ETHIO12.COM

ሻለቃ ዳዊት የአማራን የትጥቅ ትግል እንደሚመሩ እስክንድር ነጋ ይፋ አደረገ

” አሁን ህዝብ ነቅቷል። የሚቀረው የሃይል እርምጃ ነው” በማለት አውስትራሊያ የተናገሩት ሻለቃ ዳዊት ወልደ ጊዮርጊስ በአማራ ክልል ያለው የትጥቅ ትግል መሪ መሆናቸውን እስክንድር ነጋ አስታወቀ። እሱም ትግሉን በይፋ መቀላቀሉን ይፋ አደረገ።

ከሻዕቢያ ጋር የጠበቀ ግንኙነት ያላቸውና በደርግ ዘመን ሆን ተብሎ እንዲከሽፍ የተቀነባበረውን የመንግስት ግልበጣ የመሩት ሻለቃ ዳዊት ናቸው የአማራን ትግል ይመራሉ የተባሉት። ሻለቃ ዳዊት ከሻዕቢያ ጋር በመመሳጠር በፈጸሙት ሴራ የኢትዮጵያ ምርጥ ጄነራሎች መረሸናቸውና አስመራ አደባባይ አስከሬናቸው ጎዳና ላይ መጎተቱ ይታወሳል። ሻለቃ ዳዊት ከኢሳት ባልደረባ ሲሳይ አጌና ጋር በነበራቸው ቆይታ ሱዳን ድረስ በመመላለስ ኮሎኔል መንግስቱ ሃይለማሪያም ላይ ሊካሄድ የታቀደውን ግልበጣ ሲመሩና በቅርብ ሲከታተሉ እንደነበር መናገራቸው አይዘነጋም።

ዳዊት ወልደጊዮርጊስ – የጸረ ኢትዮጵያዊነት መገለጫ

 (የፒኤችዲ) ትምህርቱን አቋርጦ ወደ አገር ቤት መጣ። እርሱ እንደሚለው ትግሉን ለመቀላቀል ቢሆንም ዋናው ዓላማ ግን በደርግ ውስጥ በመግባት ለምዕራባዊ ኃይሎች ለመሰለል እንደሆነ የበኋላ ሥራው ይናገራል። እርሱ እራሱም ቢሆን ይህንን የሁለት ቢላዋ ጨዋታ ሊያስተባብል አይችልም። እንዲያውም በአንዳንድ ቃለመጠይቆች ሞቅ ሲለው እየዘላበደ እምነቱን ሰጥቷል።

ከረሃብተኞች ጉሮሮ ዘርፈው ከአገር የኮበለሉትና በከሃጂነት ሲፈለጉ የነበሩት ሻለቃ ዳዊት በየት በኩል ዞረው የአማራ መሪ እንደሆኑ በርካቶች ይጠይቃሉ። “የአማራ ድንበር ወለጋ ነው” በማለት ሁለቱን ብሄረሰቦች ለማናከስ ጥሪ ሲያቀርቡ ነገሩ ያላማራቸው አስቀድመው በህቡዕ የሚሰራ የትግል ቡድን እንዳለ ሲናገሩ እንደንበር መዘገባችን ይታወሳል።

የባልደራስ ፓርቲ መስራች እስክድር ነጋ “የአሁኑ መንግስት በአማራ ተወላጆች ላይ ግፍ እየፈፀ ነው” ሲል በድምጽ ምክንያቱን ገልጾ የትጥቅ ትግል መጀመሩን ይፋ ባድረገበት መልዕክት፣ ሻለቃ ዳዊት በውጭ አገር ያለው የትግሉ መሪ መሆናቸውን አስታውቋል።

“መነሻችንን አማራ መዳረሻችንን ኢትዮጵያ አድርገን የአማራ ህዝባዊ ግንባር መስርተን ወደ ትግል ገብተናል፣በውጭ ሃገር ያለውን ድጋፍ ለሚመሩት ሻለቃ ዳዊት ወልደጊዮርጊስ ተባበሯቸው” ሲል እስክንድ በድምጹ የትብብር ጥሪ አቅርቧል። በገሃድ ትግሉን መቀላቀሉንም አሳውቋል። የመታገያ ድርጅቱም የአማራ ህዝባዊ ግንባር እንደሆነ ገልጿል።

