድረጉን ጠቅሶ መልስ ሰጥቷል። ዛሬ ከሰአት የጊዜ ቀጠሮ መዝገቡን የተመለከተው ችሎቱ ተጨማሪ ምርመራ መደረጉ አስፈላጊ ነው በማለት ለፖሊስ የ14 ቀን ጊዜ ፈቅዷል።

Exit mobile version