Site icon ETHIO12.COM

በሕገወጥ መንገድ አገር ውስጥ በገቡ ተሽከርካሪዎች ላይ አደን ሊጀመር ነው

ካለፉት ዘጠኝ ዓመታት ጀምሮ በሕገወጥ መንገድ የገቡ ተሽከርካሪዎች ላይ እርምጃ እንደሚወሰድ የአዲስ አበባ አሽከርካሪና ተሽከርካሪ ፍቃድና ቁጥጥር ባለሥልጣን አስታወቀ።

በባለሥልጣኑ የተሽከርካሪ ዘርፍ ምክትል ዋና ዳይሬክተር በድሉ ሌሊሳ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደተናገሩት፤ መንግሥት ሕገወጥነትን ለመከላከል በርካታ ሥራዎችን እየሠራ ሲሆን፤ ከዚህም ውስጥ አንዱ ካለፉት ዘጠኝ ዓመታት ጀምሮ በሕገወጥ መንገድ የገቡ መኪናዎችን የመለየት ሥራ አንዱ ነው። ይህም ከተጀመረ አንድ ወር ሆኖታል።

‹‹ባለሥልጣኑ ከአዲስ አበባ ገቢዎች ቢሮ ጋር በጋራ በመሆን ባደረገው ጥናት በባለሥልጣኑ የሚመዘገበው የገንዘብ መጠን እና ለገቢዎች ቢሮ የሚቆረጠው ደረሰኝ ተመሳሳይ ያለመሆን ሁኔታዎች አሉ። በዚህም በተለይ የአዲስ ተሽከርካሪዎች ዋጋ የሚቆረጥበት ደረሰኝና ገዢዎች ለመኪናው የሚከፍሉት ዋጋ ሰፊ ልዩነት ያለው መሆኑ ተረጋግጧል፡፡›› ብለዋል።

በዚህም መንግሥት ከተሽከርካሪዎች ግዥና ሽያጭ ማግኘት የሚገባውን የታክስ ገቢ እያገኘ አለመሆኑን የገለጹት ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ፤ ይህንን እና መሰል ችግሮችን ለመቅረፍ ካለፉት ዘጠኝ ዓመታት ጀምሮ በሕገወጥ መንገድ የገቡ መኪናዎችን የመለየት ሥራ መጀመሩን ተናግረዋል።

‹‹ተቋሙ በተለያዩ ጊዜያት ኹለት አይነት ሕገወጥ ተግባራት ይገጥሙታል›› ያሉት ኃላፊው፤ እነሱም ከክልል በዝውውር የሚመጡ መኪናዎች ላይ እና በተጭበረበረ ሰነድ የተመዘገቡ መኪናዎች መሆናቸውን ጠቅሰዋል።
https://t.me/addismaleda

Exit mobile version