ETHIO12.COM

19 የመደ ወላቡ ዩኒቨርሲቲ ከሞቱበት አደጋ ለምስክርነት የተረፈው ብቸኛ መምህር ምስክርነት

ከሳምንት በፊት በኦሮሚያ ክልል በምዕራብ አርሲ ዞን የደረሰው አስከፊ የትራፊክ አደጋ የ19 የመደ ወላቡ ዩኒቨርሲቲ ሠራተኞችን ሕይወት ሲቀጥፍ በ18 ሰዎች ላይ ደግሞ የተለያየ መጠን ያለው ጉዳትን አደርሷል።

የብዙዎችን ሕይወት ከቀጠፈው እና የአካል ጉዳትን ካስከተለው ከዚህ አደጋ ታዲያ ሁለት መምህራን ምንም አይነት ጉዳት ሳይደርስባቸው በሕይወት መትረፍ ችለዋል።

ከእነዚህ መምህራን አንዱ ደግሞ ደስታ ሙላቱ ነው።

በአደጋው በተከሰተበት ጊዜ ያ ቅጽበት የሕይወቱ ፍጻሜ እንደሆነ አምኖ የነበረው መምህር ደስታ፤ ከአስከፊው አደጋ በሕይወት መትረፉን የፈጣሪ ተዓምር ነው ይላል።

ቅዳሜ ግንቦት 12/2015 ዓ.ም. ከ50 ያላነሱ የመደ ወላቡ ዩኒቨርሲቲ መምህራን በማታው እና በሳምንቱ ማብቂያ ቀናት (ኤክስቴሽን) በሚሰጠው የትምህርት መርሃ ግብር በሻሸመኔ እና ዶዶላር ካምፓሶች ያሉ ተማሪዎችን ለማስተማር ንጋት 11፡30 ላይ ነበር ከሮቤ የተነሱት።

ይሁን እንጂ ሲጓዙበት የነበረው ተሸከርካሪ በምዕራብ አርሲ ዞን ውስጥ “ዎሻቲ” ተብሎ በሚጠራ አካባቢ ሲደርስ መንገድ ስቶ ወደ ገደል ውስጥ ገብቷል።

በዚህም አሰቃቂ አደጋ የ19 የዩኒቨርሲቲው መምህራን ሕይወት ሲያልፍ በርካቶች ላይ ደግሞ ቀላል እና ከባድ ጉዳት መድረሱን ዩኒቨርሲቲው ይፋ አድርጓል።

አደጋው ቅጽበት

“ዶዶላ ጠዋት 2፡30 ላይ ለመድረስ ከሮቤ ከተማ ንጋት 11፡30 ላይ ወጣን” የሚለው ደስታ ያሰቡት ሳይሳካ ከመንገድ መቅረታቸውን ያስታውሳል።

ምንም እንኳ ስለዚህ አስከፊ የትራፊክ አደጋ መንስዔ በይፋ የተባለ ነገር ባይኖርም፣ መምህር ደስታ ግን ሲጓዙበት የነበረው ተሸከርካሪ የቴክኒክ ችግር እንደነበረበት ይናገራል።

“የተሳፈርንበት መኪና ችግር ነበረበት። ሰብስቤ ተብሎ የሚጠራ ቦታ ስንደርስ ሹፌሩ መኪናውን አቁሞ ከመኪናው ስር በመግባት የሆነ ነገር ሲያስተካክል ነበር” ይላል መምህር ደስታ።

ከዚህ በተጨማሪም አሸከርካሪው እና ረዳቱ ሕዝብ ጫኝ መኪናው ችግር እንዳለበት ሲነጋገሩ እንደነበር እና ተሳፋሪዎችም በፍሬን ችግር ምክንያት አሸካርካሪው መኪናውን ለመቆጣጠር እየተቸገረ ስለመሆኑ ሲያወሩ ነበር ይላል።

መምህር ደስታ እንደሚለው የመኪናው አሸካርካሪ ጥገናውን ካደረገ እና ጉዟቸውን ከቀጠሉ ከጥቂት ደቂቃዎች በኋላ አደጋው አጋጥሟል።

“ሁለት ደቂቃ እንኳ ሳንጓዝ ነው መኪናው በከፍተኛ ፍጥነት ተጉዞ ወደ አየር ላይ ተወርውሮ ቁልቁል ወደ ገደለ ገባ።…መሪውም፤ ፍሬኑም አልሰራ ብሎ አራቱም ጎማ ልክ እንደ አውሮፕላን አየር ላይ ሆኖ ቁልቁል ነበር የተወረወረው” በማለት መምህር ደስታ አደጋው ከመድረሱ በፊት የነበረውን ቅጽበት ያስታውሳል።

