Site icon ETHIO12.COM

የሰብአዊ መብት ኮሚሽን ሰነድ የሌላቸው የኤርትራዊ ስደተኞች መታሰራቸውን ኮነን፤ “ያለ ህጋዊ ማስረጃ የትኛው አገር መኖር ይቻላል?”

በቅርቡ የተከበረው 29 "የነጻነት ቀን" በዓል አስመራ

በስደተኞች እና ጥገኝነት ጠያቂዎች ላይ የዘፈቀደ እስር ሊቆም እንደሚገባ ጠቅሶ የኢትዮጵያ ሰብአዊ ኮሚሽን መንግስትን ኮነነ። ” በዓለም የትኛው አገር ያለ ህጋዊ ፈቃድና ሰነድ ማንም እንደፈለገ እንደሚኖር ቦታና ስም ጠቅሶ ለልምድ እንዲሆን ኢሰመኮ ቢያስረዳን ጥሩ ነበር” ሲሉ ኢትዮ12 የነጋገራቸው አንድ ሃላፊ አስተያየት ሰጥተዋል።

መንግስት የኤርትራ ተወላጆች ምንም እንኳን ኢትዮጵያን እንደ ቅኝ ያዢ አገር፣ እንዲሁም በኢትዮጵያ ሲኖሩ ልዩ መድልዎ ይደረግባቸው እንደነበር ታስቦ ” ነጻነት” በሚል ኤርትራዊ መሆንን ከመረጡ በሁዋላ መድልዎ እንዳላደረገ የገለጹት ሃላፊው፣ ” ኮሚሽኑ ህጋዊ ሰነድ መጠየቅ በየትኛው አገር ህገወጥ ተግባር ተደርጎ እንደሚያስነቅፍ ቢያብራራ መልካም ነበር” ብለዋል።

ስማቸውን ሳይጠቅሱ ምላሽ የሰጡት ሃላፊ ” ህጋዊ ሰነድ የሌለው ማንም ይሁን ማን ህጋዊ እስካልሆኑ ድረስ መጠየቃቸው አግባብ ነው” ካሉ በሁዋላ ” ኢትዮጵያ ስደተኞችን ተቀባይ አገር ናት። የኤርትራ ስደተኞችም ደግሞ ቤታቸው ቢሆንም ሰነድ አሟልተው ህጋዊ ሊሆኑ ይገባል። እነሱ ብቻ ሳይሆኑ ከበርካታ አገር የመጡ ሰነድ አልባዎች ላይ የህግ አግባባ የተከተለ ስራ ተሰርቷል። ለምን ሰነድ ተጠየቅን ማለትና፣ ለምን ህጋዊ እንዲሆኑ ተጠየቁ ብሎ መቃወም የአንድን አገር ብሄራዊ ክብር መጋፋት ነው” ብለዋል። የግል አስተያየታቸውን የሰጡት እኚሁ ሃላፊ መንግስትን ለመቃወም ሲባል ብቻ በየትኛውም አገር የማይደረግን ነገር የኢትዮጵያ መንግስት እንዲያደርግ መግፋት በዜጎች ደህንነት ላይ አደጋ እንዲፈጠር መመኘት እንደሆነ ገልጸዋል። ከጊዜው መግለጽ አልፈለጉም እንጂ በርካታ ሰነድ አልባ ወንጀለኞች መያዛቸውንም አመልክተዋል።

ኮሚሽኑ በማህበራዊ ገጹ የሚከተለውን አስፍሯል።

የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) በአዲስ አበባ ከሚገኙ በተለይ በኤርትራዊያን ስደተኞችና ጥገኝነት ጠያቂዎች በቀረቡ አቤቱታዎች መሠረት ባደረገው ክትትል፣ “የማስረጃ ሰነድ የላችሁም” በሚል ምክንያት በፖሊስ የተያዙ፣ በተለያዩ ክፍለ ከተሞች ለእስር ከተዳረጉት በመቶዎች የሚቆጠሩ ስደተኞች እና ጥገኝነት ጠያቂዎች መካከል ያለ ፍርድ ቤት ትእዛዝ በፖሊስ ቁጥጥር ስር የዋሉ፣ ክስ ሳይመሠረትባቸው በእስር የቆዩ መኖራቸውን እና በተለያየ ጊዜ በቁጥጥር ስር ከዋሉ በኋላ በአብዛኛው የተለቀቁ መኖራቸውንም ኮሚሽኑ መመልከቱን ገልጿል።

ኢሰመኮ የእስሩ ሰለባ የሆኑ በርካታ ስደተኞች እና ጥገኝነት ጠያቂዎችን በንፋስ ስልክ ላፍቶ እና በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ፖሊስ መምሪያዎች በመገኘት ክትትል ያደረገ ሲሆን፣ ግለሰቦቹ ከተያዙ በኋላ ፍርድ ቤት ሳይቀርቡ ከ10 ቀናት በላይ በእስር ላይ መቆየታቸውን፣ በፖሊስ ቁጥጥር ስር የዋሉበት ምክንያትም “ስደተኛ መሆናችሁን የሚገልጽ የሰነድ ማስረጃ የላችሁም”፣ “ከካምፕ ለመውጣት ፈቃድ ሳይኖራችሁ ከተማ ውስጥ ተገኝታችኋል”፣ “የሥራ ፈቃድ ሳይኖራችሁ በሥራ ላይ ተሰማርታችኋል’’ በሚል መሆኑን ኮሚሽኑ ተረድቷል፡፡

