Site icon ETHIO12.COM

ጎንደርና ሸዋ መክሮ ወሰነ፤ የተስተጓጎሉ መንገዶች ነጻ ሆኑ

መከላከያ በአማራ ክልል በስፋት መሰማራቱን “ህዝብ ጨነቀው፣ ህዝብ ደነገጠ” በሚል ዜና ያደረጉ ዜናቸውን አላሻሻሉም። በጎንደርና በደብረሲና ሸዋ ሮቢት መስመር ለተሽከርካሪ ታግደው የነበሩ መንገዶች ሙሉ በሙሉ ክፍት ሆነዋል። ይህን ያስታወቁት በስፍራው ያሉና ያዩ እማኞች ናቸው። የድርጅት ሰዎችም መስክረዋል።

በግል የማህበራዊ ገጻቸው ያስታወቁ፣ በግል ምስክርነታቸውን የሰጡ እንዳሉት የአገር መከላከያ ሰራዊት ከህዝብ ጋር ባደረጋቸው ጥበብ የተሞላው መስተጋብር፣ ከህዝብ ጋር በተደረገ ውይይት መግባባት ላይ ተደርሷል። ተዘገተው የነበሩ መንገዶች ሙሉ በሙሉ ክፍት ሆነዋል።

በአማራ ክልል የሚካሄደውን ተቃውሞ በድርጅት ደረጃ በገሃድም ይሁን በህቡዕ ማን ሃላፊነት ወስዶ እንደሚመራው ለብዙዎች መነጋገሪያ እንደሆነ በስፋት በሚነገርበት ወቅት አቶ በለጠ ሞላ “ጩኸቱ ግን የማነው? መነሻውስ ከየት ነው?ፍላጎቱስ ምንድን ነው?” በሚል የግል ፍርሃቻና አስተያየታቸውን አስፍረው “ህዝብ ከጩኸት ወጥቶ ወደ ውይይት ማምራት አለበት” ብለው ነበር።

በተመሳሳይ የመንገድ መዘጋቱንና ይኸው ባለቤቱ በውል የማይታወቀውን የአመጽ ጥሪ የሚደግፉ ሚዲያዎች አየር ሃይልን፣ መከላከያን፣ እንዲሁም ዕርቅና ሰላም የሚሰብኩ ወገኖችን ክፉኛ እያወገዙ ነው።

“በቂ ውይይት ሳይደረግ ወደ ግጭት መሄድ የለብንም ብለን አበክረን ተከራክረናል። ጎንደር ከጠዋት ጀምሮ በተደረገ ውይይት መንገዶች እየተከፈቱ ነው። ጥሩ ስራ ነው። ውይይቱ የለብ ለብ መሆን የለበትም። ችግሮቻችን ነቅሶ በደንብ መነጋገር ያስፈልጋል። ተደጋጋሚ ውይይት በማድረግ ወጥ ሃሳብ መያዝ መልካም ነው። ወጥ እና የተገመገመ ሃሳብ ተይዞ ትግል ከተደረገ ማሸነፍ ይቻላል። ስለሆነም ውይይቱ እስከ ቀበሌ ድረስ ይቀጥል። የተራራቁ ሃሳቦች ይቀራረቡ። ሁሉም በየፊናው እየታገለ ያለው ለህዝብ ተጠቃሚነት እስከሆነ ድረስ ምክክሩ እና ውይይቱ ይቀጥል… !” ሲሉ የአብኑ ስራ አስፈጻሚ አቶ ጋሻው መርሻ በጎንደር ሰላም መስፈኑን አብስረዋል። አያይዘውም “ይህ እንዲሆን ያደረጋችሁ አካላት በሙሉ ምስጋና ይገባቹሃል…!” ብለዋል።

የአማራ ህዝብ ጥያቀዎቹን ሁሉ ወዳጅ በማብዛት፣ ሌሎችም እንዲጋሩት በማድረግ ጥበብ በተመላው መንገድ ማከናወን እንዳለበት የሚያምኑ ደጋግመው ውይይትና ሰላም መቅደም እንዳለበት ያምናሉ።