ከዚህ አስከፊ አደጋ ምንም አይነት ጉዳት ሳይደርስበት በመትረፉ “ትልቅ ደስታ አለኝ፤ ፈጣሪንም አመስግናለሁ” የሚለው መምህር ደስታ፤ ጉዳት ሳይደርስበት በሕይወት የተረፈው ተቀምጦ የነበረበት ቦታ እንዲሁም አደጋው ሲደርስ ከወንበሩ ባለመንቀሳቀሱ ሊሆኑ እንደሚችል ይገምታል።

“መጨረሻ አካባቢ ነበር የተቀመጥኩት። ከመጨረሻ ረድፍ ሁለተኛው ላይ። አብዛኞቹ ሕይወታቸውን ያጡት ከፊት ወንበር አካባቢ የተቀመጡት ናቸው። ካለቁት መካከል አብዛኛዎቹ በድንጋጤ [መኪናው ገደል ከመግባቱ በፊት] ተነስተው የቆሙት ናቸው” ይላል።

“እንደ ዕድል ሆኖ አጎንብሼ ተቀምጬ ነበር። መኪናው አየር ላይ ሆኖ ሲበር ጭንቅላቴን ይዤ አቀርቅሬ ነበር። በዚያ ቅጽበት ሁላችንም አለቅን ብለን ነበር። ወደ ሞት እየሄድን እንደሆነ ተሰማን። መኪናው ገደሉ ውስጥ እስኪከሰከስ ድረስ በተስፋ መቁረጥ እየተጠባበቀን ነበር” የሚለው ደስታ ከአደጋው በፊት የተሳፋሪዎች ጩኽት ጎልቶ ይሰማ እንደነበር ያስታውሳል።

“መኪናው ገደሉ ውስጥ ከመሬት ጋር ተላትሞ ከተሰባበረ በኋላ በየአቅጣጫው ተበተንን። እኔ ግን ምንም አይነት ጉዳት አልደረሰብኝም። ላፕቶፕ ከምፒዩተሬ እና ስልኬ እንኳ ምንም ሳይሆኑ በወደቅኩበት ከጎኔ አገኘኋዋቸው። የሰዎች አስክሬንን አልፌ በእራሴ ከገደሉ ወጣሁ” በማለት የነበረውን ሁኔታ ይገልጻል።

ክፉኛ የተጎዳው የትምህርት ክፍል

በመደ ወላቡ ዩኒቨርሲቲ የኢንፎርሜሽን ሳይንስ መምህር የሆነው ደስታ ሙላቱ ከአደጋው በኋላ ወደ ሮቤ ከተማ የተመለሰ ሲሆን፣ አንገቱ ላይ ሕመም ተስምቶት የኤክስሬይ ምርመራ ቢያደርግም ምንም ችግር እንደሌላበት በሐኪሞች ተነግሮታል።

በአደጋው የአስራ ዘጠኝ ባልደረቦቹ ሕይወት ማለፉ ያሳዘነው መምህር ደስታ፣ “እኔ በተዓምር ያለምንም ጉዳት በሕይወት መትረፌ ዕድለኛ የሆንኩ ያህል ይሰማኛል” ይላል።

በመደ ወላቡ ዩኒቨርሲቲ ሠራተኞች ላይ የደረሰው አስከፊ አደጋ የመማር ማስተማር ሥራው እንዲቋረጥ ያደረገ ሲሆን፣ በተለይ ደግሞ በስፖርት ሳይንስ የትምህር ክፍል ላይ ከፍተኛ ጉዳት መድረሱን መምህር ደስታ ይናገራል።

“አብረን የወጣን መምህራን መንገድ ላይ መቅረታቸውን ማመን አልቻልኩም። አሁን ራሱ መልሰን እንደምንገናኝ ነው የማስበው” በማለት በሥራ ባልደረቦቹ ሕልፈት የተሰማው ሐዘን ጥቅል መሆኑን ይገልጻል።

ቢቢሲ አማርኛ

Exit mobile version