Site icon ETHIO12.COM

አማራ ክልል “ህዝብ አስታግሱልን” ማለቱን አስታወቀ

ሰላም የሁልጊዜም ብቸኛ አማራጫች መሆኑን አመልክቶ ክልልና ሀገር አፍራሽ ተግባር ውስጥ ለተሰማሩ ጥሪና ማስጠንቀቂያ ተሰተ። ብጥብጥና ሁከት የሚቀሰቅሱ የሚሳተፉ ግለሰቦች እንዲሁም ቡድኖች ሁሉ ከድርጊታው እንዲቆጠቡ የአማራ ክልል ያስታወቀው ወቅታዊ ሁኔታን አስመልክቶ ባወጣው መግለጫ ነው።

በመግለጫው ክልሉ “ህዝብ ምስክሬ ነው” ሲል እንዳስታወቀው መልካሙን የፋኖ ስም አለ አግባብ በመጠቀም ዘረፋ ውስጥ የገቡ፣ በወንጀል የሚሳተፉና ህዝብ “አስታግሱልን” ሲል ምሬት ያቀረበባቸው አሉ።

የመግለጫው ሙሉ ቃል እንደሚከተለው ቀርቧል፦

ከአማራ ክልል መንግሥት በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ የተሰጠ መግለጫ

ሰላም የሁልጊዜም ብቸኛ አማራጫችን ነው!

የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት የዜጎችን ሰላም፣ ህልውና፣ የኑሮ መሻሻል እና ብሔራዊ አንድነትን ማፅናት የሚያስችሉ የሰላም፣ የልማት እና የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ የፖሊሲ ጉዳዮችን በመፈፀም እና በማስፈጸም ውጤታማ ክንውኖችን በማድረግ ላይ ይገኛል።

ከገጠሙን ፈተናዎች ጋር ፅኑዓን ሁነን እስከ መሥዋዕትነት ድረስ በመታገል የለውጡ ምዕራፍ ከተጀመረ ጊዜ አንሥቶ ሕዝባችን በሰላም፣ በልማት እና ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ላይ ቀጥተኛ ተሳታፊ እና በፍትሐዊነት ተጠቃሚ ይሆን ዘንድ ያላሰለሰ ጥረት ሲደረግ ቆይቷል፤ እየተደረገም ይገኛል።

በሰሜኑ የሀገራችን ክፍል በሀገር መከላከያ ሠራዊት ላይ የደረሰውን ጥቃት መነሻ በማድረግ የፌዴራል መንግሥቱ የሀገርን ሉዓላዊነት እና የግዛት አንድነት ለማስጠበቅ ከታጠቁ ኃይሎች ጋር በገባበት ጦርነት ሕዝባችን የብዙ ጉዳቶች ሰለባ ሁኖ አልፏል። እንደ ሀገር የተፈፀመብንን ወረራ ለመቀልበስ መላው የክልላችን ሕዝብ ከሀገር መከላከያ ሠራዊት እና ከፀጥታ አካላት ጎን በመቆም ከመላው ኢትዮጵያዊ ጋር ተባብሮ ጉዳቱን ማስቆም እና መቀልበስ ተችሏል።

የክልላችን መንግሥት የድኅረ-ጦርነት እቅድ አውጥቶ ተፈናቃዮችን በዘላቂነት ማቋቋም፤ ጉዳት ለደረሰባቸው በቂ እንክብካቤ ማድረግ፣ የፈረሱ አስተዳደራዊ መዋቅሮችን መልሶ ማደራጀት፣ የወደሙ መሠረተ ልማቶችን መልሶ መጠገን ከሁሉም በላይ ደግሞ በሕዝባችን ላይ ፀንቶ የነበረው የጦርነት ሥነ ልቡና ወደ ቀደመው የሰላም እና ልማት ሥነ ልቡና ለመመለስ መጠነ ሰፊ ሥራዎች ተሠርተዋል፤ እየተሠሩም ይገኛሉ።