የክልሉ አመራርም ለሶስት ቀናት በዝግ ራሱን ገምግሞ ባለ ዘጠኝ ነጥብ የአቋም መግለጫ ማውጣቱ ይታወሳል። ክልሉን የሚመራው አማራ ብልጽግና አሁን የተመረጠው መንገድ ክልሉን የሚያራቁት፣ ኢኮኖሚውን የሚያሽመደምድ፣ ልማቱን የሚያከስም፣ ኢንቨስትመንትን የሚገድል ስለሆነ በጽኑ ለመታገል ሲወስን “ጽንፈኞች” ያላቸውን ሃይሎች ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ለመታገል መስማማቱን በመግለጽ ነው።

ቀደም ሲል የአማራ ብልጽግና መጠለፉንና መዋቅሩ ሳይቀር ተሰብሮ እንደነበር፣ የደህንነት ግብረ ሃይል ባወጣው ሪፖርት ይፋ ማድረጉ ይታወሳል። ይህንኑ ጠለፋና በክልሉ ሊደረግ የነበረውን ትርምስ ማክሸፉንም አስታውቆ ነበር።

የእስክንድር ነጋን የትጥቅ ትግል መቀላቀል ተከትሎ ባልደራስ ዛሬ ባካሄደው ጠቅላላ ጉባኤ፤ ወደ ሀገር አቀፍ ፓርቲነት ለማደግ የቀረበለትን ውሳኔ ማጽደቁን ይፋ አድርጓል።

ባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ ፓርቲ ወደ ሀገር አቀፍ ፓርቲነት ለማደግ ዛሬ እሁድ ግንቦት 13፤ 2015 ባካሄደው ጠቅላላ ጉባኤ ሲወሰን ። በምክትል ፕሬዝዳንትነት ሲያገለግሉ የቆዩት አቶ አምሃ ዳኘውን ፕሬዚዳንት አድርጎ በእስክንድ ምትክ ሾሟቸዋል።

አቶ እስክንድርን ለመተካት በዛሬው ጠቅላላ ጉባኤ ከቀረቡ ሶስት ዕጩዎች መካከል፤ የፓርቲው ምክትል ፕሬዝዳንት አቶ አምሃ ዳኘው ይገኙበታል። ለፕሬዝዳትነት ለመወዳደር የቀረቡት ሌሎች ዕጩዎች፤ የፓርቲው ብሔራዊ ምክር ቤት ጸሀፊ ዶ/ር በቃሉ አጥናፉ እና የፓርቲው የህግ ክፍል ኃላፊ የሆኑት አቶ ሳምሶን ገረመው መሆናቸውን ዜናውን የተከታተሉ ሪፖርት አድርገዋል።

አቶ ኤርሚያስ ለገሰ የባልደራስ የአሜሪካ ምዕራፍ መሪ እንደነበሩ አይዘነጋም። በሻለቃ ዳዊት ወልደ ጊዮርጊስ መመሪያ ከ360 የዩቲዩብ አውድ እንዲለቅ መደረጉን ያስታወቀው ኤርሚያስ አስቀድሞ ምን ሂሳብ አስልቶ ” እኔ ምንም ውስጥ የለሁበትም፣ የማናጅመንት አባልም አይደለሁም፣ በማናቸውም ውሳኔዎች ውስጥ የለሁበትም፣ ሃሳቤን ብቻ ይዤ ነው ስሠራ የነበረው” ለማለት እንደተነሳሳ ለበርካቶች አሁን ድረስ ግልጽ አልሆነም። እሱም አላብራራም። በደፈናው ብብሄሩና በአመለካከቱ ሳቢያ ጫና ይደረግበት እንደነበር አመልክቷል።

ሂደቱን የሚከታተሉ ዜናው እንዳሳሰባቸው እየገለጹ ነው። በተለይም ትህነግ የኤርትራን መንግስት እየከሰሰ መሆኑ ምን አልባትም የትግሉን ጨዋታ እንዳያሰፋው ፍርሃቻ አላቸው። እነዚህ ወገኖች በአማራ ክልል በኩል አለ የሚባለውን ችግር ዘርዝሮ በውይይት መፍታቱ እንደሚሻልም ይገልጻሉ።

Exit mobile version