እነ ሻለቃ ዳዊት ወልደ ጊዮርጊስና በኢትዮጵያ ሰላምና መረጋጋት አይናቸው ደም የሚለብስ ነጭ ለባሾች በስውርና በግልጽ አመጹን እየመሩት እንደሆነ በርካታ ምስክሮች፣ የሚዲያ ክተታቸውና አዛኝ መስለው ለመታየት ከሚያደርጉት ሩጫ በቀላሉ መረዳት እንደሚቻል በርካቶች ይገልጻሉ። በተለይም ሻለቃ ዳዊት ጎረቤት አገር እየመሸጉ እንደሚዶልቱ፣ በቅርቡ አውስትራሊያ ባደረጉት ንግግር ” ንቃት አብቅቷል፣ ወደ ተግባር እርምጃ እናመራለን” ማለታቸው የዚሁ ማሳያ እንደሆነ የሚናገሩና ንግግራቸውን የሚጠቅሱ አሉ።

ሻለቃ ዳዊት የኢትዮጵያ ምርጭ ጀነራሎች ያለቁበትን ሆን ተብሎ እንዲከሽፍ ታስቦ የተዘጋጀ መፈንቅለ መንግስት የመሩ መሆናቸውን ለኢሳት መናገራቸው ይታወስል። ሱዳን ሆነው ሲመሩትና ግንኙነት ዘርግተው ሲቆጣጠሩት በነበረው መፈንቅለ መንግስት ኢትዮጵያ ቁልፍ የጦር መሪዎቿን ካጣች በሁዋላ ጦሩ መሰበሩን ምስክሮች በጥልቀት ጽፈውበታል።

ጥያቄው እንዲህ ያሉትን ሰው ዛሬ አብዛኛው ሳይሆን እጅግ ጥቂቶቹ “አማራ ነን” የሚሉ እንዴትና በምን መስፈርት ተቀበሉት? የሚለው ነው። አቶ በለጠ እንዳሉት “ከጩኸቱ ጀርባ የሻለቃውን ዳራ እየረገጠ የሚጋልበው ማን ነው?” የሚለው ነው።

“አንድ ሁለት ተብሎ የአማራ ህዝብ ጥያቄዎች ቢለዩ እውን ሻለቃ ዳዊት የሚመሩት የህቡዕ ሃይልና የሚዲያ አድማ አሁን በያዘው መልኩ ሊያስፈጽመው ይችላል” ሲሉ የሚጠይቁ፣ አቶ በለጠ ሞላ የሚጠይቁትን ከመጠየቅ፣ አቶ ጋሻው የተመኙትን ከመመኘት የዘለለ አማራጭ እንደማይኖር ያልገባቸውና ተደናግረው የነበሩ እየተረዱ እንደሆነ የውይይቱ አውዶች ያስረዳሉ። በጎንደር ውይይት ላይ የተሳተፉ ያሉትም ይህንኑ ነው።

“ጎንደር የለውጥ ማርሽ ቀያሪ ነው። ጎንደር ሲቃወምና ሲደግፍ ያውቃል። በአንድ ወቅት ጊዜ ጠብቆ ” የኦሮሞ ደም ደሜ ነው” ሲል ለውጡ ጥርስ አበቀለ። ተናከሰ። የአማታ ህዝብ ላይ ግድያው ሲበረክት በድፍን ኦሮሞ ላይ ዘመቻ ተጀመረ የዛኔ ” ጸባችን ከኦሮሞ ሳይሆን ከኦህዴድ ጋር ነው” በሚል ጎንደር ተቃውሞውን አስተካከለው” በሚል መረጃ አጣቅሰው አስተያየት የሰጡ፣ ነገሮች በቅርቡ መልክ እንደሚይዙ አመልክተዋል።

በሰሜን ሸዋ አቅጣጫ በደብረሲና፣ ሸዋ ሮቢት የተዘጋው መንገድ መከላከያና ህዝብ መክረው ለትራፊክ ክፍት እንዳደረጉት ምስክሮች አመልክተዋል። ምንም ጊዜ ለመከላከያ ሰራዊት ክብርና ፍቅር እንዳላቸው በገሃድ የገለጹት የአካባቢ ነዋሪዎች በበርካታ ጉዳዮች መጋባባት ላይ ደርሰዋል። መንግስት ውስጡ ያለውን አተራማሽ እንዲያጸዳም ጠይቀዋል።

Exit mobile version