በድኅረ ጦርነት የክልሉም ሆነ የፌዴራል መንግሥቱ ከመንግሥት የፀጥታ መዋቅር ውጭ በፈቃደኝነት ተሰባስበው በጎ አስተዋጽኦ ላደረጉ ቡድኖች አስፈላጊውን እውቅና እና የጀግና የክብር ሽልማት በማበርከት የትውልድ ተምሳሌቶች ተደርገው እንዲዘከሩ አድርጓል።

በጦርነት ጊዜ ሁሉም ተዋጊ እና ተጠራጣሪ እንዲሁም የተጠቂነት እና የመወረር ሥነ ልቡና የነበረበትን ሁኔታ ቀይሮ የተገኘውን የሰላም አየር በመጠቀም ወደ መልሶ መቋቋም፣ ልማት እና ዘላቂ ሰላም ለማምጣት መጠነ ሰፊ ሥራዎች ተከናውነዋል። በክልሉ ውስጥ እየተስፋፋ የነበረውን የጦርነት አድማስ ለመቀልበስ የተንቀሳቀሰውን ኃይልም ወደ ሰላማዊ ሕይወቱ ለመመለስ እና አይበገሬ የልማት አርበኛ አድርጎ ለመጠቀም መጠነ ሰፊ ውይይቶች ተደርገዋል።

መንግሥት ባቀረበው ጥሪ መሠረት በፈቃደኝነት ሕዝባቸውን ከጥቃት ለመከላከል አደረጃጀት ፈጥረው እና በግንባር ተሰማርተው አኩሪ ገድል ለፈጸሙት ወገኖቻችንም ይኸው የሰላም አማራጭ ተዘርግቶ ቀጣዩን ዘመን በሕዝባቸው ዘንድ ተከብረው ወቅቱ የሚጠይቀው አገልግሎት ውስጥ በመሳተፍ ተጠቃሚ እንዲሆኑ የክልሉ መንግሥት ብዙ ጥረቶች እና ውይይቶች አድርጓል።

ሁኖም ግን በእነዚህ አደረጃጀቶች ውስጥ የሚገኙ ጥቂት ኃይሎች በቅንነት ሀገራቸውን ባገለገሉ ሐቀኞች ስም በመጠቀም የግል ጥቅማቸው እንዳይቋረጥ አደረጃጀት የፈጠሩበትን መሠረታዊ ዓላማ በመዘንጋት እና ፖለቲካዊ መልክ በመስጠት፣ የአማራ ሕዝብ ፍላጎት ባልሆነበት ሁኔታ በመንግሥት የፀጥታ አካላት ላይ ትንኮሳ በማድረግ ክልላችን እና ሀገሪቱን ወደ ትርምስ በመውሰድ በውጭ እና በውስጥ የተደራጁ ኃይሎች መጠቀሚያ ለመሆን ተንቀሳቅሰዋል።

ነገር ግን ዛሬም ቢሆን በዚህ ተግባራቸው ምክንያት የመንግሥት ለሰላም የተዘረጉ እጆች ሳይታጠፉ የሰው ሕይወት ያጠፉ፤ የመንግሥትን የፀጥታ መዋቅር ለማፍረስ ትንኮሳ ያደረጉ፤ ዘረፋ እና የለየለት ውንብድና ውስጥ በመግባታቸው ምክንያት ሕዝብ አስታግሱልን በማለት ጥያቄ ያቀረበባቸው እና በከፍተኛ ሆደ ሰፊነት የቀረበውን የሰላም አማራጭ ገፍተው መንግሥትን ደካማ ለማድረግ እና ለመገዳደር የሞከሩ ቡድኖች ላይ መንግሥት በተመረጠ ሁኔታ ሕግ የማስከበር ሥራ ላይ ይገኛል።

