ETHIO12.COM

አሜሪካ በኢትዮጵያ ላይ ጥላው የነበረውን የሰብዓዊ መብት ጥሰት ክስ አነሳች፤ ኢትዮጵያ የተያዘባት ብድርና እርዳታ ይለቀቃል

ዜናው በኑሮ ውድነትና በኢምፖርት ላይ የተጋረጠውን ችግር የሚቀርፍ ትልቅ ብስራት ቢሆንም መርዶና ችግርን የሚዘግቡ ተደጓሚና ታዛዥ ሚዲያዎችን ጨምሮ በርካቶች ልክ እንደ ባህር ሃይል ዳግም ውልደት ዜና በዝምታ አልፈውታል፤ ዜናው ታላቅ የፖለቲካ እንደምታና ኢትዮጵያ ላይ በፍርደ ገምድልነት ሲጫን የነበረው ቀንበር መሰበሩን የሚያሳይ ቢሆንም በርካታ ሚዲያዎችን ማስከፋቱ አስገራሚ ሆኗል

የፕሬዚዳንት ጆን ባይደን አስተዳደር የወሰደው ይህ እርምጃ የአሜሪካና የዓለም አቀፍ ኢኮኖሚያዊ ዕርዳታ ወደ ኢትዮጵያ መላክን ለማስቀጠል መንገድ የሚከፍት መሆኑንን ጠቅሶ ፎሬይን ፖሊሲ ዜናውን ይፋ አድርጎታል። ቁልፍ መረጃዎችን ይፋ የሚያደርገው ፎሪን ፖሊሲ አሜሪካ በኢትዮጵያ ላይ ጥላው የነበረውን የሰብዓዊ መብት ጥሰት ክስ አነሳች በሚል መግቢያ ያሰራጨው ዜና አገራቸውን ለሚወዱና በክሱ ምክንያት ኢትዮጵያ ላይ ተጥሎ የቆየው ማዕቀብ ያደረሰው ጉዳት ለገባቸው መረጃው ሰበር ዜና ሆኖላቸዋል።

በሌላ በኩል የተራ ፌስ ቡክና ቲዊተር ቅንጣቢ በመልቀምና በመጠጋገን እንዳሻቸው ዜና የሚሰሩና የሚያሰራጩ የውጭ ተከፋይ ሚዲያዎችን ጨምሮ አገር ቤት ያሉ መገናኛዎች ዜናውን አጉልተው አለማስተጋባታቸው ግራሞትን እንደፈጠረ አስተያየት ተሰጥቷል።

አሜሪካ ከሰብዓዊ መብት ጥሰት ጋር በተያያዘ ኢትዮጵያ ላይ ያሳለፈችውን ውሳኔ ማንሳቷን ፎሬይን ፖሊሲ የፕሬዜዳንት ባይደን አስተዳደር ደብዳቤ ጠሶ ” ኢትዮጵያ አሁን ላይ በከፍተኛ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ውስጥ እየተሳተፈች አይደለችም ” በሚል ለኮንግረሱ ማሳወቁን ይፋ አድርጓል።

የትግራይ ነጻ አውጪ ግንባር መከላከያን አርዶና ዘርፎ አማራና አፋርን ክልልን ሲወር፣ በአሜሪካና አውሮፓ ህብረት ሙሉ ድጋፍ ስለነበረው የኢትዮጵያን መንግስት ሙሉ በሙሉ ተጠያቂ ለማድረግ ከፍተኛ ዘመቻ መደረጉ ይታወሳል።

የዓለም ታላላቅ የሚባሉ አገራት መሪዎች፣ ተቋማት፣ ሚዲያዎች፣ የተባበሩት መንግስታትን ጨምሮ ኢትዮጵያ ላይ ሲረባረቡ በነበረበት ወቅት ” አግባብ አይደለም” በሚል ሲሟገቱ የነበሩ ወገኖች ” እንኳን ደስ ያላችሁ” ሲሉ ዜናውን ተቀባብለውታል።

ጦርነቱ ባስከተለው ውድመት፣ ዝርፊያና አጠቃላይ ኪሳራ የተወጠረችው ኢትዮጵያ ወደ አገር ውስጥ የምታስገባው ምርት እጥረት በከፍተኛ ደረጃ ፈተና ሆኖባት ሰንብቷል። ብድርና እርዳታ ተይዞባት፣ የራሷንም ገንዘብ እንዳታንቀሳቅስ ተግታ መድሃኒት እንኳን በቅጡ ለማስገባት መከራዋን ስታይ የቆየችው ኢትዮጵጵያ በውስን ወዳጆች እርዳታ ይህን ጊዜ እንዳለፈች በርካታ መረጃዎች አሉ።

በውስጥ ካለው ሌብነትና የንግድ የተናበበ አሻጥር፣ የሚዲያ ዘመቻና አድሏዊ ውሳኔ ህዝቧ ለችግር የተጋለጠባት ኢትዮጵያ ይህ ቀንበር እንዲነሳላት መወሰኑ የፖለቲካው ፋይዳው እጅግ ትላቅ ቢሆንም፣ በማህበራዊና ኢኮኖሚ ቀውሱ ለተማረሩ ዜጎች መልካም ዜና ሆኖ አለመቅረቡ ያስገረማቸው ” ኢትዮጵያ ውስጥ መርዶ ካልሆነ በስተቀር ሌላ ዜና እንዳይሰራ ማዕቀብ ተጥሎ እንደሆነ ግልጽ ይነገረን” ሲሉ ተደምጠዋል።

“ይህ ውሳኔ የአሜሪካ እና የዓለም አቀፍ ኢኮኖሚያዊ ዕርዳታ ወደ ኢትዮጵያ መላክን ለማስቀጠል መንገድ የሚከፍት ነው” ሲል ፎሪን ፖሊሲ የዜናውን እምብርት አሳይቷል።

አሁን ላይ ከሰብዓዊ መብት ጥሰት ጋር በተያያዘ የባይደን አስተዳደር የወሰደው እርምጃ አሜሪካ ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ግንኙነት ለማሻሻል የጀመረችውን እንቅስቃሴ ለማጠናከሯ ማሳያ እንደሆነና በቀጣይም ይህንኑ ግንኙነት ለማሻሻል እየሰራች ባለችበት ወቅት ላይ መሆኑን ፎሬይን ፖሊሲ አጽኖት ሰጥቶ ዘግቧል።

የአውሮፓ ህብረትም ከኢትዮጵያ ጋር ስትራቴጂክ አጋር ሆኖ ለመቀጠል መውሰኑንን ማስታወቁና ኢትዮጵያ በቀይ ባህር ላይ ቁልፍ የአውሮፓ ወዳጅ አገር እንደሆነች ማስታወቁ አይዘነጋም። ከዚሁ ጋር ተያይዞ ይሁን በሌላ በግልጽ ባይታወቅም ኢትዮጵያ ግዙፍ የባህር ሃይል አደራጅታና በመሳሪያ አዘምና ለማናቸውም ግዳጅ ዝግጁ ማድረጓን ባለፈው ሳምንት ይፋ ማድረጓ ይታወሳል። በተመሳሳይ ይህም ዜና ከላይ ለተጠቀሱት አካላትና ሚዲያዎች ዜና አልሆነላቸውም መባሉ ይታወሳል። ባህር ሃይል ከሰላሳ ዓመት በፊት የትግራይ ነጻ አውጪ በገሃድ እንዳፈረሰውና፣ ኢትዮጵያን ባህር አልባ አድርጎ ማስቀረቱ የሚታወስ ነው።

Exit mobile version