በተጨማሪም ስደተኝነታቸውን የሚያሳይ ያልታደሰ መታወቂያ እያላቸው በእስር ላይ የሚገኙ ስደተኞች መኖራቸውን፣ በአብዛኛው ደግሞ ጉዳያቸው እየተጣራ ስደተኛ ለመሆናቸው የሰነድ ማስረጃ ያላቸው እየተለቀቁ መሆኑን፣ የተወሰኑት ደግሞ ጉዳያቸውን በአግባቡ ለማስረዳት የቋንቋ ችግር እንደገጠማቸው ጭምር ኮሚሽኑ ለመገንዘብ ችሏል፡፡

መንግሥት ለስደተኞች ተገቢውን ጥበቃ እንዲያደርግ በዓለም አቀፍ እና በብሔራዊ ሕጎች ግዴታ የተጣለበት በመሆኑ በስደተኞች እና ጥገኝነት ጠያቂዎች ላይ ያለ ሕግ አግባብ የሚደረግ እስር በነጻነት የመንቀሳቀስ መብታቸውን ከመገደቡም ባሻገር ለስደተኞች የሚደረገውን ጥበቃ እና ከለላን ጨምሮ ላሉባቸው ችግሮች ዘላቂ መፍትሔን ለመስጠት የሚደረገውን ጥረት አደጋ ላይ ይጥላል፡፡

ኢሰመኮ ይህንን ጉዳይ በተመለከተ ከስደተኞች እና ተመላሾች አገልግሎት ከፍተኛ ኃላፊዎች እንዲሁም ከፌዴራል የፍትሕ አካላት ጋር የተነጋገረ ሲሆን፤ ጊዜው ያለፈበት/ያልታደሰ የመታወቂያ ሰነድ የያዙ፣ አልያም ከካምፕ ለመውጣት ፈቃድ ሳይኖራቸው ከተማ ውስጥ ሲንቀሳቀሱ የተገኙ ስደተኞችን በተመለከተ በሚመለከተው የፌዴራል ፖሊስ አካል እና በስደተኞች እና ተመላሾች አገልግሎት መካከል የሰነድ ማጣራት እና የማመሳከር ሥራ እየተሠራ መሆኑን እና በዚህ ሁኔታ ውስጥ ያሉ ስደተኞች ከእስር የሚለቀቁበት አሠራር እንደተዘረጋ ተገልጾለታል። ኃላፊዎቹ የስደተኞች እና የጥገኝነት ጠያቂዎች የመታወቂያ እድሳት ወይም የመታወቂያ አገልግሎት ላለፉት ሁለት ዓመታት የተቋረጠ መሆኑን በተመለከተ፣ አሠራሩን በዲጂታል ቴክኖሎጂ እንዲደገፍ ለማድረግ ታልሞ በጊዜያዊነት የተቋረጠና አዲሱ የምዝገባ ሥርዓት ተግባራዊነቱ በታሰበው ፍጥነት ያልተቀላጠፈ ቢሆንም፣ በቅርቡ ተግባራዊ እንደሚደረግ ገልጸዋል።

የኢሰመኮ ምክትል ዋና ኮሚሽነር ራኬብ መሰለ የተፈጠረውን ችግር ለመፍታት በመንግሥት የጸጥታ አካላት እና በስደተኞች እና ተመላሾች አገልግሎት መካከል በተወሰነ መልኩ ውይይትና መረጃ መለዋወጥ መኖሩ ጥሩ መሆኑን ገልጸው፣ “ይሁንና ዘላቂ መፍትሔ የሚሆነው ለሁለት ዓመታት ተቋርጦ የቆየውን የስደተኞች እና ጥገኝነት ጠያቂዎችን ምዝገባ እና መታወቂያ እድሳት በአፋጣኝ ተመልሶ እንዲጀመር ማስቻል ነው ብለዋል”።

ምክትል ዋና ኮሚሽነሯ አክለውም ከስደተኞች እና ጥገኝነት ጠያቂዎች መካከል በወንጀል ድርጊት የተጠረጠሩ ሰዎች ካሉም በመደበኛው የወንጀል ሥነ-ሥርዓት ደንቦች መሠረት በተገቢው ጥንቃቄ ልየታ በማድረግ በሕግ አግባብ ብቻ የሚፈጸም ሊሆን እንደሚገባ አስታውሰው፤ ከዚህ ውጪ ያለአግባብ በእስር ላይ ያሉ ስደተኞች እና ጥገኝነት ጠያቂዎች ካሉ ኮሚሽኑ ክትትሉን የሚቀጥል መሆኑን ገልጸዋል፡፡

Exit mobile version