የሕግ ማስከበር እርምጃው በገለጽናቸው ምክንያቶች ችግር ባለባቸው በጣም ውስን የክልላችን አካባቢዎች የሚደረግ እንጂ ሁሉንም የክልላችን አካባቢዎች የሚመለከት አለመሆኑንም መገንዘብ ያስፈልጋል። ጽንፈኛ የሆነው የማኅበራዊ ሚዲያ “አንቂ” ነኝ ባይ እንደሚለው ሕዝባዊ እምቢተኝነት ውስጥም አለመሆናችን መታወቅ አለበት። እንዲያውም ሕዝባችን በሰላም ወጥቶ እንዳይገባ፤ ሠርቶ እንዳይበላ ለማድረግ የሚሞክሩትንና ከሰላማዊ አማራጮች ጋር የተፋቱትን ቡድኖች እንድናስታግስለት አበክሮ ሲጠይቅ የቆየ መሆኑን ራሱ ሕዝባችን የሚመሰክረው ሐቅ ነው።

በሌላ መልኩ እየተከናወነ የሚገኘው የሕግ ማስከበር ሥራ የአማራን ሕዝብ ትጥቅ ማስፈታት አለመሆኑን ደጋግመን ለሕዝባችን አሳውቀናል። እየተከናወነ የሚገኘው የሕግ ማስከበር የክልላችንን ሕዝብ ወደ ዘላቂ ሰላም በማስገባት የሕዝባችን የትግል ዓላማ አልፋ እና ኦሜጋ የሆነውን ሰላም፣ ፍትሐዊ ልማት እና ተጠቃሚነትን እውን ለማድረግ መሆኑን መረዳት ያስፈልጋል።

በዚህ የሕግ ማስከበር ሥራ የትኛውም በክልላችን የሚኖር ሰላማዊ ዜጋ ሠርቶ የሚለወጥበት፤ በሰላም ወጥቶ የሚገባበት እንዲሁም ለአንድ ዓላማ ሕዝባዊ አንድነት ፈጥረን ቀጣይ የትግል መስመሮችን አብረን በመጓዝ ለበለጠ ድል የምንበቃበትን መንገድ የሚተልም መሆኑን መላው ሕዝባችን ሊገነዘበው ይገባል።

የክልላችን መንግሥት ዛሬም ሰላም የሁልጊዜም ብቸኛ አማራጫችን እደሆነ ያምናል። ስለሆነም ከሀገር መከላከያ ሠራዊት እና ከሌሎች ጥምር የፀጥታ ኃይሎች ጋር በመሆን የሀገር አንድነትን እና ሉዓላዊነትን ለማስጠበቅ በፅናት የተዋደቁ ሰማዕታትን ጀግንነት ከንቱ በሚያደርግ መንገድ የተሰለፋችሁ እንዲሁም የሕዝባችን ጥቅሞች ላይ በመቆም የተሳሳተ ዓላማ ውስጥ የገባችሁ ፅንፈኛ ግለሰቦች እና ቡድኖች ከእኩይ ድርጊታችሁ ተቆጥባችሁ መንግሥት ያስቀመጣቸው የሰላም አማራጮች ተጠቃሚዎች እንድትሆኑ ዛሬም ደግመን ደጋግመን እናሳስባለን።

በአንዳንድ ጽንፈኛ የማኅበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚዎች የሚደረገው ከመንግሥት የሕግ ማስከበር ዓላማ ውጭ የሆነ፤ የሕዝብን ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊ እና ማኅበራዊ ጥቅሞች የሚያሳጣ እና ሕዝባችን በየጊዜው እንታገልባቸው ዘንድ የሰጠን መሠረታዊ ችግሮቹ የሚፈቱበትን ስልቶች የማይደግፍ እንዲሁም ሀገርን ወደ ትርምስ የሚመራ የሁከት እና የብጥብጥ ቅስቀሳ ሁሉ ፈጽሞ ስህተት እና ክልላችን እና ሕዝባችንን ዋጋ የሚያስከፍል እንዲሁም ለተራዘመ ጊዜ የሚያጎሳቁል መሆኑን መረዳት ያስፈልጋል።

ስለሆነም በዚህ ክልል እና ሀገር አፍራሽ ተግባር ውስጥ ተሰማርታችሁ ብጥብጥ እና ሁከት የምትቀሰቅሱ እና የምትሳተፉ ግለሰቦች እና ቡድኖች ሁሉ ከድርጊታችሁ ልትቆጠቡ ይገባል።

“ሰላም የሁልጊዜም ብቸኛ አማራጫችን ነው!!”

የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት

Exit mobile version